2022-06-19 12:04:16
ሰኔ 12 የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል! እንኳን አደረሳችሁ!
የቅድስት አፎሚያ እና የቅዱስ ላሊበላ እረፍት ነው!
በቀሲስ መ/ር ሄኖክ ወ/ማርያም
ሰኔ 12 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ደገኛዋን ቅድስት አፎሚያን ከሰይጣን ተንኮል
የታደገበት ዕለት እንደሆነ ድርሳኑ መዝግቦልናል፡፡
ቅድስት አፎሚያ አስተራኒቆስ የተባለ ደግ ባል ነበራት፡፡ ይህ ሰው ሊሞት ሲል
የቅዱስ ሚካኤልን ስዕል አዘጋጅቶ በመስጠት፤በየወሩ በቅዱስ ሚካኤል ቀን
ለድሆች፣ለጦም አዳሪዎች ምጽዋት እንድትሰጥ፤መስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ
ፈጣሪዋ አጥብቃ ከመጸለይ እንዳታቋርጥ ነግሯት ያርፋል፡፡
ቅድስት አፎሚያም ይሄንን ርህራሄና ሰብአዊነት የተመላበት በጎ ሥራ አጥብቃ
መስራት ጀመረች፡፡ የበጎ ነገር ጠላት የሆነው ሰይጣን የቸርነት ሥራዋን
ተመልክቶ ወደ ቅድስት አፎሚያ መጣ፡፡ አዛኝ በመምሰልም ‹‹ለምን ገንዘብሽን
ታባክኛለሽ፤ይልቁንስ ገንዘብሽ ከማለቁ በፊት ባል አግብተሽ አትኖሪም ባልሽ
እንደሆነ ጸድቋል ምጽዋት አያስፈልገውም›› አላት፡፡
ሰይጣን የአስተራኖቆስን መጽደቅ የተናገረው አፎሚያን ለማስደሰት ሳይሆን እንደ
አዳምና ሔዋን ለማሳት ነው፡፡ ዘፍ 3÷1-8
ቅድስት አፎሚያም ‹‹ሌላ ባል ላላገባ ከፈጣሪዬ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ››
አለችው፡፡ ሰይጣንም የሚያስትበት የጥፋትና የተንኮል መንገድ ብዙ ነውና
መነኩሴ በመምሰል ብዙ ቢዘበዝባትም አፎምያ ግን ለሥጋዊ ምክሩ ቦታ
ሳትሰጠው እንቢኝ አለችው፡፡
ሰይጣንም በዚህ ሳያበቃ ያስትልኛል፣አፎሚያን ያሳምንልኛል ያለውን ሐሳብ
እያመጣ ቢነግራትም በእንቢታዋ ጸናች፡፡ ለሰይጣን ውሸት የየዕለት ሥራው
ስለሆነ ይባስ ብሎ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ ብሎ እርፍ አለው፡፡ ሰይጣን በአምሳለ
መልአክ ሰውን እንደሚያስት ያወቀው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰይጣን ራሱን የብርሃንን
መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣል›› ብሎ ነግሮናል፡፡ 2ኛ ቆሮ 11÷14
ስለዚህ አፎምያ በቅዱስ ሚካኤል ተመስሎ ቢነግራትም አልቀበልም አለችው፡፡
ወዳጆቼ እስቲ እራሳችንን እናስብ ስለ እውነት እኛ ብንሆን ይህንን ፈተና እናልፍ
ነበር? ይህ የአፎሚያን የእምነት ጥበብ የሚያሳይ ነው፡፡
ሰይጣንም አሉኝ የሚለውን ሰይጣናዊ ማሳመኛ ጥበብ ተጠቀመ፡፡ አፎሚያም
ምንም ይበል ምንም አለተቀበለችውም፡፡ ምክንያቷ ደግሞ ንግግሩና ገጽታው
