Get Mystery Box with random crypto!

[ዕለተ ዐርብ የመድኀኔ ዓለም ስቅለት] በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት የተደረገ] (ነ | አሚነ ፅድቅ✨

[ዕለተ ዐርብ የመድኀኔ ዓለም ስቅለት]
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት የተደረገ]
(ነገረ ክርስቶስ ከሚለው መጽሐፌ በጥቂቱ የተወሰደ)
ጌታችን ዓለምን ለማዳን በቀራንዮ በመስቀል ላይ ከምድር ከፍ ከፍ ብሎ ስለምን ተሰቀለ? ቢሉ:-
“እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኲሎ ኀቤየ” (ከምድር ከፍ ከፍ ባልኊ ጊዜ ኹሉን እስባለኊ) ብሎ ነበርና ይኽነን ሊፈጽም ነው (ዮሐ ፲፪፥፴፪)፡፡

ዳግመኛም ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉ “ኅሩይ ማእከለ እግዚአብሔር ወሰብእ” እንዲል አምላክ ወሰብእ ኾኖ እንዳስታረቀን ለማጠየቅ፡፡

በመጨረሻም ምድርን በኪደተ እግሩ እየተመላለሰ እንደ ቀደሳት፤ ዐየራትን ደግሞ ሥብ እያጤሱ አስተራኲሰውት ነበርና አየራትን ለመቀደስ ነው፡፡

ንጹሐ ባሕርይ ጌታችንን አይሁድ መስቀሉን አሸክመው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ከወሰዱት በኋላ ኹለት ወንበዴዎችን በቀኝና በግራ አድርገው ጌታችንን በመኻከል ሰቅለውታል (ማቴ ፳፯፥፴፰)፡፡

በትርጓሜ ወንጌል እንደታተተው ክፉዎች አይሁድ ይኽነን ያደረጉበት ምክንያት በክፋት ነው፤ ይኸውም በቀኝ የሚመጡ ሰዎች በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት፤ በግራ የሚመጡ ሰዎች በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ አይተው “ይኽ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ወንበዴ ነው” ይሏቸዋል፤ ከዚያም ጌታን “ይኽስ ምንድነው?” ብለው ሲጠይቁ “ይኽስ ከርሱ ልዩ ነውን አንድ ነው እንጂ” ብለው ሰዎችን ለማሳሳት ያደረጉት ነው፡፡

ዳግመኛም አነገሥንኽ ብለውታልና ቀኛዝማች ግራዝማች ሾምንልኽ ለማለት ለመዘበት፡-
በተጨማሪም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕ ፶፫፥፲፪ ላይ “ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሯልና” የሚለው ትንቢቱን ሊፈጽም ሲኾን ምስጢሩ ግን እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጥሯል፤ ሌላውም በዕለተ ምጽአት እኛን ኃጥኣንን በግራ ጻድቃንን በቀኝ ታቆማለኽ ሲያሰኛቸው ነበር (ማቴ ፳፭፥፴፫፤ ራእ ፩፥፯)፡፡

ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲገልጹ፡- “ወሰቀልዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ዲበ ዕፀ መስቀል እንዘ ገጹ መንገለ ምሥራቅ ወእዴሁ ዘየማን መንገለ ደቡብ ወእዴሁ ዘፀጋም መንገለ ሰሜን…” (ጌታችን ኢየሱስንም በዕንጨት መስቀል ላይ ሰቀሉት፤ ፊቱን ወደ ምሥራቅ ቀኝ እጁን ወደ ደቡብ፤ ግራ እጁን ወደ ሰሜን አድርገው ሰቀሉት … ከርሱም ጋር ኹለቱን ወንበዴዎች አንዱን በቀኝ አንዱን በግራው በመኻከላቸው ጌታችን ኢየሱስን አድርገው ሰቀሉ፤ ሕዝቡም ርሱም እንደነርሱ ወንበዴ ነው ይሉት ዘንድ ሰቀሉት፤ ርሱ ግን ወድዶ ከወንበዴዎች ጋር በዕንጨት መስቀል ተሰቀለ፤ ልዑላን መላእክት ፈርተው በፊቱ ራሳቸውን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉለት ርሱ በሚሰቅሉት ፊት ራሱን ዝቅ አደረገ (ፊልጵ ፪፥፲፤ ራእ ፬፥፲-፲፩)።

በከሃሊነቱ ሰማይና ምድርን ያጸና ከግርማውም የተነሣ ሰማያትና ምድር የሚንቀጠቀጡለትን ርሱን ደካማ ዕንጨት ተሸከመው (ምሳ ፴፥፬፤ ኢሳ ፵፪፥፭)፤ ርሱ ግን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ከራሱ ያስታርቀን ዘንድ ከሰማይ ዝቅ ብሎ ከምድር ከፍ ብሎ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ርሱም ስለእኛ በሥጋው በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ከኀጢአታችን ይለየን ዘንድ በቸርነቱ ያድነን ዘንድ ተሰቀለ (፩ጴጥ ፪፥፳፬)።

ርሱ ግን ሰማያትን ይቀድስ ዘንድ በአየር ያሉ አጋንንትን ያወርዳቸው ዘንድ በዕንጨት መስቀል ላይ ተሰቀለ፤ ሙሴ አርዌ ብርትን በገዳም እንደ ሰቀለው ርሱም በዕንጨት ላይ ተሰቀለ ፤ በርሱ ያመነ ኹሉ ይድናል እንጂ እንዳይጐዳ የክብር ባለቤት ርሱ ግን ስለ እኛ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ (ዮሐ ፫፥፲፬-፲፭)፤

