በረመዷን ዉስጥ የተካሄዱ ትላልቅ ጦርነትና ድሎች 1) የበድር ጦርነት በረመዷን 17ኛው ቀን ሁለ | ABX
በረመዷን ዉስጥ የተካሄዱ ትላልቅ ጦርነትና ድሎች
1) የበድር ጦርነት
በረመዷን 17ኛው ቀን ሁለተኛው ዓ.ሂ ላይ የተካሄደ በኢስላም ታሪክ የመጀመሪያው ትልቁ ጦርነት ነበር። ሙስሊሞች በቁጥር ሦስት እጥፍ ያህል ከሚበልጣቸው የመካ ሰዎች ጋር ተፋልመው ትልቅ የሆነ ድል የተቀዳጁበት ነው። በድር በተለምዶ 'የውም አልፉርቃን/የመለያ ቀን' በመባልም ይታወቃል። እውነት ከሀሠት የተለየበት ቀን ነው። የበድር ድል ለሙስሊሞች ከፍተኛ የሆነ የሥነልቦናንም ያጎናፀፈ ሲሆን እነርሱን ሊያጠፉ ያሰፈሰፉ ጠላቶች አንገታቸውን የደፉበት ነበር።
2) የመካ መከፈት
የመካ ሙሽሪኮች ከሙስሊሞች ጋር የፈፀሙትን ስምምነት በመጣሳቸው የአላህ መልዕክተኛ ሰ.ዐ.ወ በረመዷን አሥረኛው ቀን ጦራቸዉን ይዘው ተንቀሳቀሱ። በረመዷን 20ኛው በድል መካ ገቡ። ከጠላት በኩል ከፍተኛ የሆነ መከላከል አልገጠማቸውም ነበር። ግና ድሉ ትልቅ ድል ነበር። ነብዩን ባልደረቦቻቸው ከዓመታት ስደት በኋላ ወደ ትውልድ ቀያቸው መመለስ ችለዋል። ነብዩ ሰ.ዐ.ወ መካ በድል ሲገቡ በከፍተኛ መተናነስ ዉስጥ ሆነው አላህንም አብዝተው እያመሰገኑ ነበር።
3) የተቡክ ዘመቻ
ነብዩና ባልደረቦቻቸው በረጀብ ወር ዘጠነኛው ዓ.ሂ. ነበር ይተንቀሳቀሱት። ዘመቻው 50 ቀናትን የፈጀ ሲሆን በተቡክ ሀያ ቀናትን ቆዩ። የተቀሩት ቀናት ሲሄዱና ሲመለሱ መንገድ ላይየፈጀባቸው ጊዜ ነው። በከፍተኛ ቁጥር ተሰባስቦ የነበረው ጠላት በመሸሹ ምክንያት ጦርነት ባይካሄድም ሙስሊሞች በዚህ ዘመቻ በየአካባቢ ጠላቶችን አጽድተዋል፣ በጠላቶቻቸው ላይም ከፍተኛ የሥነልቦና የበላይነትን ተጎናጽፈዋል።
4)በላጥ አሹሀዳእ
በ114 ዓ.ሂ ሸዕባን ወር መጨረሻ ላይ ተጀምሮ እስከ ረመዷን ወር መግቢያ ቀናት ድረስ የዘለቀ በሙስሊሞችና የመስቀል ጦረኞች መካከል የተደረገ ጦርነት ነበር። ዐብዱረሕማን ጦርነቱን መርቶታል። ሙስሊሞች ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው። መሪዉን ጨምሮ በርካታ ሠራዊትም አለቀባቸው።
5) የዐሙሪያ ጦርነት
አብን አል-አሢር እንደፃፉት የሩሞች ንጉሥ በሙስሊም አካባቢዎች ላይ ያደረሰው የዉድመት ዜና ለአል-ሙዕተሲም ደረሰው። በተጨማሪ ጦር የተማረከች አንዲት ሙስሊም ሴት 'ዋ ሙዕተሲማህ!' ሙዕተሲም ሆይ የት ነው ያለኸው! ብላ ተጣራች። ሙዕተሲም ጉዳዩ አንገበገበው። ዙፋኑ ላይ 'ለበይክ! አቤት ደረስኩልሽ' በማለት ወዲያዉኑ ጦሩን አዘመተ። ድልም ተቀዳጀ። ጊዜው 223 ዓ.ሂ በወርሃ ረመዷን ነበር።
6) የሓሪም ጦርነት
በአንፆኪያ አቅጣጫ ኤሌፖ አካባቢ በታላቅ ምሽግ ከታጠረ የጠላት ጦር ጋር የተደረገ ፍልሚያ ነው ። በ559 ዓ.ሂ በረመዳን ወር በኑረዲን ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው የሙስሊም ጦር ዉስጥ ሥፍራውን በተለያያ አቅጣጫ በማጥቃት ምሽጎችን በመሰባበር ድልን ሊጎናፀፍ ችሏል።
7) ዐይን ጃሉት
በረመዳን ወር 658 ዓ.ሂ ነበር ከተታሮች ጋር ነበር በፈለስጢን ምድር ናቡሊስ አካባቢ የተካሄደው። ጦርነቱን ከሙስሊሞች በኩል ስይፈዲን ቁጥዝ ነበር የመራው። ሰይፈዲን ቁጥዝ በታላቅ የአላህ ፍራቻ እና መተናነስ ዉስጥ ሆኖ ወደ ዐይን ጃሉት አመራ። በታሪክ በትልቁ ከሚወሱት ፍልሚያዎች አንዱ ሲሆን ከከባድ ዉጊያና እልቂት በኋላ የኋላ ኋላ ሙስሊሞች ትልቅ ድል አገኙ።
8 ) የሸቅሀብ ጦርነት
በሞንጎል ወራሪዎችና በሙስሊሞች መካከል በረመዷን ወር 702 ዓሂ የተካሄደ ነው። ኢብኑ ከሢር እንደዘገቡት
ተዋጊዎች እንዲያፈጥሩ ፈትዋ የተሠጠበት ነበር። ቀኑን ሙሉ ሲዋጉ ዉለው አመሻሽ ላይ ድሉ የሙስሊሞች ሆነ።
https://t.me/NejashiPP