Get Mystery Box with random crypto!

ቅዱስ ፓትርያርኩ ምን አሉ ? ዛሬ በአዲስ አበባ ' ጃንሜዳ ' ባሕረ ጥምቀት በነበረው የጥምቀት | ማኅበረ ቅዱሳን ( Mahibere Kidusan)

ቅዱስ ፓትርያርኩ ምን አሉ ?

ዛሬ በአዲስ አበባ ' ጃንሜዳ ' ባሕረ ጥምቀት በነበረው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልዕክት አስተላልፈው ነበር።

ከቅዱስነታቸው መልዕክት መካከል የሚከተለው ይገኝበታል ፦

" ... እኛን የላከ እግዚአብሔርም ሆነ፣ ከሱ የተላክን እኛ ለሰው ልጆች ሁሉ የምናስተላልፈው መልእክት “ንስሐ ግቡ” የሚለው ነው፡፡

በእውነት ንስሐ ከገባን ጠቡ፣ ግድያው፣ ዘረፋው፣ መለያየቱ ይቆማል ፤ በምትኩ ደግሞ ፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነት ይሰፍናል፤ መከባበር፣ መተማመን፣ መስማማትና ይቅር ባይነት የበላይነቱን ያገኛል፤ ውጤቱም ሰላምና ዕድገት ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን ቃል የምትሰማ ነፍስ ካለች እኛ የምንነግራት ይኼና ይኼ ብቻ ነው።

ከንስሐና ከፍቅር ውጭ በእግዚአብሔር ስም የሚናገር መልእክተኛ ካለ እሱ የእግዚአብሔር መልእክተኛ አይደለም፤  እባካችሁ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች የእግዚአብሔርን ቃል በሰላምና በሰላም ብቻ ለሕዝቡ እናድርስ፤ ሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ሰምቶ ለሰላም ይታዘዝ፡፡

ሌላው የጥምቀት በዓል ዋና መልእክት “ያለው ለሌለው ያካፍል” የሚለው ትእዛዘ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ወገኖቻችን ሕፃናት፣ እናቶች፣ እኅቶችና አረጋውያን በረኃብ ተቈራምደው ዕለተ ሞታቸውን ሲጠብቁ እያየን ነው፡፡

ወገኖቻችን በረኃብ እንዲህ እየሞቱ #እንደባዕድ ዝም ብለን የምናይ ከሆነ ክርስቲያንነቱ ጥያቄ ውስጥ አይገባምን ? ስለሆነም ኢትዮጵያውያንም ሆን የዓለም ማኅበረ ሰብ በሙሉ በጽኑ ረኃብ ለተጠቃው ሕዝባችን እጃቸውን እንዲዘረጉ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ጥያቄያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር በዚሁ ዕለት እኛን ለመቀበል ሰማያዊ በሩን እንደከፈትልን እኛ ኢትዮጵያውያንም አእምሮአችንን ከፍተን ለመረዳዳት ለሰላም፣ ለፍቅር ለይቅርታ ለአንድነትና ለእኩልነት ተጠቃሚነት በርትተን እንድንሰራ ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላፋለን፡፡ "

(ሙሉ መልዕክታቸው ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia