Get Mystery Box with random crypto!

#ከስሜ_በፊት ክፍል ዘጠኝ 'ይሀውላችሁ አንድ ጊዜ የተሳሳተ አረዳድ እንዳይኖራችሁ...' 'ዝም በ | ሜርሲ እና ብዕሯ✍

#ከስሜ_በፊት
ክፍል ዘጠኝ

"ይሀውላችሁ አንድ ጊዜ የተሳሳተ አረዳድ እንዳይኖራችሁ..."
"ዝም በል!" ከሪም ዓይኖቹን በቁጣ አፍጥጦ አቋረጠው።ወደ ፊት አንድ እርምጃ ተጠግቶት
"ከዚህ በላይ እንድትዋሸን አንፈልግም።ማብራራትም አይጠበቅብህም እኮ የፃፍከው ከበቂ በላይ አብራርተህ ነበር።"
"በእኛ ላይ ሪሰርች እየሰራህ ነበር?..በእኛ በድሃዎቹ ላይ!?"ባህሩ ነበር።
"እኛ በንፁህ ልብ ነበር የቀረብንህ።በንፁህ ልባችን አቀረብንህ።አንዳች ጥርጣሬ አልነበረንም።ህጋችንን የሻርነው ዛሬ ገና ነበር።ጥፋት እንደሆነ እየተሰማኝ ነበር ማስታወሻህን የገለጥኩት።አንድ ገፅ አንብቤ እተወዋለሁ ብዬ ነበር።ግን ስለ እኔ ስትፅፍ እንዴት ላቁም!? ስለ ጓደኞቼ ስትፈተፍት ምንም አይደሉም አያውቁም ብለህ ገመናችንን በአደባባይ ልታውጅ...ሰብአዊነት የሚባል ነገር አለ እኮ አማኑ..." ዝቅ ስትል እንባዋ ከመሬቱ ላይ ዱብ ዱብ አለ።
ዳንኤል ጥጉን ይዞ በዝምታ ይመለከታቸዋል።
ከሪም እጁን ሱሪ ኪሱ ውስጥ እየከተተ
"አሁን ወደ መጣህበት ትሄዳለህ ወይስ እኛ እንውጣለህ?" አለው።
አማኑኤል እንባው ባቀረሩ ዓይኖቹ ተመለከታቸው።
"እውነቱን ሳልነግራችሁ..." ፊቱ ላይ ያረፈበት ቡጥ ንግግሩን አቋረጠው።ዳንኤል ዘሎ ከሪምን ያዘው።አማኑኤል የተመታበትን በኩል በአንድ እጁ በመያዝ ቀና ብሎ ተመለከታቸው።
"ባንዳ... አንድ ነገር እናገራለሁ ብትል ልገድልህ ሁላ እችላለሁ።ህዲና ሳይጠፉ የጠፉትን አባትህን ፈልጋቸው።"
"አዎ አባቴ ጠፍቷል...እርሱን ለመፈለግ ስል ነው ከካናዳ ድረስ የመጣሁት።" ይሄን ሲናገር ድምፁን ከፍ አድርጎ ነበር።ዓይኖቹ ላይ የሞላው እንባ ጉንጩ ላይ ይፈስ ነበር።
"መዋሸት እንጂ መደበቅ ይቻላል ስትሉኝ አልነበር!?....እኔም ደበቅኳችሁ እንጂ አልዋሸሁም።አንድ ጊዜ ተረጋግታችሁ ስሙኝና ከዛ እሄድላችኋለሁ።አማኑኤል ከአንዱ ጥግ በሚገኘው በርኩማ ሄዶ ተቀመጠ።ቀና ብሎ ሲመለከታቸው ባህሩ ቀድሞ ፍራሹ ላይ ተቀመጠ....መዓዛም ከጫፉ ሄዳ ተቀመጠች ዳንኤል ከሪምን በእጁ እንደያዘ ወስዶ አስቀመጠው።
"ቤተሰቦቼ ከዚህ ሃገር ከወጡ አስር ዓመት ሆናቸው።እኔ ግን እዚህ መሆንን ስለምፈልግ እየተመላለስኩ በመሃል ነበርኩ።ሁሉ ነገር በሰላም እየሄደ ነበር አባቴ እስኪታመም ድረስ" ሁሉም ከጎነበሱበት ቀና ብለው ተመለከቱት።
* * *
ከስድስት ወር በፊት
ካናዳ


