Get Mystery Box with random crypto!

ማን አቆመህ? መሔድ እስከምትችለው እንዳትሔድ፣ መድረስ ያለብህ ስፍራ እንዳትደርስ፣ ማግኘት ያለብ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ማን አቆመህ?

መሔድ እስከምትችለው እንዳትሔድ፣ መድረስ ያለብህ ስፍራ እንዳትደርስ፣ ማግኘት ያለብህን እንዳታገኝ፣ ማትረፍ ያለብህን እንዳታተረፍ፣ የሚገባህን እንዳይኖርህ ማን አገደህ? ማንስ አቆመህ? ጀምሮ በመተው ልማድ ታስረህ፣ ሞክሮ በማቆም አዙሪት ውስጥ ገብተህ፣ ሁሉን የመነካካት እንጂ የመጨረስን መልካም ተግባር ወደኋላ ብለህ ከመንገድህ ለመሰናከልህ ሰዎችን፣ ሁኔታዎችን፣ አሰራርን፣ መንግስትን ብትወቅስ ምንም ዋጋ የለውም። ምክንያት የማትደረድር ከሆነ እውነታውን ጠንቅቀህ ታውቀዋለህ። ስለራስህ ጀብደኝነት ለማውራት እንደምትጣደፈው ድክመትህንም ለእራስህ ከማስረዳት ወደኋላ አትበል። የምታውቀው ማንነትህ ወዳጅህ እንጂ ባዳህ አይደለም፤ የሚረዳህ እንጂ የሚገፋህ አይደለም፤ የሚያውቅህ እንጂ ያልተገለጥክለት አይደለህም።

አዎ! ጀግናዬ..! ማን አቆመህ? ማን እንደነበርክ፣ በነበርክበት አስቀረህ? ማን ለውጥን እንደማትፈልግ፣ እንድገትን እንደምትጠየፍ፣ ከፍታን እንደምትጠላ ሊያሳምንህ ሞከረ? በአለም ዙሪያ የሚናፈሰው ተስፋቢስ ዜና ነውን? ሀገርን የወረረው አሉታዊ ትርክት ነውን? በየጊዜው የሚቀያየረው ጊዜያው ጉዳይ ነውን? አወኩት ባልከው ማግስት የሚለወጥብህ ሰው ነውን? ካንተ የማያልፈው ጊዜያዊ ምቾትህ ነውን? ባለህበት ለመቆምህ፣ በአንድ ቦታ፣ በተመሳሳይ አዙሪት ለመዋጥህ ብዙ ምክንያቶች ልትጠቅስ ትችላለህ። ነገር ግን አሁንም እዛው ባለህበት ቆመህ መቅረትን ካልፈለክ ዋንኛው ምክንያትህ አንተ እራስህ እንደሆንክ ማመን ይኖርብሃል። ለሰው ሲሆን ብዙ ምክንያት ልትደረድር ትችላለህ ለእራስህ ግን የምታውቀውን አንተው ታውቀዋለህ።

አዎ! አንዳንዴ በሆድ የሚያዙ፣ ከእራስ የማይወጡ፣ ለእራስ ብቻ እንደ ሚስጥር የሚያዙ እውነታዎች ይኖራሉ። አውጥተህ ብትናገራቸው መጠቋቆሚያ ያደርጉሃል፤ የሚሰጥህን ግምት ያሳንሱታል፤ ለትቺትና ዘለፋ ያጋልጡሃል። ስለዚህ ስለእራስህ የምታውቀው እውነታ ቢኖርም የሆድህን በሆድህ ይዘህ ሰዎች የሚታያቸውን ምክንያት ትደረድርላቸዋለህ። የምታውቀውን እውነት ተቀበል፤ ስለእራስህ የሚሰማህን ስሜት አዳምጥ፤ ባለህበት ለመክረምህ፣ በቀድሞው ስፍራ ለመሰንበትህ ከእራስህ በላይ ተጠያቂ እንደሌለ እመን። የውጪውን እንቅስቃሴ ተውና እራስህ ላይ መስራት ጀምር፤ አንድ እርምጃም ቢሆን ፈቀቅ በል፤ ለአዲስ ከባቢ፣ ለተለየ ምህዳር እራስህን አዘጋጅ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q