Get Mystery Box with random crypto!

ረቡዕ ጥር 19 እንጦጦ ማርያም የቄደር ጥምቀት እና ንስሐ የመሰጠት አገልግሎት አለ! ቀሲስ ሄኖክ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ረቡዕ ጥር 19 እንጦጦ ማርያም የቄደር ጥምቀት እና ንስሐ የመሰጠት አገልግሎት አለ!

ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ የነፍስ ግዴታዎትን ይወጡ!

የወለላይቱ እመቤት ልጆች ባለፈው ታህሳስ 27 የቄደር ጥምቀት አዘጋጅተን ብዙ ሰው ተጠምቆ ነበር። በተለያዩ ምክንያቶች ባለፈው ያልተጠመቃችሁ ሰዎች ጥር 19 ረቡዕ ጠዋት 3 ሰዓት የቄደር ጥምቀት አለ መጥታችሁ ተጠመቁ። ጥምቀት አንድ ነው ግን የምንጠመቅበት ምክንያት ልዩ ልዩ ነው።

1ኛ/ የልጅነት ጥምቀት ይህም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕጸነ ዮርዳኖስ ተወልደን የቅድስት ሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት ነው(የክርስትና ጥምቀት)

2ኛ/ የፈውስ ጥምቀት ነው። ይህም አንድ ሰው ሲታመም በጽኑ እምነት ንስሐ በመግባት ከደዌ እና ከክፉ መናፍስት እድናለሁ እላቀቃለሁ ብሎ የሚጠበቀው የጸበል ጥምቀት ነው።

3ኛ/ የንስሐ ጥምቀት (ቄደር) ነው።

ቀድር ማለት በአረብኛ እድፍ ርኩስ ማለት ነው። መጽሐፉ ወደ ግዕዝ ከተተረጎመ በኋላ ቄደር ተብሏል።

የቄደር ጥምቀት ለምሳሌ እሮብና አርብ ከበላን፣ ውርጃ ከፈጸምን፣ ከሃይማኖታችን ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ሩካቤ ሥጋ ከፈጸምን፣ የአሕዛብን ምግብ ከበላን፣ ኦርቶዶክስ ሆነን ወደ ሌላ እምነት ገብተን ከተመለስን፣ ለዛር ለጨሌ ለአቴቴ የተገበረውን መስዋዕት ከበላን፣ ጠንቋይ ቤት ከሄድን፣ ዛር አንጋሽ ጋር ከሄድን፣ ግለ ወሲብን ከፈጸምን፣ ሴት የወር አበባዋን ሳትጨርስ ግንኙነት ካደረገች፣ ወንድም የወር አበባ ካልጨረሰች ሴት ጋር ግንኙነት ካደረገ፣ ጫት ሲጋራ ከተጠቀምን ወዘተ ቄደር የግድ መጠመቅ አለብን።

ወዳጆቼ ልብስ በሳሙና ይታጠባል በመጨረሻ በኦሞ ተዘፍዝፎ ይለቀለቃል። በዚህም ጸዐዳ ይመስላል። ንስሐ ኃጢአታችንን የምናጥብበት ሳሙና ነው። ቄደር ደግሞ ኦሞ ነው ያነጻናል።

በተለይ ንስሐ ገብታችሁ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ያሰባችሁ ቄደር ተጠምቃችሁ ብትቀበሉ መልካም ነው። በንስሐ ያላካተትነው ኃጢአት በቄደር ይነጻልና። እንዲሁም በቄደር ነጽተን ቅዱስ ቁርባን ብንቀበል ይሰምርልናል።

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለባችሁ ቄደር የምትጠመቁት ንስሐ ገብታችሁ ንስሐችሁን ጨርሳችሁ ነገር ግን ቄደር ሳትጠመቁ የቀራችሁ ብቻ ናችሁ።

ሌላው ንስሐ ለመግባት አስባችሁ የንስሐ እድሉን ያላገኛችሁ እና ንስሐ አባት የሌላችሁ ጥር 19 ቀን ረቡዕ ጠዋት 3 ሰዓት መጥታች በደብሩ ካህናት ንስሐ መግባት ትችላላችሁ።

የእናንተን ችግር የሚረዱ በተለይ ለካህናት መናገር የምትጨነቁበትንና የምታፍሩበትን ለምሳሌ ግለ ወሲብንና የወሲብ ፊልምን የተመለከቱ ወዘተ ዘመን አመጣሽ ኃጢአትን የሚረዱ ካህናትን ስላዘጋጀን መጥታችሁ በነፃ ንስሐ ግቡ፣ የኃጢአት ሸክምን በእናታችሁ ቤት አራግፉ።

ስለዚህ ጥር 19 ረቡዕ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስትያን። ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጸሎቱ ይጀመራል መጥታችሁ ተጠመቁ።

አደራ ጥምቀቱ ጸበሉ ቦታ ሳይሆን እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስትያን አዳራሽ ውስጥ ነው።