2022-05-05 21:35:41
የአስተዳደር መስሪያ ቤት ውል በግልግል ይታያል? አይታይም? የሚለው የህግ ነጥብ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የተለያዬ አስገዳጅ የህግ ትርጉሞችን ሰጥቷል፡፡ ከነዚህም መካከል:-
1ኛ- በዘምዘም ፒኢልሲ እና በኢሊባቦር ዞን ትምህርት ጽ/ቤት መካከል ባለው ጉዳይ በሰ/መ/ቁ 16896 16/02/1998ዓ.ም በቅጽ 2 ገጽ 75-78 ላይ በተለይ ህግ ከከለከላቸው ነገሮች በስተቀር ተዋዋዮች የሚዋዋሉበትን ጉዳይ እንደመሰላቸው የመወሰን መብት እንዳላቸው የፍ/ህ/ቁ 1711 ስለሚገልጽ እና ውል ደግሞ ለተዋዋዮች ህግ ስለሆነ እንዲሁም ግራቀኙ በውላቸው ላይ አለመግባባቶች በግልግል እንደሚታዩ በግልጽ ስለተቀመጠ ውላቸው መከበር ስላለበት ጉዳዩ በቀጥታ በመደበኛ ፍርድ ቤት መታየት የለበትም
በማለት አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህም ማለት ጉዳዩ በቅድሚያ በግልግል ዳኝነት መታየት አለበት የሚል ነው፡፡
2ኛ- በብሄራዊ የኢትዮጽያ ኢንሹራንስ ኩባንያ እና በዘላቂ ግብርና ተሀድሶ ኮሚሽን መካከል በፋ/መ/ቁ 27349 ታህሳስ 8/2000ዓ.ም ቅጽ 7 ላይ የተሰጠ ውሳኔ ሲሆን በይዘት ደረጃ የፍ/ህ/ቁ 1765(የዘመድ ዳኛ ስለመምረጥ) እና 1731 ድንጋጌን በመጥቀስ ጉዳዩ በውላቸው መሰረት የዘመድ ዳኛ በፍርድ ቤት በኩል አሰይሞ እልባት ማግኘት የሚገባው እንጅ በቀጥታ ለፍርድ ቤት መቅረብና ውሳኔ ሊሰጥበት የሚገባ አይደለም በማለትጉዳዩ በግልግል ዳኝነት መታየት እንደሚችል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
3ኛ- በጣና ውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ እና ድሬዳዋ አስተዳደር ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን መካከል በሰ/መ/ቁ 127459 መስከረም 23/2010ዓ.ም የተሰጠው ውሳኔ ከላይ ከየናቸው ሁለት ውሳኔዎች በይዘቱ ያፈነገጠ ነው፡፡ይዘቱም የፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 315(2) የአስተዳደር መስሪያ ቤት የግንባታ ውል ጉዳይ በግልግል ዳኝነት አይታይም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ይህ ውሳኔ
የመጀመሪያዎቹን ሁለት ውሳኔዎች በግልጽ አልሻራቸውም። በተግባር እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ሰበር ወጥ የሆነ የህግ ትርጉም ለመስጠት በሚል ቢቋቋምም የተቋቋመበትን አላማ ስቶ ህግ እየሰበረ ነው:: ተገማችና ወጥነት ያለው ውሳኔ ባለመስጠቱ ዳኞች የየራሳቸውን አቋም ለመያዝና የሰበርን ውሳኔዎች አስገዳጅነት ላለመቀበል ምክንያት ሆኗል! የተለየ ሀሳብ ካለ እስኪ ወዲህ በሉ ጓዶች! ሰላም አዳር!
858 viewsMengesha Eyasie, 18:35