Get Mystery Box with random crypto!

ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ መጋቢት 10/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች 1፤ በጋምቤላ ከተማ ሰ | Muktarovich Ousmanova

ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ መጋቢት 10/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በጋምቤላ ከተማ ሰሞኑን በጸጥታ ስጋት ሳቢያ የነዋሪዎች የዕለት'ተለት እንቅስቃሴ መገደቡንና ውጥረት መስፈኑን ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች። በከተማዋ ውጥረት የተፈጠረው፣ አንድ የከተማዋ ትራፊክ ፖሊስ አባል ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን ተከትሎ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል። በከተማዋ ትናንት አንዳንድ የንግድ ተቋማት ተዘግተው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

2፤ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ በተያዘው ዓመት ምንም ስኳር አለማምረቱን የመንግሥት ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፋብሪካው ስኳር ያላመረተው፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጩ የኾነው የቁንዝላ ኃይል ማመንጫ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ብልሽት ስለገጠመውና በፋብሪካው ላይ የማሽን አቅርቦት እጥረት በመፈጠሩ እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፋብሪካው ዘንድሮ 183 ሺህ ኩንታል ስኳር እንዲያመርት ታቅዶ የነበረ ሲኾን፣ ከጅምሩ ሲገነባ ግን በቀን 12 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም እንዳለው ተገልጦ ነበር።

3፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የስነ ሕዝብ፣ ስደትና ፍልሰት ረዳት ሚንስትር ጁሌይታ ኖይስ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል። ኖይስ፣ ትናንት ከተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ሃላፊ ራሚዝ አላክባሮቭ እና ከሌሎች የተመድ ሃላፊዎች ጋር ተመድ ለተረጂዎች በሚያቀርባቸው ሰብዓዊ ድጋፎች ዙሪያ መወያየታቸውን በ"ኤክስ" ገጻቸው ገልጸዋል። ረዳት ሚንስትሯ ዛሬና ነገ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ዓለማቀፍ አጋሮች ጋር ስደተኖችን በሦስተኛ አገራት በማስፈር፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ረድዔት ሠራተኞችን ከጥቃት በመጠበቅና ኢትዮጵያ ባለፈው ታኅሳስ ጀኔቫ ላይ በገባቻቸው የስደተኞች ቃል ኪዳኖች ዙሪያ ይወያያሉ።

[ዋዜማ]