Get Mystery Box with random crypto!

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በታክስ ኦዲት ስራ ጥሩ ውጤት የተገኘበት ነው - አቶ ተስፋዬ ቱሉ የታክ | M.O.R East Addis Ababa Branch

የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በታክስ ኦዲት ስራ ጥሩ ውጤት የተገኘበት ነው
- አቶ ተስፋዬ ቱሉ የታክስ ስርዓት ዘርፍ ሚኒስትር

ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም (ምስራቅ ገቢዎች) በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦዲት ስርዓቱን ግልፅ እና ተዓማኒ ከማድረግ እንዲሁም ሊታጣ የነበረ የመንግስት ገቢ ከማስቀረት አንፃር የተከናወኑ ስራዎች ውጤት የተመዘገበባቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ይህ የተገለፀው የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ኦዲት ዳይሬክቶሬት በአዳማ ከተማ እያካሄደ በሚገኘው የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ውይይት ላይ ነው፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ ስርዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ እንደገለፁት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ ግልፅ ራዕይ እና ተልዕኮ አስቀምጦ ለተግባራዊነቱ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዋነኛነትም ለታክስ ከፋዩ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት መስጠት፣ የታክስ ህግ ተገዢነት ስርዓትን ማስፈን እና ገቢን በአስተማማኝ ደረጃ ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የታክስ ኦዲት ውሳኔ ጥራትና ፍትሃዊነት ከማረጋገጥ አንፃር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ በተገባደደው በጀት ዓመት ከታክስ ኦዲት ጋር የተያያዙ ተግባራት አፈፃፀም እጅግ አበረታችና አመርቂ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም መላው የዳይሬክቶሬቱ እና የቅ/ፅ/ቤቶች አመራርና ስራተኞችን አመስግነው በቀጣይም ለተሻለ ውጤት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የታክስ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበበ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ለውጡን እየዘወሩ ከሚገኙ ተቋማት የገቢዎች ሚኒስቴር አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የታክስ ኦዲት ፖሊሲዎችን ከመፈተሽ ጀምሮ በርካታ የማሻሻያ ስራዎች መስራቱን ተናግረዋል፡፡ በ2010 የበጀት ዓመት 8 ቢሊየን ብር ብቻ የነበረውን የኦዲት ተደራሽነት ወደ 52 ቢሊየን ብር ማሳደግ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡ ተገቢ ያልሆነ ተመላሽና ኪሳራ እንዲሁም ከደረሰኝ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን ከመከላከል አንፃር ዳይሬክቶሬቱ ሰፋፊ ተግባራት ማከናወኑንም ጠቁመው በቀጣይም የታክስ ኦዲት ስራዉን ጥራቱን የጠበቀ ፍትሃዊና ተዓማኒ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ከሁሉም ቅ/ፅ/ቤቶች የተውጣጡ አመራሮችና የታክስ ኦዲት ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ምንጭ፦ የገቢዎች ሚኒስቴር