Get Mystery Box with random crypto!

+++ ‹‹ይህም ያልፋል›› +++ +++ አንድ ንጉሥ አማካሪዎቹን ሰበሰበና እንዲህ ሲል አዘዛቸው፡ | እምነ ጽዮን መንፈሳዊ ማህበር

+++ ‹‹ይህም ያልፋል›› +++

+++ አንድ ንጉሥ አማካሪዎቹን ሰበሰበና እንዲህ ሲል አዘዛቸው፡፡ ‹‹ስከብርም ሆነ ስዋረድ፣ ሳገኝም ሆነ ሳጣ፣ የሁሉም የበላይ ስሆንም ሆነ የበታች፣ እጅግ ስደሰትም ሆነ ስከፋ፣ ድል ሳደርግም ሆነ ድል ስሆን፣ ዝናዬ ሲናኝም ሆነ ሲከስም፣ ያንን ነገር በሰላምና በጥበብ እንዳልፈው የሚያደርግ አንድ ዐረፍተ ነገር ስጡኝ፡፡ ላስታውሰው የምችል፣ መንገዱንም የሚመራኝ፣ ከልክ አልፌ እንዳልሄድ፣ ከልክ ወርጄም እንዳልወድቅ፣ የሚያደርግ አንድ ዐረፍተ ነገር አምጡልኝ፡፡ የተወሳሰብ ፍልስፍና አልፈልግም፣ ቀላልና ግልጽ የሆነውን እሻለሁ፡፡ ይህንን ሳትይዙ እንዳትመለሱ››
አማካሪዎቹ ከቤተ መንግሥቱ ወጥተው ለአራት ወራት ያህል መከሩ፡፡ አነሡ ጣሉ፤ በመጨረሻም የደረሱበትን ሐሳብ በብራና ጽፈው ወደ ንጉሡ ዘንድ መጡ፡፡ የተጠቀለለውንም ብራና ሰጡት፡፡

+++ ንጉሡም ገለጠና አነበበው፡፡ እንዲህ ይል ነበር ‹‹ይህም ያልፋል››፡፡ ለምን? አላቸው ንጉሡ፡፡ በየትኛውም የሥልጣንና የሀብት ከፍታ ላይ ብትሆን፣ በየትኛውም የዝናና የክብር ሠገነት ላይ ብትደላደል፣ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ግፍ አትሠራም፣ ፍትሕ አታዛባም፣ ድኻ አትበድልም፣ ከልክህም አታልፍም፡፡ ራስህን ዘላለማዊ አድርገህ ካሰብክ፣ ጊዜ የማይቀየር ዓለምም የማትዞር ከመሰለህ ግን ራስህን ለማስተካከል እንኳን ጊዜ ሳታገኝ ነገሮች ይቀየሩና በሠራኸው ወኅኒ ትወረወራለህ፣ ባወጣኸው ሕግ ትቀጣለህ፣ በቆረጥከው ዱላ ትመታለህ፣ ባሳደግከው ውሻ ትነከሳለህ፡፡ ስለዚህ አሁን የተቀመጥክበትን ዙፋን፣ የምታንቀጠቅጥበትንም ሥልጣን፣ ‹ይህም እንኳን ያልፋል› ብለህ አስበው፡፡

+++ ተቀናቃኞችህን ድል እንዳደረግክ፣ አገሩን ጠቅልለህ እንደያዝክ፣ ሁሉ በእጅህ ሁሉ በደጅህ እንደሆነ፣ በለስ እንደቀናህ፣ አንደኛ እንደወጣህ፣ እንደ ተጨበጨበልህ ፣ እንደታፈርክና እንደተከበርክ፣ አትቀርም፡፡ ይህም በጊዜው ያልፋል፡፡ እነዚህ ዛሬ በዙሪያህ ሆነው የሚያፍሱልህ የሚያጎነብሱልህ፣ ሳታስነጥስ ይማርህ፣ ሳትወድቅ እኔን የሚሉህ፤ ሳይበርድህ ካልደረብንልህ ሳታዝን ካላለቀስንልህ የሚሉህ፤ ሳትጠራቸው አቤት፣ ሳትልካቸው ወዴት የሚሉህ፣ ይኼ ሁሉ ሲያልፍ ያልፋሉ፡፡

