Get Mystery Box with random crypto!

ያለህበት ላይ አተኩር! ሁሉንም ደረጃ ለመውጣት እያንዳንዱን መመልከት አይጠበቅብህም ። ጀማሬ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ያለህበት ላይ አተኩር!

ሁሉንም ደረጃ ለመውጣት እያንዳንዱን መመልከት አይጠበቅብህም ። ጀማሬው ላይ ከሆንክ ሙሉ ትኩረትህን ጅማሬው ላይ አድርግ ፤ መሐል ከደረስክም እንዲሁ ትኩረትህን መሐል ላይ አድርግ ። ስላለህበት ደረጃ በቂ እውቀት ካለህ ስለመጪው ባለማወቅህ አትጨነቅ ። ብርታትህ የዛሬ እርምጃህ እንጂ የወደፊትህ አይደለም ፤ አሁን ያለህበትን ሁኔታ ሳታልፍ ፣ የደረሰብህን መከራ ሳትወጣ ገና ያልተከሰተው ጋር መድረስ አትችልም ። ሁሉም ነገር የየራሱ ቅድመተከተል አለው ፤ የእራሱ ደረጃ አለው ፤ ውጣውረድ አለው ። መደበኛ ትምህርትህን በአግባቡ ሳታጠናቅቅ ለየትኛውም ክፍተኛ መዓረግ ልትበቃ አትችልም ። ደረጃ አንድን ሳትሻገር እንዴትም ደረጃ ሁለት ጋር አትደርስም ። የፊደል ገበታ እንኳን የእራሱ ቅድመተከተል አለው ።

አዎ! ጀግናዬ..! ያለህበት ላይ አተኩር! ስለቆምክበት አስብ ፤ ሰለደረስክበት በሚገባ እወቅ ፤ ያለህበትን ጠንቅቀህ ተረዳ ። ያለፈው አልፏል መጪውም በጊዜው ይመጣል ። ወደፊት የሚሆንን ነገር ልታውቅ ትችላለህ እውቀትህ ግን የዛሬውን ደረጃ ሳትሻገር እንድታልፍ አያደርግህም። ነገን በመደገፍ የዛሬው ድጋፍህን እንዳትጥል ። ነገሮች ተያያዦች ናቸው ፤ ከፍታው ጋር ለመድረስ በዝቅታው ውስጥ ማለፍ ይኖርብሃል ። ምንምእንኳን በስተመጨረሻ እንደሚሳካ ብታውቅም ከእርሱ በፊት የሚቀድመውን ግን የመፈፀም ግዴታ አለብህ ። ብርቱ ብርታቱ የሚለካው በአንድ ደረጃ ሳይሆን እንደየሁኔታው በሚሻገራቸው ከባድና ቀላል ውጣውረዶች ነው ። ዛሬ ባለህበት ስራ አትለካም ፤ በዛሬው ገቢህ አትመዘንም ነገር ግን ለተሻለው ስራ ለመብቃትና ከዛሬ የላቀ ገቢ ለማግኘት ለጊዜውም ቢሆን በዚህ መንገድ ማለፍ ይጠበቅብሃል ።

አዎ! ጊዜያዊ ሃላፊነትን መወጣት ለትልቅ ደረጃ ያበቃል ፤ አስፈላጊ የተባሉ ደረጃዎችን እየተሻገሩ መጓዝ ብቃትን ይጨምራል ፤ በሒደት ውስጥ ማለፍ የተሻለ ማንነትን ይገነባል ። ዛሬ አንድ ያልከው ትንሽ እርምጃህ ሲደጋገም ውጤቱ እያማረ ይመጣል ። ዋናው ጉዳይ የቀጣዩ እርምጃህ ክብደትና ቅለት ሳይሆን የዛሬው እርምጃህ በአግባቡ መታለፍ ነው ። ከመዳረሻህ የሚያደርስህ በጥቂት የጀመረው እንቅስቃሴህና ያልተቋረጠው ጥረትህ ነው ። በየትኛውም የህይወት ጉዞ ምናልባትም ልታውቅ የምትችለው በመሃል ያለውን ውጣውረድ ሳይሆን ያለህበትን ሁኔታ ነው ፤ እንዲሁም በጥቂቱ መጪውን ብትገምት ነው ፤ መሃሉ ግን ላንተም ሆነ ለተመልካች አይነገርም ፤ ግልፅም አይደለም ። መጪውን ትተህ በጊዜው የሚጠበቅብህን በአግባቡ ተወጣ ። ትኩረትህ የማያሳድገው ነገር የለምና ያለህበት ላይ በማተኮር በቅድሚያ እርሱን አሳድግ ፤ እርሱን ተሻገር ፤ በእርሱ መንገድ ያሰብከውን እውን አድርግ ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q