Get Mystery Box with random crypto!

በተግባርህ አሸንፍ! ምርጫህ የማይመቸው፣ ውሳኔዎችህ የማያስደስተው፣ ተግባርህ የማያረካው መሃበረሰ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

በተግባርህ አሸንፍ!

ምርጫህ የማይመቸው፣ ውሳኔዎችህ የማያስደስተው፣ ተግባርህ የማያረካው መሃበረሰብ ውስጥ ካለህ ብዙ ምርጫ የለህም። ደጋፊ በማጣትህ ውሳኔህን ትጥላለህ ወይም ብቻህን ተጋፍጠህ ታልፈዋለህ። ተቃውሞህን ለማሸነፍ፣ ተቃርኖህን ጥሎ ለማለፍ ብዙ ተዓምር መስራት፣ ያልሆንከውን መሆን፣ ከአቅምህ በላይ መንጠራራተት፣ ለማሳመን መጣጣር አይጠበቅብህም። ተግባርህ ከበቂ በላይ ነው፤ ተጨባጩ ስራህ ሁሉንም ያስተካክላል፤ እራስህን ለእርሱ አሳልፈህ መስጠትህ ከባዱን ሁኔታ ያሻግርሃል። ማድረግ እንደማውራት ቀላል እንደማይሆን ታውቀዋለህ። ለማድረግ ስትነሳ እንደምትጨርሰው ውስጥህ ማመን ይኖርበታል፤ መሰናክሎችህን እንደምትሻገር ማመን ይጠበቅብሃል።

አዎ! ጀግናዬ..! በተግባርህ አሸንፍ! አዲስ ተግባር፣ አዲስ ማንነት፣ የተለየ አካሔድ፣ የተለየ ስራ እጅግ በጣም ብዙ ፈተና ይኖረዋል። ቤተሰብ አይረዳህም፤ መሃበረሰቡ ቶሎ አይቀበልህም፤ ውጤቱን ቶሎ አትመለከትም፤ ተቃዋሚህ ይበዛል፤ የሚተችህ እልፍ ነው፤ ችግርህን የሚቆጥርልህ ከዙሪያህ አይጠፋም፤ ውስጥህ ቢታገልም ውጪ በሚመለከተው ነገር ብዙ ይፈተናል። ከዚህ ሁሉ ተቃሞና ፈተና በስተጀርባ በእራስመተማመን የተባለውን ወሳኝ ነገር ያታግልሃል። እንደምትችለው ብታውቅም የሚወራብህን እየሰማህ፣ የሚሰጥህን አስተያየት እየተቀበልክ፣ የጠቆረብህን ፊት እየተመለከትክ፣ የሚያሽሟጥጡብህ ላይ እያተኮርክ ለመውደቅ ትንገዳገዳለህ፤ ለማቆም ታማትራለህ፤ ተስፋ ለመቁረጥ ትሰናዳለህ። ከውስጣዊ መሻትህ በላይ ውጫዊው ምላሽና ገፅታህ እራስህን እንድትጠራጠር ያደርጉሃል።

አዎ! ተግባርህ ግን ለሁሉም ምላሽ አለው፤ ስራህ ግን ለሁሉም መልስ ይጠሳል፤ የማያቋርጠው ጥረትህ የተቃዋሚህን አፍ ያዘጋል፤ ውጤትህ ውጫዊ ተቃርኖህን ያርቀዋል። ጠንክረህ የምትሰራው አንድም ህልምህን እውን ለማድረግ ሲሆን ሌላም ተቃውሞህን ለማስታገስ ነው። ማንም በተቃራኒህ ቢቆም፣ ማንም መንገድህን ቢዘጋብህ ከእርሱ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ መግባት አይጠበቅብህም፤ እርሱን ለማሳመን ላይ ታች ማለት አይኖርብህም። በጀመርከው መንገድ መቀጠል፣ ለህልምህ መታገል፣ ለአላማህ መወገን፣ ራዕይህን ማስኬድ፣ ወደፊት ብቻ መመልከት፣ አሰናካዮችህን ማስወገድ ብቻ በቂ ነው። "አትችልም" ብትባል ቆመህ መቻልህን በቃላት ስብጥር፣ በአርፍተ ነገሮች ህብረት አታስረዳም። ችሎታህን የሚያሳየው ሁነኛው መንገድህ ተግባርህና ተግባርህ ብቻ ነው። በተግባርህ አሸንፍ፤ ተቃውሞህን በውጤትህ ቀልብስ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q