+++ ካንተም በፊት ሌሎች ነበሩ፣ ካንተም በኋላ ሌሎች ይመጣሉ፡፡ ከፊትህ ሌላ ባይኖር ኖሮ ከኋላህ ሌላ ባልመጣም ነበር፡፡ በጊዜ ውስጥ ትናንት ዛሬና ነገ አሉ፡፡ ዛሬ ትናንት፣ ነገ ዛሬ እየሆኑ ያልፋሉ፡፡ አንተ ሌሎችን እንደተካህ ሁሉ የሚተካህም የግድ ይመጣል፡፡ አንተ ሌሎችን እንደረታህ ሁሉ የሚረታህም ነገ ይመጣል፡፡ አንተ ሌሎችን እንዳሠርክ ሁሉ የሚያሥርህም ነገ ይመጣል፡፡ አንተ እንደቀበርክ ሁሉ ቀባሪህም ነገ ይመጣል፡፡ እስኪ ለቀስተኞችን እይ፤ የዛሬ ቀባሪ ሁሉ ነገ በተራው ተቀባሪ ነው፡፡ ማንም ራሱን የሚቀብር የለም፡፡ ሌላውን እንደቀበረ ሁሉ እርሱን ሌላ ይቀብረዋል እንጂ፡፡ ‹ይህም ሁሉ ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ሁሉን በልኩ፣ ሁሉን በደንቡ ታደርገዋለህ፡፡

+++ የሌሎችን ታሪክ አጥፍተህ፣ የሌሎችን ሐውልት ሰብረህ፣ የሌሎችን ዋጋ አርክሰህ፣ የሌሎችን ስም ገድለህ መኖር ትችላለህ፤ ዐቅሙና ሥልጣኑ እስካለህ ድረስ፡፡ ነገር ግን ይህም ያልፋል፡፡ ያንተንም ታሪክ የሚያጠፋ፣ ያንተንም ሐውልት የሚሰብር፣ ያንተንም ስም የሚያጎድፍ፣ ያንተንም ዋጋ የሚያረክስ በተራው ይመጣል፡፡ የሚተካህን የምትፈጥረው ዛሬ በምታደርገው ተግባር ነው፡፡ ክፉ ከሆንክ ክፉ ይተካሃል፣ ርቱዕ ከሆንክ ርቱዕ ይተካሃል፡፡
+++ ይኼ ሁሉ ዓለም አልፎ ብትወድቅ፣ ብትሰበር፣ ብትታሠር፣ ብትረሳ፣ ብትሰደድ፣ ብታጣ፣ ብትነጣ፣ ከላይ ወደታች እንዳየኸው ሁሉ ከታች ወደ ላይ የምታይበት ዘመን ቢመጣ፣ ያሰብከው ቀርቶ ያላሰብከው ቢሆን፣ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ አስብ፡፡ ‹ይህም ያልፋል› ብለህ ካሰብክ ተሥፋ አትቆርጥም፣ ነፍስህ ሳትወጣ አትሞትም፣ ራስህን ለብስጭትና ንዴት፣ ለቁጣና ትካዜ አሳልፈህ አትሰጥም። የሥልጣን ጫፉ መውረድ እንደሆነው ሁሉ የውርደት ጫፉ ሥልጣን ነው፡፡ የብርሃን ጫፉ ጨለማ፣ የጨለማም ድንበሩ ብርሃን ነው፡፡ የበሽታ ጫፉ ጤና፣ የጤናም ጫፍ በሽታ ነው፡፡ ዓለም ቋሚ አይደለችም፡፡ ጊዜ ወደ ፊት ብቻ ነው የሚሄደው፡፡

+++ እሥር ቤቱ ሲተከል የነበሩት አሁን የሉም፤ ስለዚህም አንተም እዚያ እሥር ቤት አትኖርም፡፡ ችግር ሲጀመር የነበሩት አሁን የሉም፤ አንተም ችግር ውስጥ የግድ አትሰምጥም፡፡ እንደሚያልፍ ካመንክ፡ ለማሳለፍ ትጥራለህ፡ እንደሚያልፍ ካላመንክ ግን ያለህበትን ትቀበለዋለህ፡፡...ይህም ያልፋል...!!!

ሀቁ ይህ ነው አንተምጋ ያለው ያልፋል።

❖ ወስብሐት ለእግዚአብሔር
❖ ወለወላዲቱ ድንግል
❖ ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን።
አሜን
እምነ ጽዮን መንፈሳዊ ማሕበር