ስላልተካከለ፡፡
በአፎምያ መንፈሳዊ ቆራጥነት የተበሳጨው ሰይጣንም ዓይኑን አፍጥጦ፣ጥርሱን
አግጥጦ አንቆ ሊገላት ሲል ቅዱስ ሚካኤል ብርሃናዊ ክንፉን እያማታ በቅጽበት
ደረሰላት ከሰይጣንም እጅ አዳናት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም ስለ እረፍቷ ‹‹ብጽዕት
አፎሚያ ሆይ ሄደሽ የቤትሽን ሥራ አዘጋጂ፣ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት
ትለያለሽ፣እነሆ እግዚአብሔር ዓይን ያላየውን፣ጆሮም ያልሰማውን፣በሰው ልብ
ያልታሰበውን አዘጋጅቶልሻል›› ብሎ የምስራቹን ነግራት ከእሷ ተሰወረ፡፡
ቅድስት አፎምያም የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን ዝግጅት ከፈጸመች በኃላ ወደ
ኤጲስቆጶሱና ወደ ካህናቱ መልዕክት ላከች እነሱም መጡ፡፡ ለእነሱም ቀሪ
ገንዘብዋን ለድሆች ለጦም አዳሪዎች ይሰጥዋቸውም ዘንድ አስረከበቻቸው፡፡
ከዚህ በኃላ ተነስታ ጸለየች፣የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልንም ሥዕል አንስታ
አቅፋ ሳመችው/አፎሚያ ለሰይጣን ይህንን ስዕል ስታሳየው ነው አሳች መልኩ
ወደ ሰይጣንነት የተቀጠረው/ ያን ጊዜም ቅድስት ነፍሷ ከሥጋዋ ተለየች፡፡ ቅዱስ
ሚካኤልም የከበረች ነፍሷን በብርሃናዊ ክንፉ አቅፎ ደግፎ የፈጣሪውን
መንግስት እንድትወርስ አድርጓታል፡፡
ከቅድስት አፎምያ ሁለት ነገር እንማራለን፡፡ አንደኛው ጥቅም አዘል ፈተናን አልፋ
ሰይጣንን ድል መንሳትዋ ሲሆን ሁለተኛው አፎምያ ጽድቅ ሰርታ የሥጋ ፈተናዋን
ድል ነስታ፣ሰይጣንን ማሸነፍ የቻለችው ጫካ ገብታ ሳይሆን በዓለም ሆና ነው፡፡
ስለዚህ ጽድቅ ሰርቶ ለመጽደቅ ሥራ እንጂ ቦታ እንደማይወስነው ታሪክዋ
አስተማሪ ነው፡፡
፨ ሰኔ 12 ቀን እረፍቱ ለቅዱስ ላሊበላ ፨
ቅዱስ ላሊበላ በነገሠ ጊዜ እኔ ንጉሥ ነኝ ብሎ ድሆችን ሳይንቅ፣በአገዛዙ ሰዎችን
ሳያስጨንቅ የኖረ ጻድቅ ነው፡፡ ጌታችን ቅዱስ ላሊበላን የፍቅሩን ጽናት በማየት
መልአኩን ላከለት፡፡ መልአኩም ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጠቀው፡፡ በዚያም
ቤተ ክርስትያንን እንዴት እንደሚያንጽ ጥበብን ገለጠለት፡፡
ቅዱስ ላሊበላም ሥጋ የለበሱ ሰዎች ሳይሆኑ ቅዱሳን መላእክቶች በስውር
እየተራዱት እነዛን አስደናቂ፣ለውጭ ጥበበኞች አጨቃጫቂ የሆኑትን ፍልፍል
አብያተ ክርስትያናትን አንጿል፡፡
ጌታችንም ሰኔ 12 ቀን በብርሃን ሰረገላ ተቀምጦ፣የሚያስፈራ መብረቅን ተጎናጽፎ
ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ወደ ቅዱስ ላሊበላ መጣ፡፡ ጌታም ‹‹ወዳጄ
