Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን። በምስጋና መጠለፍ ና ከንቱ ውዳሴ | ምክረ አበው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

በምስጋና መጠለፍ ና ከንቱ ውዳሴ

ምስጋና የ ባህርይ ገንዘቡ የሆነዉ ለ እግዚአብሔር ነው ።1ኛ ዜና 16፥25, መዝ 18፥3 መዝ 96፥4 ,2ኛ ሳሙ 22፥4 እኛ ሰዎች ደሞ ከ አፈር የተበጀን ፈጣሪ የሰራን ፍጥረቱ ነን በ እኛ ዘንድ የ ፈጣሪ ክብር እንዲገለጥ ይገባል። ለ ፈጣሪ ምስጋና ለማቅረብም አንደበት ተሰርቶልናል። መዝ 34፥1 "ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው።" እንዳለ ቅዱስ ዳዊት ።

ሆኖም ግን ለ ፈጣሪ የሚገባውን ምስጋና ለ ራስ ማድረግ መጣጣር በዘመናችን አገልጋዮች በስፋት ይታያል። በዘመናችን በብዙ አገልግሎቶች ስብከቱ፣ ዝማሬው ፣ ክህነቱ የራሳቸው እስከሚመስል አገልጋዮች ሲመፃደቁበት ማየት የተለመደ እየሆነ መጥትዋል ። በዚህ የተነሳ ለ ቤተክርስትያን እኛ እናውቅልሻለን የሚል አካል እየበዛ ፤ አገልጋዮች ከሚሰበከው ወንጌል በላይ ስለ ድምፅ ጥራት ና ስለ መድረክ አያያዝ ጉዳይ ሲጨነቁ ማየትም የተለመደ ነው።



አንድ መርከብ በ ውሃ የተሞላ ውቅያኖስ ላይ ሳይሰጥም መከሄድ ይችላል። መርከቡ መስመጥ የምትጀምረው በ ራስዋ ቀዳዳ ተከስቶ፤ በ ውሃ ከተሞላ ውቅያኖስ ውሃው ሰርስሮ የገባ ጊዜ ነው። አንድ አገልጋይም በሚያገልግልበት ጊዚያት የ ምስጋና ብዛት የ መቆለጳጰስ ጥግ ስለተነገረው ሳይሆን ፤ በ ልቡ ለ ምስጋናዎቹ ና አድናቆቶች ቦታ መስጠት ሲጀምር ነው በ ከንቱ ውዳሴ ተጠልፎ የሚወድቀው።

በርግጥ ምእመናን ናቸው አገልጋዮች በ ከንቱ ዉዳሴ እንዲወድቁ ፆር እየሆኑ ያሉት ። ታቦት ያላቸው ብዙ መካናት ትቶ አገልጋዮች ተከትሎ ሚዋትት ፤ እግዚአብሔር ሳይሆን አገልጋዮች የሚያመልክ ስለ ክርስቶስ ከመስበክ ይልቅ ላንቃዉ እስኪያመው ስለ መምህር እገሌ ዘማሪት እገሊት ሲኸራከር የሚውል ምእመን እንደ ፈሪሳውያኑ በ ነቀፋ የተሞላ ክርስትና የሚኖር ከሆነ ቆይትዋል። ምእመናን ለ እናታችን ሄዋን እንዳሳታት ዲያብሎስ ያለ የ ሽንገላ ቃላትም ለ አገልጋዮች ከ መናገር መከልከል ይገባናል።

ከመነኮሳት ታሪክ አንድ ታሪክ ለማስታወስ ያክል።

ከዘመናት በ አንዱ አንዲ ወጣኒ መነኩሴ በ መንፈሳዊ አገልግሎቱ የተነሳ በብዙ ምእመናን ዘንድ አድናቆትመንፈሳዊ ና ዉዳሴ ማግኘት ጀመረ በዚህም የተነሳ ደስ ብሎት ወደ አበመኔቱ ሄደና ስለ መንፈሳዊ አገልግሎቱ በብዙ ምእመናን መወደዱን አድናቆት ና ዉዳሴ ማግኘቱን ነገራቸው።
አበመኔቱ እንዲህ ብለው ምክር ሰጡት "ልጄ ሂድና ሙታንን ተሳደብ አሉት እንዳሉትም ወደ መቃብር ስፍራ ሄዶ ሙታንን ተሳደበ ። በ ሁለተኛው ም ቀን ሂደህ ሙታንን አመስግናቸው አሉት ፤እንዳሉትም ወደ መቃብር ስፍራ ሄዶ ሙታንን አመስግኖ ወደ አበመኔቱ ተመለሰ።አበመኔቱም ሙታን ስትሰድባቸው ሆነ ስታመሰግናቸው ምን አሉህ አሉት ። ወጣኒ መነኩሴዉም ምንም መልስ አልሰጡኝም አላቸው።አበመኔቱም ለ መነኩሴዉም ልጄ አንተም ልብህ ለ ሰዎች ምስጋና ና ለ ሰዎች ስድብ ክፍት አድርገህ ኑር አሉት።"ስለዚህ ኣእምሮህን ገዝተህ ምስጋና ለ መቀበል እንደምንደረደረው ሁሉ ስድብ የ መቀበልን ፀጋ ቢኖረን ከ ከንቱ ውዳሴ መራቅ እንችላለን። መፅሓፍ ቅዱስም እንዲህ ይለናል "ሰዎች ስለሰው ልጅ ሲጠሏችኹ ሲለይዋችኹም ሲነቅፏችኹም ስማችኹንም እንደ ክፉ
ሲያወጡ ብፁዓን ናችኹ እንሆ ሰርቶም በ ሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችኹ ዝለሉም አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።" ሉቃ 6፥ 22 -23 ስለዚህ ክርስትያን ቅን ሰርቶም ለሚመጣበት ዘለፋ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል።ከንቱ ዉዳሴ የተሞላን ከሆንን ግን እሄ ማድረግ ይከብደናል።

ለ አንድ ነገር በ ሃላፊነት ስሜት ኣድርጌዋለው ብሎ መናገር ከንቱ ውዳሴ መፈለግ አይደለም። ይልቁ ግን ስለ ችሎታህ ና ስለ ዓቅምህ ከሌሎች የ ምስጋና ችሮታ መጠበቅ ከንቱ ውዳሴ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ በ ቂሳርያ መንፈስቅዱስ የገለጠለትን የ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሲመሰክር በ ጌታ ዘንድ ሞጎስ አግኝትዋል ። በራሱ ፍቃድ ሲደገፍ የ ወንድሞቹ የ እነ ዮሃንስ ትጋት ግምት ውስጥ ሳያስገባ "ሁሉ ቢተዉህ እኔ እስከ መጨረሻ እከተልሃለው " የሚል ከንቱ ዉዳሴ ፈልጎ የተናገረዉ ንግግር ግን ያመጣው ውጤት መልካም አልነበረም። እኛም ስናገለግል ጌታ በ እኛ እንዲናገር ፈቅደን የ ወንድማችንን አገልግሎት አክብረን ሊሆን ይገባል። ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላቹ ወዮላችሁ"ሉቃ 6፥26 ብሎ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን በ ከንቱ ዉዳሴ ተጠልፈክ የሚደረግ እዩኝ እዩኝ ማለት የሚሰጠን በረከት ፤ የሚጨምርልን ፀጋ የለም።ስለዚህ ከ ውዳሴ ከንቱ የ ራቀ ቅን አገልግሎት እንድናገለግል ይገባል።

@ ሄኖክ ታደሰ ,መስከረም 19,2013 ዓ/ም ተፃፈ።