Get Mystery Box with random crypto!

እወዳታለሁ ገራሚ ናት ደስስስ ትለኛለች። ብዙ ግሩም ጊዜ አሳልፈናል አብረን ስንሆን ሰአቱ ይበ | ቅንጭብጭብ

እወዳታለሁ ገራሚ ናት ደስስስ ትለኛለች።
ብዙ ግሩም ጊዜ አሳልፈናል አብረን ስንሆን ሰአቱ ይበርብኛል አብረን ውለን ከመቼው መሸ ትለኛለች ቶሎ ቶሎ ትናፍቀኛለች።

ቀልድ ይገባታል ኮስተር ብዬ ስኮምክ ታሽካካልኛለች፣ ነፍሳችን ይናበባል ፣ ሳናወራ እንግባባለን ።

ከስምንት ወር በፊት <<አግባኝ>> አለችኝ አልተዘጋጀሁም አልኳት፣ ጊዜ ስጪኝ ፣ ትንሽ ታገሺኝ አልኳት
<<አልችልም >>አለችኝ።

የመንደሩ ሰዎች ሽሙጥ ፤ የቤተሰቦቿ ጭቅጭቅ እና እድሜዋ አስጨነቃት ።

እኔ ደግሞ ባልተዘጋጀሁም አቋም ፀናው።

ከህይወቴ መስመር መሰስ እያለች ሄደች። እየደበረኝ ቅር እያለኝ በአቆሜ ፀናው።

አልፎ አልፎ ከአንገት በላይ ሃይ እንባባላለን።

ባለፈው ሳምንት እንገናኝ አለችኝ። ተገናኘን ፤ አይኗ ውስጥ ጉጉት፣ ተስፋ እና ደስታ ምንም አላየሁም። <<በነገራችን ላይ ቅዳሜ ሰርጌ ነው ከቻልክ ልጠራህ ነው የመጣሁት>> አለችኝ።

ትኩር ብዬ አየኋት ቅናቴን ለመደበቅ የደረቀ ፈገግታ ፈገግኩ (ደስስስ የማይል ስሜት ወረረኝ) ያሳዝናል አመለጥሺኝ አልኳት።

<<ብሽቅ ስለሆንክ ተፈላሰፍክ መጠበቅ ፈልጌ አልቻልኩም>>አለችኝ እኔን የምትወደኝን ያህል የምታገባውን ልጅ እንደማትወደው ገብቶኛል።

ያዘዘችውን ቢራ ተጎነጨች እና መጨዋወታችንን ቀጠልን።

<<በእድሜህ ማሳካት የምትፈልገው ነገርን ዛሬ ካልጀመርከው መሽቶ በነጋ ቁጥር ጭንቀትህ ይበረታል ።

ትልቅ ለመምሰል እንዳልጣርን ፤ አንድ ፍሬ ለመባል እንባክናለን።

መንደርተኞች ሳይታወቃቸው ጫና ውስጥ ይከቱሃል ። ባገኙህ ቁጥር ጨዋታ ለመፍጠር ይሆን አሳስቧቸው ይሆን ብቻ ምንጩ ባልታወቀ ምክንያት እንደቀልድ ምንድን ነው መፍዘዝ አግቢ እና ሰርግ አብይን እንጂ ይሉኛል ።

ቤተሰቦቼ ተጠርተው ስለበሉት ሰርግ ከሰርግ ሲመለሱ ይተነትናሉ ይገባኛል መልእክት እያስተላለፉ ነው

ተረድቼሃለሁ ችስታ ነህ ብታገባ ድህነት ፓራላይዝ የሚያደርግህ ይመስልሃል በልጅነት እየራበህ እንዳደክ የነገርከኝን አልረሳሁም ።

አሁን ካገባሁ የትላንት ህይወቴን እደግመዋለሁ ብለህ ትሰጋለህ።

ሁኔታህ እና የኔ ፍላጎት አራምባ እና ቆቦ ሆነ ። እንደሁኔታ በቅርቡ በቀላሉ ትዳር የሚባል ስብጥር ውስጥ እንደማትገባ እርግጠኛ ነኝ

ጌታ ይሁንህ ፤ እህቴ እንዴት ቆማ እንደቀረች አውቃለሁ .. . .. . ዘግይቶ ማግባት ለወንድም ምቾት እንደማይሰጥ ከልጅህ ጋ እየተንከባለልክ መጫወት ሲሳንህ ይገባሃል።

ብልጥ ነኝ ባዮች ቆመው የሚቀሩት እየተመራመሩ ነው ፤ ህይወት በስሌት እና በምርምር ብቻ የሚሳካ እየመሰላቹ ነው>>

ዝም አልኳት ንግግሬ ከዝምታዬ ካነሰ ለምን እናገራለሁ ። ያወራችው የቱ ነው ስህተት ?!

ከነፍ ዝምታ በኃላ አይኖን ትክ ብዬ እያየሁ ትዳርሽ የተባረከ ይሁን አልኳት ።

ፈጥኖ ከመሳሳት ዘግይቷ ትክክል መሆን በእጅጉ ይሻላል ደሞ ያልተሳካ ትዳር ቆሜ ቀረው የሚል ጥድፍያ ውጤት ነው ብዬ ተፅናናው።

Adhanom Mitiku
@kinchebchabi @kinchebchabi