Get Mystery Box with random crypto!

ጉባዔው በ26 የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ። -------------- | 🇪🇹ዘወልድ ምክረ-ሕግ🇪🇹‼️

ጉባዔው በ26 የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
--------------------------------------------------------------------------------
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ረቡእ ሚያዝያ 05 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ 26 ጉዳዮች ላይ በመወያየት 25ቱ የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት እንዲዘጉ የወሰነ ሲሆን፤ በአንድ ጉዳይ ላይ በሰፊው በመወያየት ጉዳዩ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግበት በይደር እንዲያልፍ ወስኗል።
ሰፊ ውይይት የተደረገበትና ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግበት የተወሰነው ጉዳይ የንብረት ክርክር ጉዳይ ሲሆን ለክርክሩ መነሻ የሆነው ቤት የስምንት ሰዎች ይዞታ የተመዘገበ ሆኖ እያለ ፍ/ቤቱ ከስምንቱ አመልካች አንዱ ሆነው የቀረቡትን የተከሳሽ ሚስትንና ተከሳሽ ሆነው የቀረቡትን ባል በማከራከር የከሣሽ እና ተከሣሽ የጋራ ሀብት ነው በማለት ይወስናል፡፡ የተቀሩት ሰባቱ ባለይዞታዎችም ውሳኔውን በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 358 በመቃወም ጣልቃ ገብ አመልካች ሆነው ወደ ክርክሩ ቢገቡም ፍ/ቤቱ በክርክሩ ሂደት ወቅት ግማሾቹ በምስክርነት የቀረቡ ሌሎቹ ደግሞ ችሎት እየገቡ ሲከታተሉ የነበሩ በመሆኑ መብታቸውን ለማስከበር ጣልቃ በመግባት መከራከር እየቻሉ የክርክሩን ውጤት ጠብቀው መብታቸውን የሚነካ ውሣኔ ሲሰጥ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ. 358 መሠረት ያቀረቡት ተቃውሞ ተቀባይነት የለውም በማለት ብይን ይሰጣል፡፡ የይግባኝ አቤቱታቸውን ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ቢያቀርቡም ፍ/ቤቱ አስቀርቦ በማከራከር የስር ፍ/ቤት ውሣኔን አፅንቷል፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም አያስቀርብም በማለት ጉዳዩን በመዝጋቱ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መ.ቁ. 201187 እና 187023 የሰጣቸው ውሣኔዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40/1፣ 2፣ 7 እና 81 ስር የተደነገጉትን የንብረት መብቶች እና በአንቀጽ 9/1/ የተደነገገውን የሕገ መንግሥት የበላይነት ድንጋጌን ስለሚቃረን የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሰጠን በማለት ጠይቀዋል፡፡
ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ በስፋት የተከራከረ ሲሆን በአንድ በኩል ከላይ ፀንተው ያሉት ሁለቱ ውሣኔዎች ለሕገ መንግሥት ትርጉም አቤቱታ የቀረቡ ቢሆንም ሁለቱም የፍ/ቤቶቹ ውሣኔዎች ማስረጃን በመመዘን እና ሕግን በመተርጎም የተወሰኑ በመሆናቸው የአመልካቾችን የትኛውንም ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚፃረሩ አይደሉም የሚል ሀሳብ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል የፍ/ስ/ስ/ህጉ ቁ. 358 ድንጋጌ ይዘት ሲመረመር በዋና ክርክር ወቅት ተካፋይ መሆን ሲገባው በክርክሩ ተካፋይ ያልሆነና ወይም በክርክሩ መብት ያለው እና ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ፍርድ መብቱ የተነካበት ሰው ፍርዱ ከመፈጸሙ በፊት የመቃወም አቤቱታ አቅርቦ መከራከር እንደሚችል በግልጽ ስለሚገነግግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 56795 ላይ አንድ ክርክር መጀመሩን ያወቀ ወገን የክርክሩን ውጤት ጠብቆ መብቱን የሚነካበት ሆኖ ባገኘው ጊዜ ከውሳኔው በኋላ የሚያቀርበው አቤቱታ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 358 መሰረት ተቀባይነት የለውም ብሎ የሰጠው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ህግን ከመተርጎም ስልጣኑ ያለፈና የአመልካቾችን ንብረት የማፍራት መብት የሚጻረረር በመሆኑ ውሳኔው የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 37፣ 40 እና 79(1) ድንጋጌ ስለሚቃረን የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል የሚል ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ጉባዔውም በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ጥናት እንዲደረግበትና ለቀጣይ ውይይት እንዲቀርብ ወስኗል፡፡