Get Mystery Box with random crypto!

በሰሞነ ሕማማት የሚጸለይ ጸሎት እና የማይጸለይ ጸሎት የቱ ነው? ሰሞነ ሕማማትን እንዴት ባለ ጾም | ቀሲስ ሄኖክ ወልደ-ማርያም

በሰሞነ ሕማማት የሚጸለይ ጸሎት እና የማይጸለይ ጸሎት የቱ ነው?

ሰሞነ ሕማማትን እንዴት ባለ ጾምና አመጋገብ እንድናሳልፍ ነው ቅድስት ቤተ-ክርስትያናችን የምታዘን?

በቀሲስ ሄኖከ ወልደ-ማርያም

ሼር በማድረግ ላላወቁት አሳውቁ፣ የተዘናጉትን አንቁ!

ተወዳጆች ሆይ በሰሞነ ሕማማት ብዙዎቻችሁ የሚጸለዩት እና የማይጸለዩት ጸሎቶች ጥያቄ እንደሚሆንባችሁ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ጥያቄ በተቻለኝ አቅም ለመመለስ እና እናንተም ተረጋግታችሁ አውቃችሁ ሕማማትን በስግደት ብቻ ሳይሆን በጸሎት እንድታሳለፍ ጥቂት ይህን እላሉ፡፡

በዚህ በሰሞነ ሕማማት አንዳንዶች ይህ አይጸለይም ይህ ይጸለያል እያሉ ምክንያቱን ሳያስረዱና ሳያውቁ ሲጽፉ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ ምዕምናኑን በጸሎት ዙርያ ጥያቄ እና ውዝግብ ውስጥ ይከታቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው በዚህ በሰሞነ ሕማማት የጌታችን ሕማም፣ ስቃይ፣ መከራ የሚታሰብበት እንጂ የሌሎችን የቅዱሳንን በዓላት አብረን የምናስብበት ጊዜ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእነሱ በዓል ከጌታ ሕማም፣ ስቃይ፣ መከራና ለሰው ልጆች ከከፈለው ውለታ አይበልጥምና፡፡ እንኳን እኛ በዚህ በሰሞነ ሕማማት በአጸደ ነፍስ ያሉትም ቅዱሳን የጌታን ሕማም የሚያስቡበት እንጂ የራሳቸውን ክብር የሚሹበት ጊዜ አይደለም፡፡

በሰሞነ ሕማማት ምዕመናኑ ከሚጸልየው ጸሎቶች ውስጥ ውዳሴ ማርያም፣ ዳዊት፣ ሰይፈ ሥላሴ፣ ሰይፈ መለኮት፣ አርጋኖን፣ ሰኔ ጎልጎታ፣ ትምህርተ ህቡአት፣ ድርሳነ ማሕየዊ፣ ድርሳነ መድኃኔ ዓለም ወዘተ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ከየት እንዳገኙት ባላውቅም ውዳሴ ማርያም እና ዳዊት ብቻ ነው የሚጸለየው ይላሉ፡፡ ግን ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጸሎቶች በሰሞነ ሕማማት ይጸለያሉ፡፡

በእርግጥ በሰሞነ ሕማማት የማይጸለዩ ጸሎቶች ተብለው ሳይሆን የሰሞነ ሕማማት ሥራዓት በዚህ ሳምንት የማያካትታቸው ጸሎቶች አሉ፡፡ እነሱም መልክዐ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ አይጸለዩም፡፡ ግን በግብረ ሕማማት ላይ አባ ጊዮርጊስ የደረሰው መልክዐ ሕማማቱ በዜማ ይጸለያል፡፡

ይህ የሚያሳየው የጌታን ሕማም በተመለከተ ለጌታ ሕማም የሚስማማ መልክዐ መጸለዩን ነው፡፡ በመልክዐ ኢየሱስ ላይ ‹‹ሰላም ለትንሣኤከ፣ ሰላም ለዕርገትክ›› የሚሉ ሰላምታዎች ወይም ምስጋናዎች አሉ፡፡ ስለዚህ እስከ አርብ የጌታን ትንሣኤና ዕርገት ሳይሆን ሕማማት ስለምናስብ ነው የማንጸልየው፡፡

