Get Mystery Box with random crypto!

የኛና የነርሱ ከፍታ ለምን ተለያየ? (2) የጽሑፉ ምንጭ - የረመዳን ትርፋማ ስምምነቶች እና ወ | ABX

የኛና የነርሱ ከፍታ ለምን ተለያየ?
(2)
የጽሑፉ ምንጭ -
የረመዳን ትርፋማ ስምምነቶች እና ወርቃማ እድሎች መጽሐፍ
 
ዝግጅት፡- ዶ/ር በድር አብዱልሐሚድ
               ዶ/ር ሙሐመድ ራቲብ አን-ናብሉሲይ

ትርጉም እና ጥንቅር፡- ዐብዱልከሪም ታጁ

አንተ ያ ረመዷኑ! ከአላህ ጋር መገናኛ፤ ወደ እርሱ መቃረቢያ ወር ነህ፡፡ የቁርአን ወር ነህ፡፡ ቁርአን ተደጋግሞ የሚነበብብህ፣ ከቀልብ በሽታዎች ፈውስ የሚገኝብህ፣ ከኃጢያት ቆሻሻዎች የሚፀዱብህ፣ በእውቀት የሚበለፅጉብህ፣ በመልካም ሥራ የሚከብሩብህ፣ በዚክር የሚያጌጡብህ ... ልዩ ወር ነህ፡፡ ታዲያ እንዴት ፀጥታህ በግርግር፣ ዒባዳህ በዛዛታ ሊለወጥ ቻለ?
“ገሥጽም፤ ግሣጼ ምእመናንን ትጠቅማለችና፡፡” 
(አዝ-ዛሪያት፡ 55)
ቁርአኑ “አስታውስ” ብሏልና አንድ ነገር ላስታውሳችሁ ወደድኩ፡፡
ሰው ሁሉ አስቀድሞ ቢዘጋጅና እቅድ ቢያወጣ ብዬ ተመኘሁ፡፡ ፍጥነትህን በአንድ ጊዜ መቶ ላይ ማድረስ አትችልም፡፡ ቀስ በቀስ፣ ደረጃ በደረጃ ቢሆን እንጂ ከዜሮ ጀምረህ በድንገት መቶ ላይ መድረስ አትችልም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በረመዷን ወር መጀመሪያ ቀን ላይ ድንገት ልትለወጥ አትችልም፡፡ ከአንድ ቀን በፊት ከነበርክበት ሁኔታህ ባንድ ጊዜ ልትላቀቅ አትችልም፡፡
በፍፁም! ስለዚህ ቀደም ብለህ እራስህን አዘጋጅ፡፡ ከአሁኗ ሠዓት ጀምረህ ለዚህ ትልቅ ወር ተሰናዳ፡፡ ለዚህም ቀድመህ ልትከውናቸው የሚገቡ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ወሩ ከመግባቱ በፊት መጠናቀቅ ያለባቸውን ቤተሠባዊ፣ ድርጅታዊ ወይም ሌሎች ትላልቅ ጉዳዮች ቀድመህ ከውንና ወሩን ከእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ነጻ አድርገው፡፡ ቀጥለህ የመንፈስና የአካል ዝግጅት አድርግ፡፡ ሰላሳ ቀን አስተካክለህ ለመፆም፣ ሰላሳ ቀን የፈጅር ሶላት ከተቻለ በጀመዓ ቢያንሰ ቢያንሰ በወቅቱ ለመስገድ፣ ሰላሳ ቀን በየዕለቱ ቁርአን ለመቅራት፣ ሰላሳ ቀን ዓይንህን የምር ለመስበር፣ ሰላሳ ቀን እንቶ ፈንቶ ወሬዎችን እርግፍ አድርገህ ለመተው ካሁኑ ዝግጅት አድርግ፡፡
የወሩን ሰላሳ ቀናት በዚክር፣ በንባብ፣ በዒባዳ፣ ከአላህ ፊት በመቆም፣ ነፍስን በመታገል፣ ራስን በመፈተሸ፣ ህይወትህን በመመርመር... ለማሳለፍ ተዘጋጅ፡፡ ዛሬ ወሩ ሲያልፍ፣ ችግሮችህ በሙሉ አብረው ቢያልፉ ምን ይመስልሃል? ድካምህ ሁሉ አልፎ መላኮታዊ ሽልማትህ ብቻ ቢቀር፣ ፆመኛ ሁለት ደስታዎች አሉት፡- ፆም በሚፈታበት ቀን እና ከጌታው ጋር በሚገናኝባት ዕለት ተብሎ በሐዲሥ እንደተነገረው፡፡
ለዚህ ታላቅና ልዩ ወር ከአሁኗ ሠዓት ጀምሮ መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጉዳዮች ሊኖሩብን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን መወሰን አለብን፡፡ ዛሬውኑ መፍትሔ ልናበጅላቸው ወይም ከረመዷን በኋላ ልናዘገያቸው ይገባል፡፡ የቤተሠባዊም ይሁን የሥራ ጉዳዮቻችንን በሙሉ ዛሬ እንከውናቸው ወይም ባሉበት እንተዋቸው፡፡ ከዚያም ይህን ልዩ ወር ከአላህ ጋር ብቻ የምንኖርበት ወር እናድርገው፡፡

የአንድ ድርጅት አሥተዳዳሪ በሥሩ የሚገኝን አንድ ተቀጣሪ፣ በቀን ውስጥ አምስት ጊዜ እዚህ ቦታ እየሔድክ ለተወሰነ ጊዜ ቆመህ ተመለስ ብሎ ቢያዘው ወይም ምንም ትርጉም በሌለው ሥራ ሲያደክመው ቢውል ትክክለኛ ድርጊት ነው ብለህ ትቀበለዋለህ? በተመሳሳይ ሁኔታ ከምግብና ከውሃ ታቅበህ ነገር ግን የምታማ፣ የምትዋሽ፣ መገኘት ከሌለብህ ቦታ ላይ የምትገኝ ወይም ሙሰልሰል (ተከታታይ ፊልም) ላይ ተጥደህ የምትውል ከሆነ፣ ይህ ፆምህ የተለየ ፋይዳ እንግዲያስገኝልህ መጠበቅ አግባብ ይሆናልን?

ይቀጥላል ...

https://t.me/NejashiPP