Get Mystery Box with random crypto!

#_ሰኔ_22_የቅዱስ_ዑራኤል_እለት_ከሞት_የዳንኩበት_ዕለት_ነው በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም ተወ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

#_ሰኔ_22_የቅዱስ_ዑራኤል_እለት_ከሞት_የዳንኩበት_ዕለት_ነው

በቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ተወዳጆች ሆይ ከላይ በርዕሱ የነገርኳችሁ የሞት አፋፍ ታሪክ የተፈጸመው የዛሬ 17 ዓመት በ19 98 ዓ.ም ምህረት ነው።

የዛሬ 20 ዓመት ጻድቃኔ ማርያም እያለሁ በረከት አገኝባቸዋለሁ ብዬ የማስታምማቸው ሁለት ወጣቶች ነበር። የሁለቱም ሕመም ይዘት አንድ አይነት ቢመስልም፣ በሳይንሱ ዓለም ስም ቢሰጠውም በመንፈሳዊው ዓለም ደግሞ የዛ የመናጢ ሥራ ነው።

እነዚህን ሁለት ወጣቶች በክፉ መናፍስት አእምሮአቸው ታስሮ ስለነበር፣ አእምሮአቸው መታሰር ብቻ ሳይሆን፣ በተለይ አንደኛው ሙሉ በሙሉ እራሱን አያውቅም ነበር። ሁለተኛው ሻል ቢልም አልሸሹም ዞር አሉ ነው።

እነዚህን ሁለት ታማሚ ወጣቶችን ያለ ገንዘብ ክፍያ በነጻ ሳስታምም እመቤታችን ታድናቸዋለች ለእኔም ለነፍሴ ይሆኑኛል ብዬ ነበር የማስታምማቸው። በእመቤታችን ፈቃድ እነዚህን ሁለት ወጣቶች ከጻድቃኔ ማርያም ወደ እንጦጦ ማርያም ይዣቸው መጣሁ። በዛም መንፈሳዊ ትግል ጀመርን።

መቼም ማስታመም ሲባል የለመዳችሁትን የሰማችሁትን ማስታመም ሳይሆን እራሳቸውን ስለማያውቁ፣ እንደ ሕፃን ልጅ ተከታትሎ ምግብ ማብላት ሥራዬ ነበር። ሌሊት ኪዳን፣ ጠዋት ጸበል፣ ጾም ከሆነ ደግሞ ከሰዓት ቅዳሴ ወስዶ አስቀድሰን መምጣት ሥራዬ ነበር። እራሳቸው ላይ ሽንት ሲሸኑ፣ ሲጸዳዱ ሰውነታቸውን፣ ልብሳቸውን ማጠብ ሥራዬ ነበር። ልብሳቸውን ሰውነታቸውን በየሳምንቱ ወንዝ ወስጄ ማጠብ ሥራዬ ነበር።

ሌሊት ተነስተው ስለሚወጡ ለመተኛት እቸገር ነበር። በውድቅት ሌሊት በር እየከፈቱ ሊወጡ ሲሉ ነቅቼ አስተኛቸዋለሁ። እነሱ አይተኙ እኔንም አያስተኙ። ታዲያ አንድ ቀን ሌሊት ከፍተው እንዳይወጡ ምን ላድርግ? ብዬ አሰበኩ! አንድ ሐሳብ መጣልኝ ደስም አለኝ።

በጠዋት ተነስቼ መርካቶ ገብቼ ሁለት ሰንሰለት እና አራት ደህና ቁልፍ ገዝቼ መጣሁ። አይመሽ የለ መሸ። ሲመሽ አንዱን ሰንሰለት አንዱ ታማሚ እጁ ላይ አስሬ እጁን በሰንሰለት ቆለፍኩኝ። የእሱን ሰንሰለት ጫፍ ደግሞ የእኔ ቀኝ እጅ ላይ አስሬ የእኔንም እጅ በሰንሰለት ቆለፍኩኝ።

