Get Mystery Box with random crypto!

__ወደ_ውስጥ ዝናብ ይቀጥቅጠኝ፤ በረዶውም ይውረድ ፀሀይም ያቃጥለኝ፤ ሰውነቴን ያንድድ፣ ናፍቆት ያ | ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን📖

__ወደ_ውስጥ
ዝናብ ይቀጥቅጠኝ፤ በረዶውም ይውረድ
ፀሀይም ያቃጥለኝ፤ ሰውነቴን ያንድድ፣
ናፍቆት ያስቃየኝ፤ እድሜም ይሩጥ ይለፍ፤
ሆዴን ይቦርቡረው፤ አንጀቴም ይንሰፍሰፍ፣

በሩቅ ፍቅር ራብ፤ ልታረዝ ልጠማ፣

ይንከራተት ልቤ፤ በሃሳብ ቁዘማ።

 

            ምስክር ባልሆንም፤ አጠገብሽ ሆኘ፣
            በክፉ በመጥፎ፤ ስምሽ እየናኘ
            ሃዘንሽ በርትቶ፣
            ጣርሽ ተበራክቶ፣
            የልጅ ያለህ ስትይ፤ ጆሮየ እየሰማ፣
            ፍቅርሽ ሆዴ ቀርቷል፤ ውስጤን እያደማ።
            ከጉያሽ ባልሆንም መከራሽ ሲበዛ፤
            ስቃዩ ውስጤ አለ ተቅምጧል በዛ።

 

ጉዳትሽ፣ ውርደትሽ፤ ሀዘን ሆነ ደስታ

ይደርሳል፣ ይመጣል፤ ካለሁበት ቦታ።

     ሰዎች ተገደሉ፣ ልጆችሽ ተራቡ፣

     ወጣቶችሽ ሁሉ፤ በከርቼሌ ገቡ፣

     ሙስናው በረታ፣ መብቶች ተጣሱ

     ጎሳ ተንሰራፋ፣

     ማንነትሽ ጠፋ፤

     አንችነትሽ ከፋ፤

     ፍቅር ረከሰ፣

     መተማመን ጠፍቶ፤ ፍራቻ ነገሰ።

 

ሁሉም ይዳረሳል፣ በወሬ ነጋሪ

ይመጣል ሰንጥቆ ባህርን ተሻግሮ

ነፋስንም ቀዝፎ፣ ባየር ተወርውሮ።

 

እጅግ ያሳቅቃል፤ ከርቀት ሲሰማ

ይቅርብኝ አይሉት ያንችን ነገርማ።

መዳኒት የሌለው፤ ፈውስ አይገኝለት፣

ተስፋ ብቻ ቋጥሮ አሻግሮ መመልከት።

የስቃይ ተካፋይ፣ የታሪክ መስካሪ

ሆኖ አለመገኘት፤ ያማል ውሰጥ ያደማል፣

ስቃይን ያበዛል፣ ወደ ውስጥ ይፈሳል።

 

          ግና

         

          ግና ከጎንሽ ነኝ የቅርብ ሩቅ ሆኜ

          ባህር ተሻግሬ ለመኖር ወስኜ

          ሲያምሽም ልታመም፤ ስት’ቆስይም ልቁሰል

          ላ’ይንሽ እስኪያበቃኝ ስቃዩ ይከመር

          ራብሽ ይሰማኝ፤ ጠግቤ ልታረዝ፣

          የሆንሽውን ሳልም ባሳብ ልጠማዘዝ።

ግና

 

ግና እነግርሻለሁ… ስትጮሂ እጮሃለሁ

የስቃይሽን ልክ ላ’ለም አሰማለሁ።

 

ዝናብ ይቀጥቅጠኝ፣ በረዶውም ይውረድ
ፀሀይም ያቃጥለኝ፣ ሰውነቴን ያንድድ፤
ናፍቆት ያስቃየኝ፣ እድሜም ይሩጥ፤ ይለፍ
ሆዴን ይቦርቡረው፣ አንጀቴም ይንሰፍሰፍ።…

 

ውስጤን በመሃላ ካንቺው አጣብቄ፤

ላልከዳሽ፣ ላልረሳሽ፤ ቃሌንም ጠብቄ

ልኖር ወስኛለሁ ከጉያሽ ርቄ።

 

ተጠናቀቀ ሴፕቴምበር 26/2014 8፡33
#ከወደዱት_ለወዳጆ
#From
@lorate_tsegaye_gebremedihen
@lorate_tsegaye_gebremedihen
@lorate_tsegaye_gebremedihen