Get Mystery Box with random crypto!

ለእራስሽ ድረሺላት! ለሚያይሽ ሁሉ የደላሽ፣ የተመቸሽ፣ ህይወት አልጋ በአልጋ የሆነልሽ ትመስያለሽ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ለእራስሽ ድረሺላት!

ለሚያይሽ ሁሉ የደላሽ፣ የተመቸሽ፣ ህይወት አልጋ በአልጋ የሆነልሽ ትመስያለሽ፤ ነገር ግን ውስጥሽን አንቺ ታውቂያለሽ፤ ህመምሽን፣ የልብ ስብራትሽን፣ ቁስልሽን አንቺ ትረጂዋለሽ። ፊትሽ ፈክቶ፣ ጥርስሽ ስቆ፣ ገፅሽ አብርቶ ህመምሽን ባያክም፣ ቁስልሽን ባያደርቅ፣ ብሶትሽን ባያስተነፍስ ምን ዋጋ አለው። ሰው ባየሽ ሊያውቅሽ ይሞክራል ነገር ግን በፍፁም ሊያውቅሽ አይችልም፤ በንግግርሽ ሊገልፅሽ ይጥራል ነገር ግን በፍፁም ንግግርሽ ውስጥሽን አይወክልም። አንዳንዴ ድብብቆሽም ይደክማል። ለማን ብለሽ፣ ምን እንዳይመጣ ብለሽ በውስጥ እያረርሽ በውጭ እንደምትስቂ አታውቂውም። በብዙ ሰዎች ተከበሻል ነገር ግን ማንም ህመምሽን ሊረዳሽ አልሞከረም፤ ጊዜ ሰጥቶ አላዳመጠሽም፤ ትኩረት ሰጥቶ አልተከታተለሽም። እንዲሁ እንደሚያይሽ የደላሽ ትመስይዋለሽ፤ የሰው ልጅ ከበላ ከጠጣና ለብሶ ካማረበት ማንም ችግር አለበት እርዳታ ያስፈልገዋል ብሎ አያስብም።

አዎ! ጀግኒት..! ለእራስሽ ድረሺላት፤ እራስሽን አድኚ። ሁለት ሰው ሆነሽ፣ ሁለት ገፅ ኖሮሽ ከእራስሽ በቀር ማንም እንደማያድንሽ እወቂ። ሰዎች ሃሳብ ሊሰጡሽ ይችላሉ፤ ሊመክሩሽ ይችላሉ ነገር ግን በፍፁም ህመምሽን አይታመሙልሽም፤ ስቃይሽን አይሰቃዩልሽም። ብቻሽን እንደሆንሽ እያሰብሽ እራስሽ ላይ አትጨከኚ፤ በገዛ ፍቃድሽ እራስሽ ላይ የህይወትን ክብደት አትጨምሪ። ከአምላክሽ ቀጥሎ ለእራስሽ ያለሽው አንቺ እንደሆንሽ እወቂ። ዘወትር ብቻዋን ስትሆን ቁስሏ የሚቀሰቀስባት፣ ህመሟ የሚያገረሽባት፣ በማስመሰል አለም የምትሰቃየዋ ምስኪን ሴት አታሳዝንሽም? እርሷስ ብትሆን ካንቺ በቀር ማን አላት? ማን ደርሶ ከስቃይዋ እንዲገላግላት ትጠብቂያለሽ? ጊዜ አትፍጂ፣ የህመም፣ የስቃይ ወቅትሽን አታስረዝሚ። እራስሽ ላይ በመጨከን፣ ህይወትሽን ይበልጥ በማወሳሰብ ምንም አታገኚም። ለእራስሽ ብለሽ ህመምሽን ተንፍሺ፣ ለእራስሽ ብለሽ ፍረሃትሽን ተጋፈጪው፤ ለእራስሽ ብለሽ ከአስጨናቂ ሃሳቦችሽ ፋታ ውሰጂ።

አዎ! ጀግናዬ..! ብዙ ሸክም አለብህ፤ ቀላል የሚመስሉ ነገሮች ፋታ ነስተውሃል፤ የህይወት ፈተና ተወሳስቦ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶሃል። ገፅህና ውስጥህ እጅጉን ተራርቀዋል። የቤተሰብ ጉዳይ፣ የትምህርት፣ የግንኙነት፣ የስራ፣ የገንዘብ ችግር ተደራርበው ስለእራስህ እንኳን እንዳታስብ አድርገውሃል። አንደ ነገር ግን አስታውስ ሁሉም አሳሳቢና አስጨናቂ ነገር የሚመጣው ካንተ ቦሃላ ነው፤ ያንተ ህልውና ከምንም ነገር በላይ ነው፤ ቀዳሚም ነው። እራስህን ተደብቀህ አትችለውም፤ ለእራስህ እያስመሰልክ አታመልጠውም። ለውስጥ ህመምህ እረፍት ካልሰጠህ፣ ቁስልህን ካላከምከው የህይወትህ ጨለማነት እንዲሁ እንደቀጠለ ነው። ብዙ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ውስጥ ነህና አትረበሽ፤ የገጠመህ ጉዳይ መፍተሔ አለውና በእራስህ ተስፋ አትቁረጥ፤ የሃዘንህ መቋጫ ቅርብ ነውና ቀና በል። ያንተን ጉዳይ ጉዳዬ ብለው ሊያነሱህ የሚመጡ ባይኖሩም አንተ ለእራስህ ድረስለት፤ ካቀረቀረበት አንገቱን ቀና አድርገው፤ ሲፈራው የነበረውን ነገር ተጋፈጥለት፤ የውስጥ ብሶቱን አውጣለት፤ ተንፍስለት።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q