የአንደኛውን ታማሚ ግራ እጅ በሰንሰለት አሰርኩኝ። የእሱን የሰንሰለት ጫፍ አዙሬ ግራ እጄ ላይ አስሬ እጄን በሰንሰለት ቆለፍኩኝ። የእነሱን ሁለት ቁልፍ የእራሴን ሁለት ቁልፍ ያዝኩኝ። እነሱን ግራ ቀኝ አድርጌ እኔ ሆዬ መሃላቸው ተኛሁ። እነሱም ተኙ፣ ተሳስረን መተኛት ጀመርን። እንደነገርኳችሁ እራሳቸውን ስለማያውቁ ሌሊት አንደኛው ቀስ ብሎ ተነስቶ ወደ በሩ ሊሄድ ሲል እጄ ከእጁ ጋር በሰንሰለት ስለታሰረ ጎተተኝ ነቃሁ "ተኛ" ብዬ ተቆጥቼ አስተኛሁት።

እሱ ሲተኛ ከሆነ ሰዓት በኋላ ያኛው እወጣለሁ ብሎ ተነሳ፣ ወደ በሩም ሊሄድ ሲል እጁ ከእጄ ጋር በሰንሰለት ስለታሰረ ሲጎትተኝ ተነሳሁ። ብቻ ምን አለፋችሁ እመቤታችን እንድታድናቸው ከእነሱ ጋር አራት ዓመት በሰንሰለት ታስሬ ተኛሁ። እንዲህ ስላችሁ ጽድቄን ልነግራችሁ አይደለም የቅዱስ ዑራኤልን ተአምር እንጂ። አበው "ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ" ስለሚሉ የፈተናዬን መነሻ እንድታውቁት ነው። ለአራት ዓመታት ቀኝና ግራ እጄ በሰንሰለት ስለታሰረ ለረጅም ዓመት ሁለቱ እጄ ላይ የሰንሰለቱ ቅርጽ ነበር። በሂደት ጠፋ።

በአራተኛው ዓመት ሰኔ 21 ቀን 19 98 ዓ.ም እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አብረን ሌሊት ገብተን እዛው አደርን። ሌሊቱን እዛው ያለ እንቅልፍ አድረን፣ ጠዋት ኪዳን አድርሰን፣ ጸበል ወስጄ አስጠምቂያቸው ስመጣ ረፋፈደ። ቀን እነሱም እኔም አላረፍንም።

በማግስቱ ሰኔ 22 ሌሊት ሽንቴ መጣ ሲል የግድ እሱን ወደ ሽንት ለመውሰድ የእኔም የእሱም የአንደኛው ታማሚ እጅ መፈታት ነበረበት። ፈትቼ ሽንት ወጥቶ ተመለሰ። ይህ የሆነው ሌሊት 7 ሰዓት ነበር። ከምተኛ ለምን አልጸልይም ብዬ ስለማይመች እነሱን እጃቸውን ፈትቼ አሰተኝቼ ጸሎት ጀመርኩ። ሌሊት 9 ሰዓት ሲል ደከመኝ እዛው ቁጭ ባልኩበት ተኛሁ።

ብቻ ምን አለፋችሁ የሰማሁት ድምጹ መብረቅ ነበር የመሰለኝ። ሰማይ ምድሩ ተደባለቀብኝ። የት እንዳለሁ ረሳሁኝ። ሰመመንም ሕልምም መሰለኝ። ግን ከፍተኛ ሕመም ስለሚሰማኝ የሆነ ነገር እንደሆንኩ አወኩ። እንደምንም ብዬ በዳበሳ ቀና ስል አንደኛው እንኳን ሰው አህያ የማይመታበት በሩን የምንቀረቅርበት ዘበጥ ያለ መቀርቀሪያ ዱላ ይዞ ሊደግመኝ ጎንበስ ብሎ ቆሟል። ያኔ በደንብ ታወቀኝ። ለካ ደህና አድርጎ በዛ መቀርቀሪያ አቅምሶኛል።

ፊት ለፊቴ ቆሞ "እንዴት አልሞትክም? እኔኮ ሞተሃል ብዬ ነበር የተውኩህ፣ መነሳትህን ባውቅማ እንዳትነሳ አድርጌ እዛው ጨርስህ አልነበረም" በማለት አጋንንቱ ዓይኑን አፍጥጦ፣ ጥርሱን አግጥጦ ሊደግመኝ ይዝትብኛል። ምንም አቅም አልነበረኝም። የሞት ሞቴን ጸሎተ ማርያም እየጸለይኩ እመቤታችንን እየተማጸንኩ፣ ቅዱስ ዑራኤል ድረስልኝ አልኩ።

