Get Mystery Box with random crypto!

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 205827 ህዳር 27ቀን 2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት | 🇪🇹ዘወልድ ምክረ-ሕግ🇪🇹‼️

የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ/ቁጥር 205827 ህዳር 27ቀን 2014 ዓ/ም በዋለው ችሎት የአብክመ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 23(2) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ አላማውን በማያሳካ መንገድ ተርጉሞታል በማለት አስገዳጅ ውሳኔ ሰጠ ።

ጉዳዩ የተነሳው ያረጋል ተገኘ የተባለ ተከሳሽ መስከረም 11/2012 ዓ/ም በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ 1 ቱርክ ሽጉጥ ከመሰል 31 ጥይቶች ጋር ይዞ በመገኘቱ ዐቃቤ ህግ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4(1) እና 22(2) ላይ የተመለከተውን ተላልፎ ጦር መሳሪያ ይዞ ተገኝቷል በሚል ክስ መስርቶበት የአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ፍ/ቤት ተከሳሸን ባመነው መሰረት ጥፍተኛ በማለት 2ወር ቀላል እስራትና 600ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ስለወሰነና ውሳኔ የአዊ/ብ/ዞን ከፍ/ፍ/ቤት ስላጸናው በተከሳሽ ይግባኝ ጠያቂነት የአብክመ ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 23(2) ላይ የተመለከተውን የጊዜ ገደብ በመጥቀስ ተቆጣጣሪ ተቋሙ የጊዜ ገደብ አውጥቶ ምዝገባ ባልጀመረበት ሁኔታ ተከሳሽን ጥፋተኛ ብሎ መቅጣት ህጋዊ መሰረት የለውም በማለት የስር ፍ/ቤቶችን ውሳኔ በመሻሩ የአብክመ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ በማቅረቡ ነው ።
ይግባኝ የቀረበለት የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎትም ፦
1ኛ የአዋጁ አንቀጽ 23(2) ጊዜ ሰሌዳ ያስቀመጠ ቢሆንም ቅሉ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ ሆኖ ማነኛውም ግለሰብ ጦር መሳሪያ ይዞ ቢገኝ ከተጠያቂነት እንደሚድን አያስቀምጥም ።
2ኛ የአዋጁ መሰረታዊ አላማ የጦር መሳሪያን ወደ ህጋዊ ስርዓት አስገብቶ መቆጣጠር እንጅ በዚህ አንድ አመት ጊዜ ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ የጦር መሳሪያ ይዞ ለመገኘት ፈቃድ የሚሰጥ አይደለም ፤ የጊዜ ገደቡ የሚያገለግለው ጦር መሳሪያው በምዝገባ ሂደት ላይ እያለ ችግር እንዳያጋጥም እንጅ የአንድ አመት የመያዝ ፈቃድ የሚሰጥ ተደርጎ መተርጎም የለበትም ፤
ስለሆነም የጊዜ ገደብ መቀመጡ እስከ አንድ አመት ያለማንም ጠያቂነት የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመፍቀድ ታስቦ የተደነገገ አድርጎ መተርጎም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣውን አዋጅ አላማ የሚያሳካ ካልመሆኑም በተጨማሪ ተከሳሹ በሰጠው የእምነት ቃል መሰረት ጦር መሳሪያውን የያዘው ነባሩ አዋጅ በስራ ላይ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑ ያልተካደ በሆነበት ሁኔታ ተከሳሽን ከተጠያቂነት ነጻ ማድረግ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 23(2) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ አላማ ባልተገባ መንገድ በመተርጎም መሰረታዊ የህግ ስህተት መፈጸም ነው በማለት የወረዳውንና የከፍተኛውን ፍ/ቤቶች ውሳኔ አጽንቶ የአብክመ ጠ/ፍ/ቤት የሰጠውን ውሳኔ ሽሮታል ።
Please share it ( እባክዎ ያጋሩት)
በ ተስፍሽ ዐቢሲኒያ