Get Mystery Box with random crypto!

ሰበብ ባይኖርስ? አዎ! በሔድንበት ሁሉ ድክመታችን እንዳይታወቅ ፣ ስንፍናችንን ላለማመን ፣ | ምርጥ ጽሑፎች✍️✍️

ሰበብ ባይኖርስ?

አዎ! በሔድንበት ሁሉ ድክመታችን እንዳይታወቅ ፣ ስንፍናችንን ላለማመን ፣ መጥፎ ስሜታችንን አለባብሶ ለማለፍ የማናቀርበው ምክንያት ፣ የማንደረድረው ሰበብ የለም ። ሃላፊነት መውሰድ ፣ ለእራስ ጥፋት ተጠያቂ መሆን የሚባለውን ነገር አብዝተን እንሸሸዋለን ። ተጠያቂነትን ፍራቻ ሁሌም ምክንያት የምትደረድር ከሆነ የትም እንደማትደርስ እወቅ ፤ ሰበብ እያበዛህ አንድ እርምጃ እደማትጓዝ ተገንዘብ ። የስሜቱ ባሪያና በሰበብ አስባቡ የተገዛ ሰው አንድም የእራሴ የሚለው ታማኝ ማንነት የለውም ፣ ሌላም በሰው ፊት ድፍረትና በእራስ መተማመን አይኖረውም ። በሚያሳዝን ሁኔታ የሚያቀርበው ምክንያት እንኳን ሌሎችን ይቅርና እራሱንም የሚያሳምን አይደለም ። ለገዛ እራሱ የሰጠው ግምትና የበታችነት ወደ ውድቀትና ተስፋ ቢስነት ያንደረድረዋል ። እላይ ታች ብለህ እራስህን ማዳን በሚገባህ ጊዜ ምክንያት በመደርደር የተጠመድክ እንደሆነ ከእራስህ በላይ ለእራስህ ጠላት አይኖርህም ።

አዎ! ጀግናዬ..! ሰበብ ባይኖርስ ? ምክንያት መደርደር ባይቻልስ ? ለጥፋቱም ሆነ ለልማቱ ሃላፊነት አለመውሰድ ባይቻልስ ? የት በደረስክ ነበር ? የህይወትህ መልክ ፣ ገፅታው ፣ ማንነቱ ምን ይመስል ነበር ? አንተስ ምን አይነት ሰው ትሆን ነበር ? ሰበብ በእርግጥም አለ ነገር ግን በመኖሩ የሚጨምርልን ነገር ከሌለ ፣ ወደፊት ለመጓዝ ካላገዘን ፣ እንድንጠነክር ካላደረገን ፣ ካላበረታን ምንድነው ነጥቡ ? ቆዳን ማልፋት ቢያደክምም በመጨረሻ ውጤት ያመጣል ፤ ሰበብ ማብዛቱ ፣ ምክንያት መደርደሩ ፣ ሁኔታዎችን ማገለባበጡ ግን እራስን ከማታለል ፣ የእራስን ዋጋ ከማሳነስ ፣ ክብርን ዝቅ ከማድረግ ውጪ የሚያመጣልን ነገር የለም ።

አዎ! ያሰብከውን ላለማድረግህ ቆጥረህ የማትጨርሳቸው በቂ ምክንያቶች ይኖሩሃል ፤ ብታደርገውም ለማድረግህ እጅግ ብዙ በቂና ከዛ በላይ ምክንያቶች ይኖሩሃል ። ለሁለቱም ሚዛን የሚደፉ ምክንያት ቢኖርህም ሚዛኑ ግን አንተ ነህ ፤ እራስህ ላይ የምትወስነው ፣ አዋጩን የምትመርጠው ፣ ጠቃሚውን የምታደርገው አንተ ነህ ። የምክንያት ለውጥ አድርግ ፤ ላለማድረግ የምትደረድረውን ምክንያት ማድረግ በሚያስችሉህ ጠንካራ ምክንያቶች ተካቸው ፤ በእነርሱ ለውጣቸው ። ላለህበት ሁኔታ ያደረሱህ ነገሮች በተናጥል ሳይሆን በጋራ ለዚህ አብቅተውሃል ። አዎንታዊ ምክንያቶችህም ብቻቸውን ሳይሆን ከቆራጥነትህ ጋር ፣ ውሳኔህን በማካተት ፣ በህይወት አላማህ በመደገፍ ተዓምራዊውን ህይወት ወዳንተ ያመጣሉ ። ሰበቦችህን አሸጋሽግ ፤ ምክንያቶችህን አቀያይር ። አሉታዊዎቹን አስቀር ፣ በአዎንታዊዎቹ ተመራ ፤ ብርታቶችህን ምረጥ ጥንካሬህን አስቀድም ፤ ያሰብከውን ትልቅ ነገር አድርገህ ተገኝ ።
═════════❁✿❁ ═════════
ሶሻል ሚዲያ ያገኘነውን እውቀት ለሌላውም የምናደርስበት የመረጃ ቋጥ ነውና ይህን ጹሁፍ ካነበባችሁት በኋላ ለሌላውም እንዲደርስ #ሼር ማድረጋችሁን አትርሱ!!! የቴሌግራም ቻናላችንን ግቡና Join አድርጉ ።
https://t.me/joinchat/AAAAAFAtO5kL7-YczXxg_Q