ተማሙቼ ተነሳሁና ሳየው ዱላውን እንደያዘ ፊት ለፊቴ ቆማል። "በቅዱስ ዑራኤል ስም ስጠኝ ዱላውን" ስለው ያለማቅማማት ሰጠኝ። ተቀብዬው አስቀመጥኩና ልጁን አረጋጋሁት። እራሴንም ተመለከትኩት። ለካ በዱላው የመታኝ ግራ ጭንቅላቴን ነበር። አልተፈነከትኩም ግን ከፍተኛ እብጠት እና ሕመም ነበነው።

ልጁንም "ለምንድነው በበሩ መቀርቀሪያ የመታኸኝ" አልኩት። እሱም "በፍጹም እኔ አልመታሁህም አለኝ። ስለገባኝ ተውኩት። በጣም የሚገርማችሁ በበር መቀርቀሪያ ግራ ጭንቅላቴ መመታቱ ሳይሆን በ10 ቀጥር ሚስማር በኩል አለመመታቴ እና አናቴ አለመበሳቱ ነው።

በሰንሰለት ተሳስረን ከመተኛታችን በፊት ሌሊት እየወጡ ሲያስቸግሩኝ በሩን በቀላሉ እንዳይከፍቱት፣ ሊከፍቱ ሲሉ በሩን ሲታገሉ እንድነቃ ብዬ የመቀርቀሪያው ጫፍና ጫፉ ላይ 10 ቁጥር ሚስማር መትቼበት ነበር። በዚህም ለመክፈት ሲታገሉ ነቃለሁ።

ግን አንድ ቀን ከፍተው ሌሊት ቢወጡ አንድ ነገር ቢሆኑስ እነሱም እኔም ተረጋግተን ብንተኛስ ብዬ ነው ሰንሰለቱን የገዛሁት። እንደነገርኳችሁ የመቀርቀሪያው ጫፎች ላይ 10 ቀጥር ሚስማር ስለነበረ ቀስ ተብሎ አዟዙሮ ካልተከፈተ መቀርቀሪያው ከመሾገሪያው አይወጣም።

ለማንኛውም ሰኔ 22 የቅዱስ ዑራኤል እለት ከሞት የዳንኩበት ዕለት ነው። እንዲህ መመታቴን የሰሙ ወዳጆቼ "ደም ወደ ውጭ ስላልፈሰሰ ምናልባት ደምህ ወደ ውስጥ ወይም ወደ ጭንቅላትህ ፈሶ ሊሆን ስለሚችል የሆነ መሳሪያ አለ ሄደህ ሆስፒታል ታየው። ጥሩ አይደለም እንዲህ አይነት ችግር በሦስት ቀን ውስጥ ሊገድልህ ይችላል" አሉ።

ወቸው ጉድ ብሞትማ ያኔ ሞት ነበር ከዛ ዘግናኝ መቀርቀሪያ ያዳነኝ ከሞት የታደገኝ ቅዱስ ዑራኤል እንደፈለ ያድርገኝ ብዬ አልሄድም አልኩ። ግን ለአንድ ሳምንት ጭንቅላቴ የራሴ አይመስለኝም ነበር። የሆነ ነገር የተሸከምኩ እስኪመስለኝ ጭንቅላቴ ከብዶኝ ነበር።

የእመቤታችንን ጸበል እየጠጣሁ፣ የሸንኮራ የቅዱስ ዮሐንስን እምነት ጭንቅላቴን እየተቀባሁ፣ የቅዱስ ዑራኤልን መልክአ እየጸለይኩ ሁሉም ሰላም ሆነ፣ ሞቴ አለፈ ቀሲስም ተረፈ። ይሄ ነው እንግዲህ ከሞት የዳንኩበት ታሪኬ እና የቅዱስ ዑራኤል ተአምር።

ነብዩ ዳንኤል"አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ፣ እነሱም አልጎዱኝም" እንዳለው ቅዱስ ዑራኤል ሊገድለኝ የነበረውን የዛን የመናጢ አፍ ዘጋልኝ። ከሞትም በተአምራት አዳነኝ። ት.ዳን 6፥22