Get Mystery Box with random crypto!

አስሐበን -ነቢ የረሱል ጓዶች የፅናት አምሳል የመርህ ወዳጆች ዘማች እግረኛ የኡማው ፈርጦች ለቅኑ | Abdurahman Seid (ሜጢ)

አስሐበን -ነቢ የረሱል ጓዶች
የፅናት አምሳል የመርህ ወዳጆች
ዘማች እግረኛ የኡማው ፈርጦች
ለቅኑ መንገድ ከዋክብት ጌጦች።

(ከባቲ ወንድሞች የዜማ ግጥም የተወሰደ)

ሙስዓብ የመካውያኑን ሙሽሪኮች ትኩረት ከነብያችን ወደርሱ ለማድረግ የኢስላምን ባንዲራና ከርሳቸው ጋር በመልክ መመሳሰሉን ተጠቀመ። ተረባርበው ገደሉት። ሙሐመድን ገደልነው ብለውም ወበሩ። የርሱም አወዳደቅ በፊቱ ከመሆኑ ጋር አፈር ውስጥ ድብቅ ነበር ያለው። የታሪክ ፀሃፊያኑ "ያንቱን ሞት ከማይ ቀድሜ ልሙት" ያለ ነበር የሚመስለው ይላሉ።

ያ የሙስዓብ ኢብኑ ዑመይር ቀብር ነው ብለው ሲያሳዩዋችሁ አንዳች ስጋ ከአካል ተቆርጦ የሚረግፍ ያህል ነው ንዝረትና ህመሙ። ያ ቅምጥል ለግላጋ ወጣት ከፈን አጥቶ በቅጠል ሲቀበር ክስተቱ በሐሳብ ግጥም ይላል። ነብዩ ጀናዛው አጠገብ ሆነው 'ሙስዓብን መካ ጎዳናዎች ላይ በቅምጥል ህይወት አውቀዋለሁ፣ ዛሬ ደግሞ መከፈኛ አጣ፣ ሙስዓብ ሆይ ሰላም ባንተ ላይ ይሁን ሰላም በናንተ ላይ ይሁን የኡሑድ ሰማዕታት ሆይ ሲሉ ድምፃቸውን የሰሙ ያህል መስሚያን ያንኳኳል።

ይህ ጀበሉ-ር-ሩማት  ሲሆን በነብያችን (ሰዐወ) ልዩ የጦር ሜዳ ላይ ንባብ ቀስተኞች ከበው ከላዩ ላይ ሳይወርዱ የመካን ሙሽሪኮች ድንገተኛ ጥቃት ይመክቱና ቀስት ያስወነጭፉባቸው ዘንድ ጥብቅ ትዕዛዝ የተሰጠበት ቦታ ነው።

ነብያችን ሙተዋል ስለተባለ ብቻ ሶሐባው ሁሉ ውሉ ጠፍቶበታል። ሙሽሪኮቹ ያለምንም ርህራሄ እየተከታተሉና እያደኑ ይገድሏቸው ይዘዋል። እርሳቸው ሞተው የኛ መኒር ትርጉም ምንድንነው በሚል የቻሉትን ታግለው ይወድቁ ይዘዋል።

የኛ ነብይ ግን በዚያች ትዕዛዝ መጣስ የተነሳ በዙሪያቸው ጥቂት ሶሐቦች ብቻ እየተከላከሉላቸው እዚያው ኡሑድ ባለ አንድ ጉድጓድ ውስጥ ወደቁ። ጥርሳቸው ተሰበረ። የብረት ቀለበት የግንባር አጥንታቸውን ሰብሮ ገባ።

በዚህ የተሰባበረ አካላቸውና ህመማቸው መሃል እንኳ ሆነው መለኮታዊ ተልዕኳቸውን አልዘነጉም። የሰውነት ድክመትና ትክትና አልጎበኛቸውም። በርግጥ አካላቸው ዝሏል፣ ኃይላቸው ደክሟል።

ከዚያ ከወደቁበት ተነስተው የዛለ አካላቸውን ይዘው ብትንትኑ የወጣውን ሰሐባ ሁሉ ለመሰብሰብ ከፍታ ቦታ ለማማተር እያዩ ባለበት ቅፅበት ከዕብ ኢብኑ ማሊክ (ረዐ) አያቸውና በደስታ "ረሱለሏህ በሕይወት አሉ" ብሎ አንዴ ሲናገር በርሱ የደስታ ስህተት የጠላት ዒላማ እንዳያገኛቸው በእጃቸው ምልክት "ቆይ አንዴ ዝም በልማ" አሉት።

ከፍ ወዳለው ተራራ ለመውጣት ቢፈልጉም የአካላቸው ዝለት፣ ቁስለትና ስብራት አቀባቸው። በክንዶቹ ወደርሳቸው ሲወረወሩ የነብሩ ቀስቶችን ሲከላከል የነበረው ጦልሐ ኢብኑ ዑበይዲላህ (ረዐ) ጎንበስ ብሎላቸው በትከሻው ላይ ተወጣጡ። 'ጦልሐ ጀነትን አፈሰ አሉ'።

እነሆ ሰሐባው ሁሉ ወኔው ተሰበሰበለት። በደንብ ተዋግተውም ከመጀመሪያው ዙር ሽንፈት በኋላ መከላከል ቻሉ። የኢስላምን ባንዲራ ከሙስዓብ መሰዋት በኋላ ዓሊይ ያዟት። ከዚያች ቅፅበት በኋላ አልወደቀችም።

ያ የሐምዛ ቀብር ነው ሲሉህ አላህ ለነብዩ በአስቸጋሪ ጊዜ መከታ እንዴት እንዳደረገላቸው፣ በዚህ ዘመቻም የአካል ክፍላቸው መቆራረጡ የነቢን ሐዘን እንዴት እንዳበረታው፣ የሐምዛ እህትና የርሳቸው አክስት ሰፊያ የሐምዛን አካል እንዳታይ ረሱሉ አርቋት እንዳታይ ማለታቸው ሁሉ በሐሳብ ግጥም ይላል።

ሲራን ላነበበ፣ የሰማዕታቱን ገድል ላስታወሰ ሁሉ ትኩስ መርዶ ነው። ለኢስላም መቋቋም የተከፈለን ዋጋ ሁሉም በእዝነ-ህሊናው ያመጣል። ሳያስበው ልቡ ትመታለች፣ ዓይኖቹም ያነባሉ።

የሙስሊም ወንድም ክብርና የሙስሊሞች ህብረት ልክ እንደዚህች ተራራ ናት። ችላ ብለህ የለቀቅካትና የተረማመድካት ጊዜ አንተንም ሌሎችንም ለኻሊድ አይነቱ ስትራቴጂስት አሳልፈህ ትሰጣለህ። በመጨረሻውም ዙር ተቀርጥፈህ የምትበላው ጥቁር በሬም አንተው ትሆናለህ። ተራራውን ጥብቅ። ትግልና ፍልሚያህን ግን ለቅፅበትም እንዳትተው።

መልካም ለይለተል ጁምዓ