Get Mystery Box with random crypto!

አንቀሳቃሹ አንተ ነህ! ምንም ያክል ሰዎች ቢያምኑብህ፣ ቢተማመኑብህ፣ ወደፊት ቢገፉህና ቢደግፉህ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

አንቀሳቃሹ አንተ ነህ!

ምንም ያክል ሰዎች ቢያምኑብህ፣ ቢተማመኑብህ፣ ወደፊት ቢገፉህና ቢደግፉህ በእራስህ ካልተማመንክና እራስህን የማታበረታ ከሆነ ምንም ማምጣት አትችልም። እሳቱ ያለው አንተ ውስጥ ነው፤ ነበልባሉ የሚወጣው ካንተ ነው፤ የማያቋርጠው ልባዊ መሻት መነሻው አንተ ነህ። ሰዎች የሚያበረቱህ ሲያገኙህ ነው፤ አንተ ግን ሁሌም ከእራስህ ጋር ነህና የውስጥ ጩሀትህንና በእራስህ ላይ ያለህን ጥርጣሬ ባዳመጥክ ቁጥር ሚዛንህን ለመሳት የፈጠንክ፣ በእራስህ ለማዘን የምትቸኩል ትሆናለህ። ሞተሩ አንተ ሆነህ ምናልባትም ለመግፋት የተወሰነ ሃይል የሚጨምሩልህ ሌሎቹ ሊሆኑ ይችላሉ። በእራስህ ካመንክ፣ ሃሳብህን ምድር ላይ አውርደህ መመልከት ከቻልክ፣ ህልምህ እውን እንደሚሆን ካመንክ፣ እያንዳንዷን ጥረትህን ዋጋ ከሰጠሃት ያምታስበውን አይነት ህይወት የማትኖርበት ምንም ምክንያት አይኖርም። በማይታይ ሃሳብ የሚታይ ውጤት እንደምታመጣ አትጠራጠር።

አዎ! ጀግናዬ..! አንቀሳቃሹ አንተ ነህ! ጀማሪውም፣ አድራጊውም፣ ፈፃሚውም አንተው እራስህ ነህ። የምኑ? የራዕይህ፣ የግብህ፣ የአላማህ፣ የህልምህ። ደጋፊ ሊኖርህ ይችላል፣ ተከታይ ልታፈራ ትችላለህ፣ አድናቂዎችህ ሊበዙ ይችላሉ። አንዴ ጥፋት ብታጠፋ ወይም ብትሳሳት ግን እነዛ አብረውህ የነበሩና ሲደግፉህ፣ ሲያጨበጭቡልህ የነበሩ ሰዎች በሰዓቱ አብረውህ ስለመሆናቸው ምንም ዋስትና የለህም። መስሎህ እንጂ ዋናው ነገር የሰዎች ተቀባይነት ሳይሆን የእራስህ ተቀባይነትና በእራስመተማመን ነው። ተቀባይነትን ለማግኘት የደከምክበት ጊዜ፣ ደጋፊ በማጣትህ ያዘንክበት ወቅት፣ በሰዎች የወረደ ንግግር በእራስህ ያፈርክበት ሰዓት የሚቆጭህ ጊዜ ይመጣል። ቀና ባልክ ቁጥር የምታያቸው ሰዎች ይቀያየራሉ፤ አንተ የምታየውና የምትሰራው ግን ያው ነህ።

አዎ! በእርግጥ የህይወት አላማህን የምትኖር በምድር ላይ ነው ነገር ግን ያንተ ሃሳብ እንዲሳካና አላማህ ምድር ላይ እንዲወርድ የአለም ሰው ሁሉ ሊደግፍህና ሊያምንብህ አይገባም። ከምንም በላይ እራስህንም ሆነ ሰዎችን እንዲያምኑብህ የሚያደርጋቸው ስራህና ስራህ ነው። ሃሳብህን አድርጎ ለመገኘት በእራስህ መተማመን ይጠበቅብሃል፤ በእራስህ ለመተማመንም አድርጎ መገኘት ይኖርብሃል። ከጎንህ የሚቆም ሰው ባይኖር እንኳን እራስህን ደግፈህ ቁም፤ ብዙዎች ቢቃወሙህም በምታምንበት አቋምህ ፅና። በጉጉት የምትጠብቀውና ተስፋ ያደረከው የሰዎች ድጋፍ ያላንተ ብርታትና ጥንካሬ ምንም እንደማያመጣ እወቅ። አንተ ባላመንክበትና ምንም ስሜት በማይሰጥህ ነገር ላይ ብዙዎች ቢደግፉህና ቢያበረታቱህ እንኳን ከድካም ውጪ ትርፍ አታገኝም። ከልብህ በእራስህ እመን፤ ያመንክበትን ከማድረግ አትቦዝን፤ ከማንም በላይ ለእራስህ ታምነህ ተገኝ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q