Get Mystery Box with random crypto!

እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ፥ እንቁጣጣሽ ወገን! * በአገር ውስጥና በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን | Christian Tadele Tsegaye

እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ፥ እንቁጣጣሽ ወገን!
*
በአገር ውስጥና በመላው ዓለም ለምትገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለ2015 ዓ/ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሰን፤ አደረሳችሁ!

አዲሱ ዓመት፦
★በኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ በሐሳብ ልዩነት ምክንያት የጥይት ድምጽ የማይሰማበት፤ ኢትዮጵያውያንም በየትኛውም ልዩነቶቻቸው/ብዝኃነታቸው ምክንያት በጠላትነት የማይተያዩበት፣
★ሁሉም ፖለቲከኞች ከየራሳቸው ግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች በላይ ለአገር አንድነትና የሕዝብም ደኅንነት ቅድሚያ የሚሰጡበት፤ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይም አንድ ልብ መካሪ፥ አንድ ቃል ነጋሪ ሆነው የሚቆሙበት፣
★ኢትዮጵያውያን በሙሉ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የምንፈጥርበት፤ ለኢትዮጵያዊነታችንም የበለጠ ድምቀትን የምንሰጥበት፣
★ፈጣሪን ለማመስገን ካልሆነ በስተቀር ለምሬትና ለልመና አንድም ኢትዮጵያዊ እጆቹን የማይዘረጋበት፣
★ነጋዴው ነግዶ የሚያተርፍበት፤ ተማሪው ያሰበው የሚሳካበት፤ ምሁሩ ለአዳዲስ ፈጠራዎች የሚተጋበት፣
★አርሶና አርብቶ አደሩ የሰብሉን እሸት፥ የከብቱን ወተት የሚያጣጥምበት፣
★ኑሮ የሚረክስበት፤ ሰው የሚወደድበት፣
★ያላገቡ አግብተው ወግ ማእረግ የሚያዩበት፥ የተጋቡትም ልጅ ወልደው የሚስሙበት፣
★የታመመው ተፈውሶ፤ የተሰደደው ወደ እናት አገሩ ተመልሶ፤ ያዘነም እንባው ታብሶ የሚደሰቱበት፣
★እስረኞች የሚፈቱበት፤ እረኞች የሚቦርቁበት፣
★በየደረጃው ያሉ የሕዝብ አስተዳዳሪዎችና መሪዎች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው በቀናነት የሚተጉበት፣
★በተለይም የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ወገኖች ከጦርነት ቀጠና ወጥተው እፎይ የሚሉበት፣
★የእምነት ተቋማት ከጉንጭ አልፋ ክርክር፣ ጥልና መለያየት ስብከት ወደ መልካም ትብብር፣ አብሮነትና የጽድቅ ማማ የሚቀየሩበት፣
★አእዋፍት የሚዘምሩበት፤ ምንጮች የማይደርቁበት፤ ዛፎች የሚለመልሙበት፣
★ድርቅና ቸነፈር የማይኖርበት፤ ደዌ የተወገደበት፣
★እንደግለሰብም ሆነ እንደአገር የተለምናቸው በጎ ውጥኖች ሁሉ የሚሳኩበት፣
★ሰውንም ሆነ እግዚአብሔርን የምናስደስትበት፤ ለወገን ጠቅመን እኛም የምንጠቀምበት፣
★እንደአገርና ሕዝብ የዓለሙ መሳቂያ እና መሳለቂያ ከመሆን ወጥተን ዳግም ላንወድቅ በክብር ተነስተን በአንድነት የምንቆምበት፣

እኒህንና እኒህን መሰል በጎ ነገሮች ሁሉ ይዞልን እንዲመጣ፤ ለዚህም የየድርሻችንን በጎ ነገር ሁሉ ያለገደብ የምናበረክትበት ይሆን ዘንድ እመኛለሁ። በድጋሜ መልካም አዲስ ዓመት!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ልጆቿን አብዝቶ ይባርክ!