Get Mystery Box with random crypto!

#ከስሜ_በፊት ክፍል ስድስት 'እንድታምነኝ እፈልጋለሁ ቡራ።ብዙ የቀሩኝ ነገሮች አሉ እነርሱን እ | ሜርሲ እና ብዕሯ✍

#ከስሜ_በፊት

ክፍል ስድስት

"እንድታምነኝ እፈልጋለሁ ቡራ።ብዙ የቀሩኝ ነገሮች አሉ እነርሱን እስካሳካ ድረስ ሚስጥሬ ሚስጥርህ ይሁን።"
ብሩክ ካለማመን ማመኑ ስለሚሻል ብቻ ተቀበለው።
* * * *
"እንደብቃለን እንጂ አንዋሽም ነው ያልሽኝ አይደል ወደ እዚህ ህይወት ምን እንዳስገባሽ ማወቅ ፈለግኩ እና..."
"ከማንም ጎዳና ተዳዳሪ የተለየ ታሪክ የለኝም።ታሪካቸው ታሪኬ ነው አማኑ።"
"ምን አልባት ብትነግሪኝ እረዳሽ ይሆናል::"
"እንዴት?"
"ወደ ቤት ልመለስ ስለሆነ...እዛ እንደዚህ አይደለም።"
አጠገቡ ሄዳ ተቀመጠች።
"ልትሄድ?"
"የምፈልገውን እስካገኝ ነው እዚህ ያለሁት።"
"አባትህን አገኘሃቸው!?"
"እያገኘኋቸው ነው።"
* * * *
"አማኑ ይቅርብህ...እኔን የምታውቀኝ በምግብ ብቻ ይሁን።"
ፈገግ ብሎ አየው።
ባህሩ ዳቦውን እየገመጠ በዝምታ ቆየ።
"ለምንድነው የምትበላው!?"
"ለመኖር..."
"እርሱማ ሁላችንም ለመኖር ነው የምንበላው።"
"እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ሰለ ሚጨንቀኝ ነው የምበላው።ስጨነቅ ስጨነቅ ከምግብ ውጭ መሸሸጊያ ያለ አይመስለኝም።በቃ በዚህ ማጣት ውስጥ ሆኜ እንኳ እበላለሁ።እራሴን የምበቀለው በምግብ ውስጥ ነው።ምግብ ሚገድል ቢሆን ኖሮ ሟች ነበርኩ።"
አማኑኤል በመገረም አየው በእርሱ ውስጥ አንድም ቁም ነገር አገኛለሁ ብሎ ባለማሰቡ እራሱን ወቀሰ።
"ምንድነው ያጣሀው?"
"ያላጣሁትን ጠይቀኝ...ከሁሉ የተሻለውን ሰው ግን አጣሁ እናም ከሁሉም ወደ ተሻሉኝ ሰዎች መጣሁ።"
"ተምረሃል?"
"ወረቀቷን ነው!?.....ግቢ ጨርሼ ሰራተኛ ነበርኩ።"
አማኑኤል ተደናግጦ ተመለከተው
"ታዲያ ለምን...?"
"ሰው አጥቼ አልኩህ እኮ አሙ...አሁን ብዙ አትዘብዝበኝ ስለ እራሴ እንኳን አውርቼ ጥቂቷን ሳስብ እታመማለሁ።በርገር መች ነበር እጋብዝሃለሁ ያልከኝ?"
* * * *
"ሰለ እኔ ብዙ ለማወቅ አትድከም አማኑ።እኔ ታሪክ የለኝም።"
"ለምንድነው ሃይማኖትህን ይሄን ያህል የምትወደው!?"
"ሃይማኖት አይደለም ክርስቶስን ነው የወደድኩት...ከእርሱ ጋር ነው ፍቀር የያዘኝ።እንደሚገባኝ አላውቀውም ለዛም ነው ለጓደኞቼ ላወራቸው እኔ ያገኘሁትን ሰላም ልገልጥላቸው ያልቻልኩት።"
"እንዴት!?"
"እኔ ጌታን የተቀበልኩት አምና ነው።ዓመትም አልሞላኝ።እዚህ መጥተው ሲሰብኩ ሰማሁ ተሸነፍኩለት።እርሱን ካስተዋወቁኝ በኋላ እነርሱ ስለምን እንደተዉኝ አላውቅም።ግን የነገሩኝን አልተውኩትም።ሰዉን አውቀዋለሁና እነርሱን ከክርስቶስ ጋር አላነፃፀርኩም።በቃ አፈቀርኩት ግን አላውቀውም።ሁሌ ከማነባት ያኔ ሲመሰክሩልኝ በነፃ ከሰጡኝ ትንሿ መፅሃፍ ቅዱሴ በስተቀር እውቀቱ የለኝም።"
"እንዲያስተምሩህ አልነገርካቸውም!?"
"ስልክ ስላልነበረኝ የከሪምን ሰጠኋቸው።ይደውላሉ ብዬ ብጠብቅ ብጠብቅ የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ።ምን አልባት ቁጥሩ ጠፍቶባቸው ይሆናል።ሌሎችን የማግኘት እድሉ ነበረኝ ግን አልቻልኩም።"
* * * *
"ድህነትን ይሄን ያህል እየጠላህ ለምን ለመስራት አልሞከርክም!?"
ከሪም ጥቂት ፈገግታ አሳየው
"እናቴ ስትሞት ውስጤም አብሯት ሞተ።ከዛ በኋለ በምንም መንገድ አቅምን ማግኘት አልቻልኩም ነበር።የሰው ልጅ ውስጡ ከሞተ ሞተ ነው።ለሞቱም ተገዢ ነው።ስጋህ ቢፍጨረጨረ ዋጋ የለውም።የሞተ ሰው ምንም ሊያደርግ አይቻለውም አማኑ።"
* * * *
"የጨረስኩ መስሎኝ ነበር።ያወኳቸው።የጨረስኳቸው።ዛሬ ሁሉንም ላወራቸው ሞከርኩ።ገና መች የህይወታቸውን መዝገብ መግለጥ ጀመርኩና!?የማያልቁ እልፍ ናቸው።እነርሱን ሳላውቅ ከዚህ ወዴትም አልሄድም።ለብሩክ የገባሁለትን ቃል ኪዳን አፈርሰው ይሆናል።ግን አባቴን ፈልጌ አላገኘሁትም።ገና ብዙ ይቀረኛል።" ማስታወሻውን ወደ መደርደሪያው መለሰው።

ይቀጥላል...

@Mercy_ena_berua