አውቀውስ ቢኾን የክብር ባለቤት ጌታን ባልሰቀሉት ነበር (፩ቆሮ ፪፥፰)፤ ሰማይ ዙፋኑ ሲኾን ምድርም በእግሮቹ የተረገጠች ስትኾን ስለኛ በዕንጨት ተሰቀለ (ኢሳ ፷፮፥፩)፤ ርሱ ግን ተጠብቆለት ስላለ ስለ ደስታው የመስቀልን መከራ ንቆ አቃልሎ ተቀበለ ኀፍረትንም ናቃት፤ ለተሰቀለው ለርሱ የማይሰግድ ቢኖር የተለየ የተወገዘ ይኹን (ፊልጵ ፪፥፰-፲፩)፤ ርሱ ግን ስለ ዓለሙ ደኅንነት በማእዝነ ምድር ወደ ላይ ወደ ታች ወደ ግራ ወደ ቀኝ ኾኖ እንደ መጋረጃ በዕንጨት ላይ ተሰቀለ፤ እኛን ከጻድቃን ጋራ አንድ ያደርገን ዘንድ ርሱ ከበደለኞች ጋር ተቈጠረ) በማለት በስፋት የነገረ ስቅለቱን ምስጢር አስተምረዋል፡፡

በመስቀል ሲሰቀልም በቀኙ የተሰቀለው ጥጦስ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ይባላል፤ በቀኝ የተሰቀለው ጥጦስ ፀሓይ ስትጨልም፣ ጨረቃ ደም ስትኾን፣ ከዋክብት ከብርሃናቸው ሲራቈቱ፣ ድንጋዮች ሲሠነጠቁ፣ መቃብራት ሲከፈቱ፣ ሙታን ሲነሡ፣ የምኩራቡ መጋረጃ ወደ ኹለት ወደ ሦስት ሲቀደድ ሰባቱ ተአምራት ሲደረጉ አይቶ አምላክነቱን ተረድቶ “አቤቱ በመንግሥት ዐስበኝ” እያለ ወደ ርሱ ሲለምን፤ በግራ የተሰቀለው ወንበዴ ሰምቶት እየተዘባበተ “አንተስ ክርስቶስ አይደለኽምን? ራስኽንም እኛንም አድን” ይል ዠመር (ሉቃ ፳፫፥፴፱)፡፡

ያን ጊዜ በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ጌታችን ለቤዛ ዓለም የተሰቀለ እውነተኛ የባሕርይ አምላክነቱን ስለተረዳ በግራ የተሰቀለውን “አንተ እንደዚኽ ባለ ፍርድ ሳለኽ እግዚአብሔርን ከቶ አትፈራውምን? ስለ አደረግነውም የሚገባንን እንቀበላለንና በእኛስ እውነተኛ ፍርድ ነው፤ ይኽ ግን ምንም ክፋት አላደረገም” ብሎ ከገሠጸው በኋላ ኀጢአት ሳይኖርበት የተሰቀለውን ንጹሐ ባሕርይ አምላኩን፡- “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ” (ጌታ ሆይ በመንግሥትኽ በመጣኽ ጊዜ አስበኝ) እያለ ሲለምነው ጌታችንም “እውነት እልኻለኊ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኾናለኽ” ብሎት ተስፋውን ሰጥቶታል፡፡

በኹለት ወንበዴዎች መኻከል ከሰቀሉት በኋላ ጲላጦስም “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክም ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው፤ (ዮሐ ፲፱፥፲፰-፳፪)፤ የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን “ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለኽ አትጻፍ” ሲሉት፤ ጲላጦስም “የጻፍኹትን ጽፌአለኊ” ብሎ መልሶላቸዋል።

ይኽነንም በሕማማት ድርሳኑ ላይ ሲተረጒሙት፡- “ወዝ መጽሐፈ ጌጋይ ዘጸሐፎ ጲላጦስ ወአንበሮ መልዕልተ ርእሱ ይደምስስ ለነ በኲሉ ጊዜ መጽሐፈ ዕዳነ ዘጸሐፉ አጋንንት” (ጲላጦስ ጽፎ ከራሱ በላይ ያኖረው በደሉን የሚናገር ይኽ መጽሐፍ ኹልጊዜ አጋንንት የጻፉትን የዕዳችንን መጽሐፍ ያጠፋልን ዘንድ ነው) በማለት አራቅቀው ገልጠዋል፡፡

ጌታችን በሚሰቀልበት ጊዜ ብርሃን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ለመሰወር ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ፀሓይና ጨረቃ ብርሃናቸውን ነሥተዋል (ማቴ ፳፯፥፵፭)፡፡

ይኽ በጌታ ስቅለት ዕለት እንደሚደረግ አስቀድሞ በነቢዩ አሞጽ ኹለት ጊዜ በትንቢት ተነግሯል፡- ይኸውም
☞ “የእግዚአብሔር ቀን ብርሃን ሳይኾን ጨለማ አይደለምን? ጸዳል የሌለውም ድቅድቅ ጨለማ አይደለምን?” (አሞ ፭፥፳)
☞ በዚያም ቀን ፀሐይ በቀትር እንድትገባ አደርጋለኊ ይላል ጌታ እግዚአብሔር በብርሃንም ቀን ምድሩን አጨልማለኊ” (አሞ ፰፥፱) ተብሎ

በዕለተ ዐርብ በጌታችን ስቅለት ዕለት ስለተደረገው ስለዚኽ ታላቅ ተአምር ሊቃውንት እንዲኽ ይገልጹታል፡-