እንዲህም በሰሞነ ሕማማት የመላእክት ድርሳናት እና የቅዱሳን ገድላት አጸለይም ወይም አይነበብም፡፡ ይህም የሆነው ቢጸለይ ነውር ኖሮበት ሳይሆን በሰሞነ ሕማማት ቅዱሳን መላእክትንና ቅዱሳን አባቶች እና እናቶችን በድርሳናቸው፣ በገድላቸው፣ በመልክዐቸው የምናስብበት ጊዜ ስላልሆነ ነው፡፡ ግን በግብረ ሕማማት ድርሳነ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እና ድርሳነ ስምዖን ዘአምድን ይነበባል፡፡

እንደሚታወቀው በሰሞነ ሕማማት ላይ የግዝት በዓላት ወይም ታላላቅ በዓላት ቢውሎ ሰሞነ ሕማማቱ ስለሚሽራቸው እነሱ እንኳን አይታሰቡም፡፡ ዋና አላማው በሰሞነ ሕማማት በቤተ ክርስትያናችን ብዙ መጻሕፍት ስለሚነበቡ ከጸሎታችን በሻገር የሚነበቡትን መጻሕፍት በነፍሳችን እያዳመጥን የጌታን ሕማም እንድናስብ ነው፡፡

ከላይ እንዳየነው መልክዐ ማርያም እና መልክዐ ኢየሱስ የማይጸለዩት እነዚህ ጸሎቶች የግል ብቻ ሳይሆኑ የማህሌት ምስጋናዎችም ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ በሰሞነ ሕማማት ማህሌት፣ ቅዳሴ ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ስለሌለ እነዚህ ጸሎቶች ለጊዘው አረፍ ይላሉ፡፡ ግን አርጋኖን፣ ሰይፈ ሥላሴ፣ ሰይፈ መለኮት፣ ሰኔ ጎልጎታ፣ ውዳሴ አምላክን በግል መጸለይ የሚከለክል ሥርዓት የለም፡፡

ያ የተረገመ መናጢ በየ ሰዉ እያደረ አጉል የቤተ ክርስትያን የሥርዓት ጠበቃ እየመሰለ፣ ሰሞነ ሕማማትን እየታከከ ከጸሎት ሕይወት እንዳያዘናጋን እንጠንቀቅ፡፡ ቢቻል በዓብይ ጾም የተዳከምን በዚህ ሳምንት በጸሎት እና በስግደት በመበርታት ልንጋደል ይገባናል፡፡ እንኳን ጸሎት ትተን እየጸለይንም ፈተናችንንና መከራችንን እኛ ነን የምናውቀው፡፡

በተረፈ ድርሳነ ማሕየዊ የማባለውን ስለ ጌታችን ሕማም፣ ስቃይ፣ መከራ በአስገራሚ ሁኔታ የሚነግረንን መጽሐፍ ገዝታችሁ ጸልዩት፡፡ ምንክያቱም ድርሳነ ማሕየዊን በሰሞነ ሕማማት ብቻ ሳይሆን የጌታን መከራ እና ውለታ እያሰበ አርብ አርብ ቀን የሚጸልየው

‹‹በነፍሱም በሥጋውም ይከብራል፣ በመንግሥተ ሰማያትም እድል ፈንታው ጽዋዕ ተርታው ጌታችንን ከገነዙት ከኒቆዲሞስ እና ከዮሴፍ ጋር ይሆናል›› እንዲሁም ‹‹በሰባቱ ጊዜያት የሚጸልየው ሰው ቢኖር በነፍሱም በሥጋው ፈጽሞ ይከብራል፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም እድል ፈንታው ጽዋዕ ተርታው እስከ ሰባ ዘመን ድረስ በየቀኑ የጌታውን መከራ እያሰባ ካለቀሰ ከጌታ ባለሟል ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ይሆናል›› የሚል ታላቅ ቃልኪ ኪዳን አለው፡

