Get Mystery Box with random crypto!

' ከአሸባሪነት መሰረዙን በፅኑ እቃወማለሁ ' - ኢዜማ ኢዜማ የህወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ ' | LEYU NEWS

" ከአሸባሪነት መሰረዙን በፅኑ እቃወማለሁ " - ኢዜማ

ኢዜማ የህወሓትን ከአሸባሪነት መሰረዝ " በፅኑ እቃወማለሁ " አለ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህ.ወ.ሓ.ት ከሽብርተኝነት መሰረዝን በተመለከተ ውሳኔውን በመቃወም መግለጫው  አውጥቷል።

በዚህ መግለጫው ፤ " ህወሓትን ከሽብርተኝነት መሰረዝ ዘላቂ ሰላምን፣ እፎይታንና ቅቡልነትን የሚያመጣ አይደለም " ብሏል።

ፓርቲው የ " ህወሓት " ን ከሽብርተኝነት መሰረዝ የተቃወመባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ያሳወቀ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ፦

- ህወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 6 መሠረት ትጥቅ ሙሉ በሙሉ አልፈታም።

- በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የትግራይን የሽግግር መንግሥትን የፌደራሉ መንግሥት በበላይነት እንዲያቋቁም ስምምነት ላይ ቢደረስም አሁንም ህወሓት በብቸኝነት የሽግግር መንግሥቱ አውራ ሆኗል ፤ ይኽም ህወሓት ዳግም የሀገር ስጋት የሚኾንበትን ዕድል እንደመስጠት የሚቆጠር ነው።

- በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያዘዙ፣ ሰብዓዊ ቀውስ ያደረሱ፣ ዜጎችን በጦርነት እንዲማቅቁ ያደረጉ፣ የሀገር ኢኮኖሚና፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ የከተቱ የሕወሓት አመራሮች በሕግ አልተጠየቁም።

- በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ትግራይን እንዲቆጣጠር አልተደረገም።

- የተጨፈጨፉ የሰሜን ዕዝ አባላት የመስዋዕትነት ምልክት የሚኾን ሐውልት ወይም ማስታወሻ በሰሜን ዕዝ ዋና ማዘዣ አልተደረገም።

- በህወሓት ቆስቋሽነት ሀገራችን ላይ ለደረሰው ውድመትና ሰቆቃ ፍትሕ እና ካሣ አልተሰጠም የሚሉት ይገኙበታል።

ኢዜማ ህወሓት የሚለው የፖለቲካ ድርጅት ስም በሕግ እንዲታገድ አለመደረጉ ከላይ የተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ቡድኑ ከሽብርተኝነት ሰርዞ ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ሊቀለበስ የማይችል ጥፋት ነው ብሏል።

ከዚህ በኋላ በ " ህወሓት " አማካኝነት ለሚደርስ ሀገራዊ ጉዳትም ዋነኛ ተጠያቂዎች ገዢው " የብልጽግና ፓርቲ እና መንግሥት " እንደሚኾኑ ከወዲሁ እንገልጸለን ሲል አሳውቋል።

ምክር ቤቱ ሌላው ቢቀር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ግዴታዎች አየተፈፀሙ መሆኑን በቅጡ ሳያረጋግጥ፣ ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ ለፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል ተጠያቂ ሳይሆን እና በህወሓት የእብሪት ጦርነት የግፍ ገፈት ቀማሽ ለሆኑ በተለይ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ለሚገኙ ወገኖቻችን ፍትሕ ሳይሰጥ ቡድኑን ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዝ መወሰኑ ታሪክ ይቅር የማይለው ፍርደ ገምድልነት  ሲል ውሳኔውን አውግዟል።

ሕወሓት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን በመጨፍጨፍ የሀገር ክህደት ፈጽሟል ያለው ኢዜማ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተው ጦርነት እና እሱን ተከትሎ ለደረሰው ሀገራዊ ቀውስ ቁጥር አንድ ተጠያቂ ህወሓት ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

@Leyu_News
@Leyu_News