አማኑኤል የሆስፒታሉን በር በዝግታ በመክፈት ወደ ውስጥ ገባ።ከአልጋው ላይ አባቱን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያየው ውስጡ ክፉኛ ተሸበረ።አባቱ በመተንፈሻ(ኦክሲጅን) ነበር የሚተነፍሱት።ወደ ውስጥ በዝግታ በማምራት ከአጠገቡ ባለው ወንበር ተቀመጠ።አባቱ በፈገግታ ካዩት በኋላ ቀና በማለት ትራሱን በመደገፍ ተቀመጡ።
"አባዬ በአስቸኳይ እፈልግሃለሁ ብለሀኝ ነበር።ምንድነው በጣም አመመህ እንዴ!?"
"በጣም ልጄ በጣም አመመኝ"
አማኑኤል በመደናገጥ
"ታዲያ ሃኪሞቹን ልጥራልሃ..."ሊነሳ ሲል በእጁ ይዞ አስቀመጠው።
"እንደዛ አይደለም ልጄ።እኔን ያሳመመኝ ሌላ ጉዳይ ነው።"
"ምንድነው አባ አስጨነከኝ እኮ"
"ሁሉንም ለመናገር ህመሙ ፋታም አይሰጠኝ።እስከዛሬ አንተም እናትህም እኔን አታውቁኝም ከመጥፎ ባህሪዬ ውጭ።የምታውቁት የበግ ለምድ የለበሰውን ሰው ነው።ግን ተኩላ ነበርኩ።በበጎች ውስጥ ተመሳስዬ የገባሁ ተኩላ።ያየሁትን ሁሉ እየቀረጣጠምኩ የበላሁ ሆዳም ተኩላ።"
አማኑኤል የሚሰማው ለጆሮው ሰቀጠጠው
"አባዬ...."
"አስጨርሰኝ!....እኔና እናትህ ከመተዋወቃችን በፊት የእርዳታ ድርጅት ላይ እሰራ ነበር።ያኔ ንፁህ ነበርኩ።የበላዮቼ ግን በሰው መራብ የደለቡ ነብሰ በላዎች ነበሩ።ሳይገባኝ አነካኩኝ ከዘገየም ቢሆን ስደርስባቸው ላጋልጣቸው ብል እኔንም ሳላውቅ አነካክተውኛልና እስር ቤት እንደምበሰብስ ነገሩኝ በእናቴና አባቴም አስፈራሩኝ አማራጭ አልነበረኝምና ዝምታን መረጥኩ።እያደር ሁሉን ነገር ለመድኩት ለድሃዎች ተብሎ ከተላከው የእርዳታ ገንዘብ ወደ ኪሴ አስገባ ጀመር።ቀስ እያለ ከእነርሱ ብሼ ተገኘሁ።በመሃል እናትህን አገኘኋት እርሷ ለጌታ ልቧን የሰጠች ሴት ነበረች እኔ ደግሞ ለሌላኛው ጌታ ልቤን የሰጠሁ እና የተገዛሁ።እርሷን አግብቼ አንተን ከወለድሁ በኋላ ላቆመው ወስኜ ነበር ግን ታገልኩ ልቤንም ወደ ጌታ ልመልስ ሆንኩ የለመደው እጄ ግን አላርፍ አለ።መፅሃፉ ለሁለት ጌቶች ልትገዙ አይቻላችሁም ሲል እውነቱን ኖራል ለካ!...ለአንዱ ከልቤ ተገዛሁ ለአንዱ በማስመሰል ተገዛሁ።በድሆች እንባ የእኔን ቤት ገነባሁ።የእኔን ከርስ እየሞላሁ ከሌላቸው አጎደልኩ።ያ ስለ ሚያሰቃየኝ ነው እጠጣ የነበረው።ሰላማችሁን የነሳሁት።ጥሩ ልሆንልህ እየሞከርኩ አቃተኝ።ከገንዘብ ጋር የተፋቀረ ሰው ስለሌላው ግድ የለውም።ሰላም ካገኘሁ ብዬ ወደዚህ ሸሽቼ መጣሁ።ስራውን ብተወው እንኳ የትላንት ፀፀቴ በደሌ ቤቴን በየቀኑ ያንኳኳል።ችላ ብዬ ቆየሁ አሁን ግን በማላመልጠው እጅ ተያዝኩ።ይሄን ቀን ዘንግቼው ኖሮ ለጊዜያዊ ስል ዘላላማዊውን ገደልኩት።ትላንት በአልጋዬ ላይ ሆኜ ቢቀበለኝ ብዬ ንስሃ ገባሁ።አሁን ነብሴ ትንሽም እረፍት አገኘች።እርሷ እንዳመለጠች ይሰማኛል።እኔ ተነስቼ ስህተቴን ባርም ምንኛ ደስ ባለኝ ግን አርፍዷል።ለዛ አንተ ስህተቴን እንድታስተካክለው።ያበላሸሁትን እንድታቀናው።ያስለቀስኩትን አንባውን እንድታብሰው ወደድሁ።ወደ ኢትዮጲያ ተመለስና አባትህን ፈልገው።የጠፋውን አባትህን በድሆች ንፁህ ልብ ውሰጥ ፈልገው።ያኔ ሳይነካካ በፊት ንፁህ ልብ የነበረውን አባትህን ህዲና በንፁሃን ውስጥ ፈልገው።እነርሱን ሆነህ ህመማቸውን ታመህ ስቃያቸው እስኪገባህ ፈልገው ስታገኘው የዛሬውን ስህተቱን አርምለት።ያስለቀሳቸውን የትኛው እንደሆነ ሲገባህ እንባቸውን አብስ።ይሄኛው አባትህ የዘራውን አረም ከመሃከላቸው ንቀል።የነጠኳቸውን ሃቃቸውን መልስላቸው።አደራህን ልጄ...." ይሄን ብሎ አይኖቹን ከደነ እስከወዲያኛው።
* * *
"እኔም የጠፋውን አባቴን ፍለጋ እናንተ ጋር መጣሁ....."


ይቀጥላል......

@Mercy_ena_berua