Get Mystery Box with random crypto!

አዲሱ አዋጅ “ስለ መኖሪያ ቤት ኪራይ ውል” ዘመን ምን ዝርዝር ይዟል? ዛሬ በፓርላማ በጸደቀው | Muktarovich Ousmanova

አዲሱ አዋጅ “ስለ መኖሪያ ቤት ኪራይ ውል” ዘመን ምን ዝርዝር ይዟል?

ዛሬ በፓርላማ በጸደቀው “የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ” ከተዘረዘሩ ድንጋጌዎች ውስጥ፤ “የመኖሪያ ቤት የኪራይ ውል ዘመንን” የሚመለከቱት የሚጠቀሱ ናቸው። “የመኖሪያ ቤት ኪራይ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ አይችልም” ሲል የደነገገው አዋጁ፤ ይህ የተደረገበትን ዋነኛ ምክንያት በማብራሪያው ላይ አስፍሯል።

“የአዋጁ ዓላማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ በመሆኑ፤ [ውሉ] ከሁለት ዓመት ያነሰ ቢሆን አከራዩ ውሉን ለማደስ ፍቃደኛ ላይሆን ስለሚችል፤ ተከራይ በየጊዜው በቀጣይ ስለሚከራየው ቤት በመጨነቅ የተረጋጋ ህይወት እንዳይመራ ያደርገዋል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ አትቷል። “ከሁለት ዓመት ያለፈ ዘመን ይኑረው ቢባል ደግሞ የአከራይን መብት እንዳይጫን፤ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የውል ዘመኑ ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ እንዲሆን” መደረጉን የአዋጁ ማብራሪያ አስገንዝቧል።

“አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከሁለት ዓመት በታች የተደረጉ የቤት ኪራይ ውሎች ላይ ይህንን አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ ፍትሐዊ ስለማይሆን፤ በውላቸው ላይ ያጸደቁት ቤት ኪራይ የውል ዘመን ተቀባይነት እንዲያገኝ ተደርጓል” ሲል ማብራሪያው አክሏል። ከዚህ በተጨማሪ የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ፤ የአንድ ቤት ባለቤትነት “በውርስ፣ በሽያጭ፣ በዕዳ ወይም በሌላ ማናቸውም ህጋዊ ምክንያት” ለሌላ ወገን ከተላለፈ፤ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውሉ ሊቋረጥ የሚችለው “ቤቱ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ የሚቆጠር የ6 ወር ማስጠንቀቂያ ለተከራይ በመስጠት ቤቱን እንዲለቅ ማድረግ እንደሚቻል ማብራሪያው” ደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

* * ዝርዝሩን ከታች ከተያያዘው ምስላዊ መረጃ ይመልከቱ