ላሊበላ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁንልህ፡፡ እኔ በማይታበል ቃሌ
እነግርሃለሁ፤ማደርያህ በክብር ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር ይሁን፡፡ በጸሎትህና
በቃል ኪዳንህ ለሚታመን እምነቱ እንደ ጴጥሮስና ጳውሎስ ደም መፍሰስ
ይሆንለታል፡፡
ወደ ቤተ መቅደስህ የሔደ ኢየሩሳሌም ወዳለው ቤተ መቅደስ እንደ ሄደ
ይሆንለታል፡፡ መቃብርህንም የተሳለመ የሥጋዬን መቃብር እንደተሳለመ
ይሆንለታል፡፡ በየወሩ የተራቡትን እያበላ፣የተጠሙትን እያጠጣ መታሰብያህን
ለሚያደርግ እኔ የተሰወረ መና እመግበዋለሁ፤የህይወትንም ጽዋንም
አጠጣዋለሁ፡፡ በመታሰብያህ ቀን ዕጣን ወይም ስንዴ የሚያገባውን እኔ
በኢየሩሳሌም ሰማያዊት በውስጠኛው መጋረጃ አስቀምጬ ከተቆረሰው ሥጋዬ
አቆርበዋሁ፤በአማላጅነትህም እየታመነ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ያንተ
ስም በተጻፈበት ቦታ እኔ ስሙን እጽፋለሁ፡፡፡ በፍጹም ልቡ ለሚያምን ይህን
የማይታበል ቃል የተናገርኩ የህያው እግዚአብሔር ልጅ እኔ ኢየሱስ ነኝ›› አለው፡፡
ቅዱስ ላሊበላም ይህንን ቃል ኪዳን ስለሰጠውና ስላጸናለት ጌታችንን እያመሰገነ
እግሩ ላይ ወድቆ አመሰገነው፡፡ ሰኔ 12 ቀንም አረፈ፡፡ ቅድስት ነፍሱንም ቅዱሳን
መላእክት ይዘው የዘላለም ማረፍያው አስገቡት፡፡
፨ የቅዱስ ሚካኤል የወር በዓላት ከነምክንያት ፨
መስከረም 12 ፦ ቅዱስ ፋሲለደስን በመከራው ሰዓት የረዳበት እና የሰማዕትነት
ተጋድሎውን ከፍጻሜ እንዲያደርስ ከጎኑ ተገኝቶ ያጸናበት
ጥቅምት 12 ፦ ነብዩ ሳሙኤል ዳዊትን ቅብዐ መንግስት እንዲቀባው የነገረበት
ቀን ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ከቅዱሳን መላእክት ረድኤት በደንብ ስለተጠቀመ
ክብራቸውን በመዝሙሩ በደንብ መዝግቧል፡፡
ህዳር 12 ፦ የቅዱስ ሚካኤል በዓለ ሲመቱ ነው፡፡ በዚህ ቀን እግዚአብሔር
የመላእክት አለቃ አደርጎ ሾመው፡፡ የመላእክት ሹመት እንደ ሰው በተጽእኖ
አይደለም፡፡ ሰው በሰው ላይ የሚሾመው ለመገልገል ነው፡፡ የመላእክት ሹመት
ግን ለማገልገል ነው፡፡ እንደ ሰው አንዱ መልአክ አንዱን መልአክ አያገለግልም፡፡
አገልግሎታቸው እግዚአብሔርንና ሰውን ነው፡፡
በዚህም ቀን ለሰው ልጆች ከፈጣሪው ምህረት የሚለምንበት እና በቃል ኪዳኑ
ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣበት ቀን ነው፡፡ ለነዌ ልጅ ለኢያሱ በታላቅ ክብር
በንጉሥ ጭፍራ አምሳል የታየበት ቀንም ነው፡፡
ታህሳስ 12 ፦ ዱራታኦስና ቴዎብስትያን የረዳበት ቀን ነው፡፡
ጥር 12 ፦ ያዕቆብን ከኤሳው፣ተላፊኖስን ከአመጸኛው ያዳነበት ቀን ነው፡፡
1.8K views09:04