Get Mystery Box with random crypto!

ፍቅር እንደዚህ ነው በአንድ ወቅት የባቡር ሀዲድ መስመር ተቆጣጣሪ ሆኖ የሚሰራ አንድ ግለሰ | Maranatha Digital Network

ፍቅር እንደዚህ ነው

በአንድ ወቅት የባቡር ሀዲድ መስመር ተቆጣጣሪ ሆኖ የሚሰራ አንድ ግለሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰው የሚቆጣጠረው መንገድ... ባቡር ካልመጣ ከታች ለሚያልፉ መኪኖች ክፍት የሚደረግና ባቡር ከመጣ ለባቡሩ የሚዘረጋ ተታጣፊ መንገድ ነው፡፡ ይህም የዘውትር ምግባሩ ነው፤ የየዕለት ስራውን የሚሰራው ይኸው ሰው በአንዲት ቀን እንደተለመደው ማልዶ ተረኛ ስለነበር ወደ ሥራው ይሄዳል።

ቀትር ላይ የትምህርት ጊዜውን ጨርሶ ከአባቱ ጋር ወደ ቤት ሊመለስ የመጣው የሚወደውና እንደብሌኑ የሚሳሳለት በስትርጅናው የወለደው አንድ ልጁ ይመጣል። የሥራ መውጫ ሰዓቱ ገና ስለነበር ልጁን አንዲጫወት ነግሮት፤ ወደ ሥራው ይመለሳል። ከውጪ ሆኖ የሚጫወተውን ልጁን ትኩር ብሎ በመስኮት የሚመለከተው አባት ሀሳብ ወሰደው፤ ድንገት ከሀሳቡ ላይ የባቡር መምጣት ምልክት ደውል አስባነነው። በዚህን ጊዜ ለመወሰን ከባድ የሆነ ችግር ገጠመው፤ እየታጠፈ በሚዘረጋው መንገድ ስር ልጁ ይጫወት ነበር አሻግሮም ሲያይ ባቡር እየመጣ ነው፡፡ መንገዱን ካልዘረጋ ባቡሩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይሞታሉ ከዘረጋው ደግሞ ልጁ ሊሞትበት ነው፡፡ አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ያ የሚሳሳለትና የእርጅና ልጁ አይከለክለው ነገር ርቋል ባቡሩን እንዳያስቆመው እየፈጠነ ነው.....
የማጠፊያና የመዘርጊያውን አዝራር(Button) ይዞ ግራ እንደተጋባ ቆሞ ነው ያለው... አሁን ባቡሩ እየቀረበ ነው አዝራሩን ካልተጫነ ስለነገሩ የማያውቁት ማለቃቸው ነው በዚህም ተጨነቀ በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሁና ምስኪኑ ልጁ አለ። በዚህን ጊዜ መወሰን ግድ ሆነበት፤ እያነባና እያዘነ አንድ ውሳኔ ለመወሰን ተገደደ ይህም ውሳኔ ልጁ ላይ ስለነዚያ ባቡሩ ውስጥ ስለሚገኙት ያባትዬውን ጭንቅ ስለማያውቁት አዝራሩን(Button) በመጫን ተሳፋሪዎቹን ማዳን ሆነ፡፡ በብዙ ጭንቅ ሆኖ አዝራሩን ተጫነ፤ መንገዱም ተዘርግቶ ብቸኛ ልጁን ጨፈለቀው። ባቡሩም ውስጥ ያሉት የተደረገላቸውን ሳያውቁ በልጁ ሞት ተሻገሩ። ባቡሩ እንደተሻገረ ሰውዬውም የልጁ አስክሬን ወዳለበት ሮጠ ደርሶም የልጁን አጥንትና ደም እየደባበሰ ማልቀሱን ተያያዘው። ዳሩ ግን በባቡሩ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ባቡሩ በልጁ ላይ ተረማምዶ ሲሻገር ለነበረው መንገራገጭ ትኩረት ሰጡ። ያ ልጁን ያጣው አባት ግን ያውቀዋል ስቃዩን ዋጋውን፡፡

ዛሬ እኛም ብንሆን እንደ ባቡር ተሳፋሪዎቹ በእግዚአብሔር ፍቅር በልጁ ሞት ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሻገርን ሰዎች ነን፡፡ የዳንነው በነጻ ቢሆንም ዋጋው ውድ አባትና ልጅ የሚያውቁት ስቃይ ነው።

ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።”
—1ኛ ዮሐ.4:10


.Maranatha Digital Network. @Maranatha_Fellowship @Maranatha_Fellowship2