Get Mystery Box with random crypto!

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ ያሳለፈውን ውሳኔ በፌዴራል መ | Christian Tadele Tsegaye

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ ያሳለፈውን ውሳኔ በፌዴራል መንግስት ስምና በመከላከያ ሰራዊት የኃይል እርምጃ ለማስፈፀም የሚያደርገውን ፋሽስታዊ እርምጃ ሊያቆም ይገባል፤

ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ባለፉት አስርት ዓመታት በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታተ እጅግ አስከፊ በሆነ ርሀብና ጠኔ፣ ስደትና መፈናቀል፣ ማንነት ተኮር ጅምላ ግድያዎችና የዘር ፍጅቶች እንዲሁም በማያባሩ ግጭቶችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ይገኛሉ። ሕዝባዊ የፍትኅ፣ የእኩልነት፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሲበረቱበት የኢሕአዴግ አገዛዝ የሄደባቸውን የጥፋትና አገር የማፍረስ እኩይ ስምሪቶች የመንፈስ ግብር ወራሹ የሆነው ገዥው የብልጽግና ፓርቲም ዓይነትና መጠናቸውን አሳድጎ ቀጥሎባቸዋል። ፓርቲውና የፓርቲው አመራሮች በአመራር ስልታቸውና ብቃታቸው ላይ እንደአካልና ግለሰብ የሚቀርቡባቸውን ጥያቄዎችና ትቺቶች የብሔርና ኃይማኖት ቅርጽ በመስጠት ነቀፌታዎቹ የሆነ ብሔርና ኃይማኖት ላይ የቀረቡ በማስመሰል ወደለየለት ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ የዘር ፍጅት ቅስቀሳ ገብቷል። አገዛዙ ግጭትን እንደኅልውና ማስቀጠያ መሣሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል።
ለአብነትም የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመጋቢት፣2015 ዓ/ም የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀትን በተመለከተ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አገራችን ከነበረችበት አንፃራዊ መረጋጋት፣ ሰላምና ተስፋ መፈንጠቅ ወደ ትርምስ፣ ስጋትና የመበተን አደጋ ገብታለች። ይህንንም ተከትሎ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጎ እሳቤ ያላቸው ወገኖች ሁሉ ገዥው ፓርቲ የወሰነውን አስተውሎት የጎደለው ውሳኔ እንዲያጤነው ደጋግመው ቢወተውቱም ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚመስል ጎረምሳዊ ግብር ውሳኔውን የተቹ ንቁ ዜጎችን የመንግስት የፀጥታ መዋቅሮችን በመጠቀም ወደ ማፈን ተሸጋግሯል፤ የአገር መከላከያ ሰራዊቱንም ከሕግና ሕገመንግስታዊ መርሆዎች ባፈነገጠ መልኩ በፓርቲ ጥርነፋ በማስገባት በሕዝብና የክልል መንግስት መዋቅሮች ላይ በይፋ በማዝመት በንፁኃን ላይ ግድያና አፈናዎችን በመፈፀም ላይ ይገኛል።

በዚህም በ6ኛው ዙር ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ሆነን በእንደራሴነት የተመረጥን እኛ፦
1) የተከበሩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ
2) የተከበሩ ክርስቲያን ታደለ
3) የተከበሩ ሙሉቀን አሰፋ
4) የተከበሩ አበባው ደሳለው እና
5) የተከበሩ ዘመነ ኃይሉ

የብልጽግና ፓርቲ፤ በመረጠን ሕዝባችን ላይ እየፈፀመ ያለውን ፋሽዝም በጽኑ እያወገዝን፤የተፈፀሙ ሕገመንግስታዊ ጥሰቶቸንና መደረግ ያለባቸውን ምክረሐሳቦች እንደሚከተለው እናቀርበቀለን።

1) ብልጽግና ፓርቲ እንደሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሆኖ ሳለ፤ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ ያስተላለፈው ውሳኔ በየትኛውም የአገሪቱ ሕግ ለፓርቲው በሥልጣንነት ያልተፈቀደ ሆኖ አግኝተነዋል። የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ፓርቲው ሕገመንግስታዊ የመንግስትና ሕዝብ ተቋማትን እንደፓርቲው አደረጃጀት የቆጠረ፤ ለብቻው በፓርቲ ደረጃ በሕዝብና መንግስት ተቋማት ላይ አዛዥ ናዛዥ እንደሆነ አድርጎ ያቀረበ በመሆኑ ከሕግ፣ ሞራልና አሰራር አንፃር ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታጠቀ ኃይል ማንቀሳቀስ የማይችሉ መሆናቸውን የሚደነግገውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር የተመለከተውን አዋጅ ቁጥር 1162/2011 የተላለፈ ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይኸንኑ የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሕግ የጣሰ ውሳኔ በመርመር በፓርቲው ላይ ተገቢውን የሕግ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።