አራቱ ወንጌላውያንና ጌታችን የመከራውን ነገር ያስተማራቸው ኤልሳቤጥ፣ መልቴዳ እና በርዜዳ የጻፉትን ድርሳነ ማሕየዊን በመጸለይ የጌታን ሕማም ልናስብ እና ከቃል ኪዳኑ በረከት ልንሳተፍ ይገባናል፡፡ ድርሳነ ማሕየዊ ልክ እንደ ውዳሴ ማርያም የየእለት ወይም ከሰኞ እስከ እሑድ የተከፋፈለ በመሆኑ ለመጸለይ አይከብድም፡፡

በዚህ በሰሞነ ሕማማት እመቤታችን በልጇ የተሰነሳ ብዙ መከራ ደርሶባታልና፣ ጌታም በእሷ ሥጋ ተሰቅሏልና እሷን በውዳሴ ማርያም፣ በአርጋኖር፣ በሰኔ ጎልጎታ፣ በጸሎተ ባርቶስ ልናስባት ልናመሰግናት ይገባል፡፡ ሥላሴንም በሰይፈ ሥላሴ ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡ ጌታችንንም በሰይፈ መለኮት፣ በውዳሴ አምላክ፣ በዳዊት በድርሳኑ ልናስበውና ልናመሰግነው ይገባል እንጂ በሕማማት ምክንያት ከጸሎት ልንርቅ አይገባም፡፡

ሰሞነ ሕማማትን እንዴት ባለ ጾምና አመጋገብ እንድናሳልፍ ነው ቅድስት ቤተ-ክርስትያናችን የምታዘን? የሚለውን ስናይ በዚህ በሰሞነ ሕማማት የቤተ-ክርስትያናችን የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው የካህኑንም የምዕመናኑንም የሰሞነ ሕማማትን የጾም እና የአመጋገብ አክራሞት እንጠቀምበት ዘንድ፣ ጸጋና በረከት እናገኝበት ዘንድ ይደነግግልናል፡፡

ወዳጆቼ በዚህ በሰሞነ ሕማማት ፍትሐ ነገሥት በአንቀጽ 15 በቁጥር 578 ላይ ጨው ያለው ቂጣ እንድንበላና የእግዚአብሔር ውኃ እንድንጠጣ ያዘናል፡፡ እንዲሁም ፉት የማለት ልምድ ያለንን ሰዎችንም ‹‹በሊህ ቀኖች ከወይን ከሥጋ ተለዩ›› በማለት በጸሎት እንድንመሰጥ እንጂ መጠጥ እንዳንጨልጥ ያዘናል፡፡

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ሰሞነ ሕማማትን በቂጣና በውኃ የመጾም ጸጋና ልምድ ያለን ሰዎች ብንተገብረው ብዙ በረከት እናገኝበታለን፡፡ ልምዱና ጸጋው የሌለን ከሆነ ግን ጽኑ ግዴታ ውስጥ አንገባም፡፡ ቂም ቋጥረን፣ ነገር ሸርበን፣ ከወዳጃችን ተናቁረን፣ በሐሜት ተጨማልቀን፣ ስድብን በምላሳችን ተሸክመን እንኳን ቂጣ እየቆረጠምን ለምለም እንጀራ በጥሩ ወጥ እየበላን ባንጾም ይሻላል፡፡ ምክንያቱም አፋችንና ልባችን የማይገናኙበት፣ ቃሉና ተግባሩ የተራራቁበት ጾማችን ጾም ሳይሆን በረከት አልባ ልምድ ነው የሚሆነን፡፡

በሰሞነ ሕማማው ውስጥ ባለው የአክፍሎት ቀኖች እንደ መንፈሳዊ ልምዳችንና ብርታታችን በሁለት መልኩ በአማራጭ ያስቀምጥልናል፡፡ ይህንንም ‹‹ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊት ዶሮ ጩኸት ጊዜ ድረስ/እስከ ቅዳሴ ማብቅያ ድረስ/ ምንም ምንም አይቅመስባቸው፡፡ ሰውዬውም ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻል ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም›› በማለት አስቀምጦልናል፡፡