Get Mystery Box with random crypto!

ከባጣ-ቆየኝ ተጠበቅ! ባጣ-ቆየኝ የተባሉ ሰዎች ሲኖርህ ወዳጆችህ ናቸው፤ ስታጣ፣ አንዳች ነገር ሲ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ከባጣ-ቆየኝ ተጠበቅ!

ባጣ-ቆየኝ የተባሉ ሰዎች ሲኖርህ ወዳጆችህ ናቸው፤ ስታጣ፣ አንዳች ነገር ሲጎድልህ ደግሞ ምንም የሌለህ፣ ምንም የማትጠቅማቸው ከንቱ ሰው ነህ። እያንዳንዱ ተግባርህ እነርሱን ከመጥቀም ጋር መገናኘት አለበት። ምንም ካላገኙብህ፣ ምንም ካልጠቀምካቸው አንተ ለእነርሱ ምንም ነህ። በተዓምር ትዝም አትላቸውም። ሩጫቸው የእራሳቸውን ሆድ ለመሙላትና ጠግቦ ለማደር እንጂ ያንተ መራብና በችግር መሰቃየት ምናቸውም አይደለም። የእነርሱ ሙቀት ማግኘት እንጂ ያንተ በብርድ መጠበስ ጉዳያቸው አይደለም። ስታገኝ እንድታካፍላቸው ሲያገኙ ደግሞ እንድትርቃቸው ይፈልጋሉ። ከሌላው ሰው በጣም የተለዩ እንደሆኑ ስለሚያስቡ ካንተ እኩል እራሳቸውን መመልከትን እንደ ውርደት ይመለከቱታል። ተጠቃሚ እስከሆኑ ድረስ አብረውህ ናቸው ካልጠቀምካቸው ግን በነጋታው ጥለውህ ለመሔድ በፍፁም አያንገራግሩም። የቀድሞ ውለታህ፣ ያደረክላቸው መልካም ነገር፣ በጎነትህ ዛሬ እስካልሆነ ድረስ ከመሔድ ልታስቆማቸው አትችልም።

አዎ! ጀግናዬ..! ከባጣ-ቆየኝ ተጠበቅ! እንደ አማራጭ ከሚመለከቱህ፣ እንደማያዛልቁህ ከተረዳሃቸው፣ የዘወትር ፍላጎታቸው እራሳቸውን ብቻ መጥቀም ከሆነ፣ ከእራስ ወዳድነት ባህሪ የገዘፈ የእራስ አምላኪነት አባዜ ካላቸው፣ ሁሌ ስህተት እንደማይሰሩ፣ ጥፋታቸው ሁሉ ቅዱስ እንደሚያደርጋቸው ከሚያስቡ፣ ህይወታቸውን በሙሉ ስለእራሳቸው ምቾትና መደላደል ብቻ ሲጨነቁ ከሚኖሩ ሰዎች እራስህን ጠብቅ። እነርሱ ጋር የሰውነትህ ልኬት በምታደርግላቸው ተግባር እንጂ በማንነትህ አይደለም። አብረሃቸው ብትሖን መሔጃ እንዳጣህና ያለህ አማራጭ ከእነርሱ መጠጋት ብቻ እንደሆነ ስለሚያስቡ እንደፈለጉ ሊያደርጉህና ሊጫወቱብህ ይሞክራሉ። ከእራስ አምላኪዎች ጋር ስትሆን አንተ መጠቀሚያ እቃ እንጂ ሰው አትመስላቸውም፤ ነገ አውጥተው እንደማይጥሉህ እርግጠኛ መሆን አትችልም።

አዎ! ከእራሳቸውን አምላኪዎች (Narcissist) ሰዎች እራስህን ልትጠብቅ የምትችልበት አዋጭ መንገድ ሳትቀደም በመቅደም ብቻ ነው። እንደ ሸንኮራ አኝከው፣ ጠዓምህን ጨርሰው ከመትፋታቸው በፊት አንተ ቀድመህ ከህይወትህ ውስጥ ትፋቸው፤ ከህይወትህ ጠራርገህ አስወጣቸው። ከእነርሱ ለመለየት ከበቂ በላይ ምክንያት እንዳለህ አስታውስ። እነርሱ ባሉበት የበታችነት እየተሰማህ፣ እየተሳቀክ፣ ሁሌም ስህተት የምትሰራው አንተ እንደሆንክ እያሰብክ፣ ካንተ በላይ ባንተ የሚደረገው ጥቅም ዋጋ እንዳለው እየተመለከትክ፣ አብሮ ከመኖር ይልቅ በአኗኗሪነት መቆጠር የእነዚህን ሰዎች ቅርንጫፍ ከእራስህ ግንድ ላይ ቆርጦ ለመጣል እጅግ በጣም በቂ ምክንያቶች ናቸው። የሰውነት ዋጋህን ከፍ ለማድረግ እራስ አምላኪ (Narcissist) መሆን ሳይሆን እራስ አምላኪዎችን፣ ባጣ-ቆየኞችን ከህይወትህ ማስወጣት በቂ እንደሆነ አስተውል።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q