Get Mystery Box with random crypto!

ይህንን ዘርዘር አድርገን ስናየው ‹‹ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱን በአንድነት ጹሟቸው›› ያለው የሁ | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

ይህንን ዘርዘር አድርገን ስናየው ‹‹ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱን በአንድነት ጹሟቸው›› ያለው የሁለቱን ቀን አክፍሎትን ነው፡፡ ሐሙስ በልተን ዓርብን ስግደት ውለን፣ ዓርብን እህል ውኃ ሳንቀምስ ቅዳሜንም ውለን ከትንሣኤ ቅዳሴ በኃላ እንድንገድፍ ያዘዘበት ነው፡፡ ‹‹ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻል ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም›› ማለቱ ዓርብን በጾም እና በስግደት ውለው የማክፈል ልምድ የሌላቸው፣ የጾም ልምድ የሌላቸው ግን መጾም የተቻላቸው ወጣንያን፣ ጎልማሶች አዛውንቶች የስቅለት እለትን ማክፈል ቢያቅታቸው ዓርብን በልተው ቅዳሜን ግን ያክፍሉ ማለቱ ነው፡፡ /ይህ ትዕዛዝ በደዌና ለመጾም የማያበቃ ልዩ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ያገናዘበ ነው/

በሰሞነ ሕማማት ፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ 15 በቁጥር 593 ላይ ሴቶች ጌጣቸውን እንዲተዉ ያዛል፡፡ ይህም የሆነው ማንም ሰው ዘመድ ሞቶበት አልያም ለቅሶ ቤት ሲሄድ ለሐዘን የሚመች ልብስ እንጂ ዓይን የሚገባ ጌጣ ጌጥ አድርጎ አይሄድም፡፡ ይህ ሰሞነ ሕማማት የጌታችንን ስቅለት እና ሞት እያሰብን የምናዝንበት እንጂ የምንጋጌጥበት ስላልሆነ ነው ሴቶች ጌጣቸውን አውልቀው ከመጋጌጥ የሚከለከሉት፡፡

እንዲሁም በዚህ በሰሞነ ሕማማት ባል እና ሚስት ሩካቤ ሥጋ እንዳይፈጽሙ ‹‹ክብርት በምትሆን በሕማማት ወራት ይህችን ኃጢአት ለሚሠራት ሰው ወዮለት›› በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ /ቁጥር 597/

በአጠቃላይ በቅድስት ቤተ-ክርስትያናችን ሥርዓት መሠረት በዚህ ሰሞነ ሕማማት የተከለከሉት ነገሮች እጅ ተጨባብጦ ሰላምታ መሰጣጣት እና መሳሳም፣ መስቀል መሳለም እና ማሳለም፣ ክርስትና ማንሳት፣ ክህነት መስጠት፣ ፍትሐት ማድረግ፣ መስከር፣ አብዝቶ እስከ ቆፈት መብላት፣ በተለይም የላመ የጣመ መብላት፣ ወዛ ፈዛዛ፣ ሳቅ ጨዋታ ጭፈራ የተከለከሉ ናቸው፡፡

ወዳጆቼ በዚህ በሰሞነ ሕማማት ጌታችንን ደግ ጊዜ አምጣ እያልን በጌታ ስቃይ ስቃያችን እንዲያልፍልን፣ በጌታ መከራ መከራችን እንዲርቅልን እንጠቀምበት፡፡

መልካም ሰሞነ ሕማማት በያላችሁበት!

ሚያዝያ 1/8/115 ዓ.ም
አዲስ አበባ