2) በኢፌዴሪ ሕገመንግስት የክልሎችን ሥልጣን በሚደነግገው አንቀጽ 52/2/ሰ ሥር «የክልሉን ፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሰላምና ፀጥታ ያስጠብቃል» በማለት ክልሎች የየራሳቸውን የፖሊስ ኃይል የማደራጀት ሕገመንግስታዊ መብት እንዳላቸውና አደረጃጀቱና አመራሩም በራሳቸው የሚወሰን መሆኑን በማያሻማ መልኩ ያስቀምጣል። የክልል ልዩ ኃይሎች በክልል መንግስታት ምክርቤቶች በኩል በአዋጅ የተቋቋመው የፖሊስ ኃይል አካል ሲሆኑ ተጠሪነታቸውም ለየክልሎቹ ፖሊስ ኮሚሽኖች ነው። ሰይጣን ላመሉ ከመጽሐፍ ያጣቅሳል እንዲሉ የብልጽግና ፓርቲ ክልሎች የመደበኛ ፖሊስ ብቻ ነው የተፈቀደላቸው የሚል የዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ሙግት ቢያቀርብም ቅሉ፤ እንደኃይማኖታዊ ቅዱስ መጽሐፍ በሚያመልከው የኢፌዴሪ ሕገመንግስት ውስጥ አንድም ቦታ መደበኛ ፖሊስ ብቻ ስለመፈቀዱ የሚያትት የሕግ ድንጋጌ የለውም። ይልቁንም በዚሁ ሕገመንግስት አንቀጽ 52/1 ላይ «ለፌዴራል መንግስት በተለይ ወይም ለፌዴራሉ መንግስትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን ይሆናል» የሚለው ድንጋጌ «የልዩ ኃይል ፖሊሰ» ማቋቋምን የክልሎች ልዩ መብት አድርጎ የሚያስቀምጥ ነው። የክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀት ሕገመንግስታዊ አይደለም ቢባል እንኳን በአንድ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ ሳይሆን ባቋቋሟቸው የክልል መንግስታት በኩል የማቋቋሚያ አዋጆቻቸው ማስተካከያ እንዲደረግበት ተደርጎ የሕግ ክፍተቱ  የሚታረም ሆኖ መሰል መብቶች ለክልሎች የተተው መሆናቸው ተጠየቅ የሚቀርብባቸው አይሆኑም።

3) የፌዴራል መንግስቱና የአገር መከላከያ ሰራዊት የአንድ ፓርቲ የግል ንብረቶች አለመሆናቸው እየታወቀ በተለይም በኢፌዴሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 87 ስለመከላከያ መርሆዎች በሚያትተው ንዑስ አንቀጽ 5 «የመከላከያ ሰራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል» የሚለውን ድንጋጌ በመጣስ እንዲሁም የአገር መከላከያ ሰራዊት በፖሊስ ሰራዊት በተለይም በክልሎች የፖሊስ አደረጃጀት ላይ ውሳኔ ለመስጠትና ማስተካከያ ለማድረግ የሕግ ሥልጣን ሳይኖረው በመረጠን ሕዝብና በራሱ በጀት በሚያስተዳድራቸው ሕዝባዊ ተቋማቱ ላይ የታወጀው ጦርነት የለየለት ፋሽስታዊ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። ጣልቃገብነቶችም በኢፌዴሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 51/14፣ 55/16 እና 62/9 መሰረት የተከናወኑ ባለመሆናቸው ግልጽ ሕገመንግስታዊ ጥሰቶችና አገር አፍራሽ ተልእኮዎች ናቸው።  የፌዴራል መንግስቱ በክልሎች ላይ በተለይም በአማራ ክልል እያደረገ ያለው ጣልቃገብነት የብልጽግና ፓርቲ በመቃብሬ ካልሆነ አልደራደርባቸውም የሚልላቸውን ፌዴራሊዝምና የኢፌዴሪ ሕገመንግስት ጭምር ገደል የከተተ ነው። በተለይም ሰራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገመንግስቱ ተገዥ መሆን እንዳለበት የሚደነግገውን አንቀጽ 87/4 ድንጋጌ የሻረ ነው።

በብልጽግና ፓርቲ የተፈፀሙ መሰል የአገር አፍራሽነት ሕገመንግስታዊ ጥሰቶችን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ የፌዴሬሽን ምክርቤትና መላው ኢትዮጵያውያን በጽኑ እንድታወግዙት ጥሪያችንን እናቀርባለን። በተለይ ሕገመንግስታዊ ሥርዓትን የመጠበቅና የማስጠበቅ የሕግ ግዴታ ያለባችሁ ተቋማት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ በመውሰድ የብልጽግና ፓርቲን አገር የማፍረስ እኩይ ተልእኮ ታስቆሙ ዘንድ በአጽንዖት እናሳስባለን።