Get Mystery Box with random crypto!

ማስታወሻ ስለ ጥሪ *** ማነው በቀደምለታ አንድ ወዳጃችን በሆነ ጉዳይ ጥሪ ነበረው፡፡ ከታዋቂዎችና | ABX

ማስታወሻ
ስለ ጥሪ
***
ማነው በቀደምለታ አንድ ወዳጃችን በሆነ ጉዳይ ጥሪ ነበረው፡፡ ከታዋቂዎችና ሀብታም ሰዎች በዛ ያሉትን፤ ከመካከለኞቹና ከድሆቹ ደግሞ በቁጥር አነስ ያሉትን ጠራ፡፡ ጥሪው ላይ በብዛት የተገኙት ግን የኋለኞቹ ነበሩ፡፡ የፊተኞቹ ግን ትሁት ከሆኑት አንድ ሁለቱ በስተቀር ሁሉም ሊያስብል በሚችል መልኩ ቀሩ፡፡

ደዕዋዎች፣ ሰርጎች፣ ለቅሶዎች … መለኪያቸዉና ደረጃቸው የታዋቂ ሰዎች መገኘት ሆኗል፡፡
አንዳንዴ ጥሪያችን ላይ ምን ዓይነት ከባባድ ሰዎች እንደተገኙ ለማሳየት ብለን ብቻ ድሆችን አልፈን ሀብታሞችን እንጋብዛለን፡፡ እነርሱም አይገኙልንም እኛም ብዙ ጊዜ አይሳካልንም፡፡ ድግሦች የፉክክር መድረክ ከሆኑ ቆዩ፡፡

የምግብ ድግስ ጥሪ ላይ ጉዳዩ በአብዛኛው የሚመለከተው ድሃዉን ነው፡፡ በፍትህ ዓለም ለሌለው ይሠጣል እንጂ ላለው አይጨመርለትም፡፡ ድሃ ተትቶ ሀብታም የሚጠራበት ሰርግ ምን ይከፋ! ይላሉ ነቢያችን ሰ.ዐ.ወ.፡፡

ከሁሉ በፊት በጥሪህ ላይ ንያህን አሳምር፤ ሰዉን ሳይሆን የአላህን ዉዴታ የምታገኝበትን መንገድ ፈልግ፤ አላህ ከወደደህ ሰው ይወድሃል፡፡ ታይታንና ዝናን እርሳ፡፡ ምንም ድሃ ቢሆኑም የጠዋት ጓደኞችህን አትርሳ፡፡ ጥሪህን ከጎረቤትና ከዘመድ ጀምር፡፡ የዑለሞችን፣ የሽማግሌዎችንና የቅን ሰዎችን ዱዓ ፈልግ፡፡ ድሆችን ብትጠራ በልተው ይደሠታሉ፤ ዑለሞችን ብታጋብዝ ከጌታህ እዝነትንና በረከትን ይለምኑልሃል፡፡

አንተ ደግሞ ወዳጄ ሆይ! ከጥሪ በመቅረት “እኔ በቀላሉ የምገኝ ሰው አይደለሁም፣ ስታንዳርዴ ከፍ ያለ ነው” የሚል ስሜት ያለው መልዕክት ለሌሎች አታስተላልፍ፤ በማሕበራዊው ሕይወት ዉስጥ ባለመሳተፍ ዋጋህንና ደረጃህን አትቆልል፤ እየተመቸህም ኦ እሱ ቢዚ ነው አይገኝም አይመቸዉም አታስብል፡፡

ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) የዓለማችን ታላቁ ሰው ከመሆናቸው ጋር ብዙ ወዳጆቻቸው ተራ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለሰዎች ጥሪም ከባድ ቦታ ይሠጡ ነበር፡፡ የድሃዉንም የሀብታሙንም፣ የባሪያዉንም የሠራተኛዉንም ጥሪ ተቀብለው ይገኙ ነበር፡፡ “በወንድም ጥሪ ላይ መገኘት ወንድምህ ባንተ ላይ ካለው መብት አንዱ ነው” ብለዋልም እርሣቸው፡፡

በርሣቸው ላይ የአላህ እዝነትና ሰላም ይስፈን፡፡


http://t.me/MuhammedSeidABX