Get Mystery Box with random crypto!

ሐምሌ 7 ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ቤት የ | ልሳነ ግእዝ ለኩልነ

ሐምሌ 7

ቅድስት ሥላሴ በአብርሃም ቤት

ሐምሌ ሰባት በዚች ቀን ሥሉስ ቅዱስ በአብርሃም ቤት የተገለጠበት ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስትነት በባሕርይ በሕልውናና በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ተገኙ፣ በዚህ ጊዜ ያልፋሉ አይባሉም መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና፡፡ ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት ‹‹ቅድስት ሥላሴ›› እንላቸዋለን፡፡
የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም፡፡ የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል፣ በቤቱም መጥተው ያድራሉ፡፡ ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም፡፡ አባታችን ቅዱስ አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል፡፡

አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ ሥላሴን በድንኳናቸው አስተናገዱ፡፡ አብርሃም እግራቸውን አጠበ፡፡ በጀርባውም አዘላቸው፡፡ ምሳቸውንም አቀረበላቸው፡፡ እነርሱም እንደሚበሉ ሆኑለት፡፡ በዚያው ዕለትም የይስሃቅን መወለድ አበሠሩት፡፡ አብርሃም ከደግነቱና እንግዳ ከመውደዱ የተነሣ በተመሳቀለ ጎዳና ላይ ድንኳን ሠርቶ የወጣ የመረደውን፣ የመጣ የሄደውን ሁሉ እየተቀበለ እግዚአብሔርን እያገለገለ የሚኖር ጻድቅ ነበር፡፡
ለዚህም ነው አብርሃም በወይራ ግራር (በመምሬ) ዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠለት፡፡ ዘፍ 18፡1-25፣ ሮሜ 4፡-3፡፡ ቀትር ሰዓት ላይ በድንኳኑ ደጅ ተቀምጦ እንግዳ ሲጠብቅ እግዚአብሔር ታየው ተነጋገረው፡፡ አንገቱን ቀና አድርጎ ዐይኑን አራምዶ በተመለከተ ጊዜ እነሆ ሦስት ሰዎች ከበላዩ ባለ ተራራ ላይ ቆመው አያቸው፣ ወደ እርሱም ሲወርዱ አይቶ ፈጥኖ ሄዶ ከሰግደላቸው በኋላ ‹‹አቤቱ በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ፤ ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ…›› እያለ በትሕትና በመጋበዝ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ በሚገባ ጋበዛቸው፡፡ ‹‹በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ›› ብሎ አንድነታቸውን፣ ‹‹ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ እግራችሁን ታጠቡ›› ብሎ የሦስትነታቸውን ምስጢር ገልጾአል፡፡

ያች ሥላሴ የገባባት የአብርሃም ድንኳን የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡፡ ሥላሴ ወደ አብርሃም ድንኳን እንደገቡ ሁሉ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም አብ ለአጽንዖ፣ መንፈስ ቅዱስ ለአንጽሖ፣ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋዋን ለመዋሐድ የማደራቸው ምሳሌ በመሆኑ አማናዊቷ የሥላሴ ማደሪያ የአብርሃም ድንኳን እመቤታችን ናት፡፡ ሉቃ 1፡35፡፡

እግዚአብሔርም አብርሃምን የዛሬ ዓመት ልጅ እንደሚወልድ ነግሮት በዓመቱ ይስሐቅን ወልዷል፡፡ ሁለቱ ሰዎች ከአብርሃም ድንኳን ወጥተው ወደ ሰዶም ወደ ገሞራ ሄዱ፣ አብርሃምም ይሸኛቸው ዘንድ አብሯቸው ሄደ፡፡ የሄዱትም ሁለቱ ሰዎች አብና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወልድ በአብርሃም ቤት ቀርቷል ይኸውም ከቤተ አብርሃም ሰው እንደሚሆን ለማጠየቅ ነው፡፡ አብርሃምም ተመልሶ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፡፡ እግዚአብሔርም የሚሠራውን ሁሉ ከአብርሃም አይሠውርም ነበርና የሰዶምን የገሞራን ጥፋት ነገረው፡፡ አብርሃምም ይቅር እንዲላቸው አብዝቶ ለመነላቸው፡፡ ሥሉስ ቅዱስን የአብርሃሙ ሥላሴን በምግባር በሃይማኖት ሆነን እናገለግል ዘንድ የቅዱሳኑ ጸሎት ይርዳን!

የእኛንም ጓዳ ጎድጓዳ አጋዕዝት ዓለም ቅድስት ሥላሴ በምህረቱ የጎብኝልን አሜን

ምንጭመጽሐፈ ስንክሳር ዘተዋሕዶ


አቅራቢ ፦ ✞ኦርቶዶክሳዊ መጽሐፍት

የግእዝ ትምህርት በyoutube
https://youtube.com/channel/UCbuXpsXU7hDaFWELjzHlxdg

➮ከወደዱት ያጋሩ
share & join
𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆  
@Orthodox_Addis_mezmur
@orthodox_spiritual_poems
@Eotc_Books_By_Pdf
@Lesangeez128
𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