Get Mystery Box with random crypto!

ተወዳጆች ሆይ! አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ሁላችንም እናው | ምጥን ቅመም (Mitin Kimem)

ተወዳጆች ሆይ! አንድ እንግዳ ወደ ቤታችን ሲመጣ ቤታችንን እንደምን እንደምናሰናዳው ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ ሁላችንም እንግዳችንን ደስ የሚያሰኘው ነገር ለማድረግ የምንቻኰል አይደለንምን? ለእንግዳችን የሆነ ነገር ባናደርግለት፥ እንግዳችን በመምጣቱ ደስ ተሰኝተን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ባናደርግለት፥ ግን ደግሞ በመምጣቱ ደስ እንደተሰኘን ብንነግረው እንግዳችን በፍጹም አያምነንም፡፡ በእንግዳችን መምጣት ደስ እንደተሰኘን ከቃላት ባለፈ በገቢር መግለጥ አለብንና፡፡ እንኪያስ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወታችን ከመጣ ደስ መሰኘታችንን በገቢር ልንገልጽ ያስፈልጋል፡፡ እንግዳችን ክርስቶስን የሚያስቈጣ ነገር ልንፈጽም አይገባንም፡፡

እንግዳ ሲመጣ ቆሻሻ ልብስ አይለበስም፡፡ እንግዳ ሲመጣ የሚያስጸይፍ ነገር አይነገርም፡፡ ክርስቶስ በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ስንፈልግም ቆሻሻ ልብሳችንን (ማንነታችንን) አውልቀን ልንጥል ያስፈልጋል፤ አስጸያፊ ነገራችንን ልንተው ያስፈልጋል፡፡ እንግዳ ሲመጣ ቤት ያፈራው ሁሉ ይቀርብለታል፡፡ ክርስቶስ ወደ ቤታችን ሲመጣም የሚበላ ነገር ልናቀርብለት ይገባል፡፡ ለመሆኑ የክርስቶስ መብል ምንድነው? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጥያቄ ሲመልስልን እንዲህ ብሏል፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ዮሐ.፬፡፴፬፡፡

እንኪያስ ክርስቶስ የራበው ይኸው ነውና እንመግበው፤ ኢየሱስ የጠማው ይኸው ነውና እናጠጣው፡፡ እርሱም ይቀበለናል፡፡ አንዲት ኩባያ ቀዝቃዛ ውኃ ብንሰጠው እንኳ ይቀበለናል፡፡ ስለብዛቱ ሳይሆን ስለፍቅሩ ብሎ ይቀበለናል፡፡ እኛን ስለመውደዱ ይቀበለናል፡፡ የምንወደው ሰው የሰጠነውን የሚቀበለን ስለ መጠኑ አይደለም፤ ስጦታው የወዳጅ ስለሆነበት እንጂ፡፡ ሰው ወዳጁ ጌታም ሁለት ሳንቲም ብንሰጥ እንኳ ብዙ እንደሰጠን አድርጐ ይቀበለናል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታችንን የሚቀበለው ድሃ ስለሆነ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድሃውም የባለጸጋውም ስጦታ እኩል የሚቀበለው ስለ ልቡናችን ኀልዮት እንጂ ስለ ስጦታው ትልቅነት ወይም ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን እንደምንወደው ለመግለጽ የግድ ብዙ ወይም በውድ ዋጋ የተገዛን ስጦታ መስጠት አያስፈልገንም፡፡ ስጦታችን እርሱ ወደ እኛ ስለመጣ ደስ የመሰኘታችን መግለጫ ነውና ስለ ስጦታችን መጠን ልንመለከት አይገባም፡፡



"ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ"