Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፳፩~ ( 221) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 ወይዘሮ አትጠገብ እን | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፳፩~ ( 221)
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
ወይዘሮ አትጠገብ እንዲሁ እየተብሰለሰለች ቁጭ ብላ የባጡን የቆጡን ከእንደገና ብቻዋን ስታወርድ ስትሰቅል የቀኗ ፅሐይ ጥላዋን እያጠላች እግሮቿን ወደ ምስራቅ ዘርግታ አንገቷን ወደ ምዕራብ አቅጣች እያሰገገች ነው። የሰውን ክፋት ገመና በብርሀኗ ስታጋልጥ ውላ በመጨረሻ በጨለማ ተረትታ ጉሟ ውስጥ ተሸጎጠች። አንድ የከፋው እና የናፈቀ ህፃን ተንደርድሮ የእናቱን ጡት ይዞ ጉያዋ ውስጥ እንደሚደበቀው ነው የጀንበሯ ቀይ ጉሙ ላይ አሸጓጎጧ። ይህን የምሽት የተፈጥሮ መስተጋብር ቆሞ ላስተዋለ ሰው ብዙ ነገር ይማራል። አንዳንድ ጊዜ በየዋህነትም ሊሆን ይችላል ወይም በጊዜው በማይሆን ስሜት የፈጠርነው ችግር አድጎ እኛ የምንደበቅበት እስክናጣ ድረስ ያደርገናል። ሰው ልክ እንደ ፅሐይ ይወጣል። እድሜው የፅሕይን አስራ ሁለት ስዐት ሲያክል ደግሞ ይመሽበታል። ከመሸ በኋላ ጠዋቱን ማግኘት ቢፈልግ አያገኝም በፀፀት ቢናውዝም በጭራሽ። ስለዚህ ሕይወታችንን በጥንቃቄና በብስለት መኖር ካልቻልን የምንጥላቸው የነገር ቃሎች እሾህ ሆነው በቅለው ሲወጉንና እርምጃችንን በሰቀቀን እንድንሞላው ያደርጉናል። ሰው የዘራውን ነው የሚያጭደው ማለት ጤፍ ከዘራ ጤፍ እንጅ ማሽላ አያጭድም እንደማለት ብቻ ሳይሆን መጥፎ ነገር ካደረግን ምላሻችን ሊሆን የሚችለው መጥፎ ነገር ነው ለማለት ነው። መቼም ነገር በምሳሌ ጠጅ በብርሌ ነውና የሚባለው።
በሀሳብ ሰጥማ ስትነሳ የተቀደደው የጎዳዋ ጫፍ የእግር ጣቷን ጠልፎ ከእንደገና ወደቀች የጎዳዋ ቀዳዳ ውስጥ የገባችው ጣቷ ትንሽ ወለም ብሏት አመማትና ይዛት ተቀመጠች። በጣም ስላመማት ሕመሟን እንደምንም እየዋጠች ቀስ አድርጋ በባዶው እየነካካች ታሻት ጀመር። ወይዘሮ የአትጠጠገብን አኳኋን የተመለከተ በጭራሽ መጥፎ ነገርን መስራት አይደለም ለማሰብ እርም ያስብላል። ከልቧ ነው ብሶቷና ኃጢያቷ ገንፍሎ አይኗን በእንባ ያጠበው።
***
ሁሉም ነገር ዝግጁ ሆኗል። ሮሃ ባንድ የተዘጋጀለትን ቦታ ቀድሞ ይዞ ዝግጅቱን አጠናቆ የፕሮግራሙን ቅደም ተከተል ብቻ ይጠባበቃሉ። ካሜራ ማኖቹ በየቦታውና መውጫ መግቢያው ካሜራቸውን አስቀምጠው እያንዳንዷን ነገር ይለቅማሉ። የሙሽሮቹ ስቴጅ በደንብ ዲኮር ተደርጓል። እንግዶች እና ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎች ቀድመው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። ድንኳኑ በሰዎች ተጥለቅልቋል በየ ድንኳኑ ኮሪደር የቀዳማዊና የሐምራዊ ፎቶ ተሰቅሎ ዙሪያው በዲም ላይት ይበራል ከፏቷቸው ስርም " የአቶ ቀዳማዊ ታረቀኝና የወይዘሪት ሐምራዊ ሱራፌል የጋብቻ ስነስርዓት"የሚል ወርቃማ ፅሁፍ ሰፍሮበታል። የሰርግ ፎቷቸውን የተመለከተ እንግዳ ሁሉ "እትፍ እትፍ ከአይን ያውጣችሁ! ትዳራችሁ በፍቅርና በረድኤት የተሞላ ይሁን!"ብሎ የማይመርቅ የለም።
ጠጁ፣ጠላው፣ቢራው ወይኑ፣ውስኪው ሁሉም በአይነት በየጠረንጴዛው ተደርድሯል። ምግቡም በአይነት ከአትክልት እስከ ዶሮ አሩስቶው በአልጫም በቀይ ተሰርቶ በጎዶጓዳ ሳህን ተቀምጧል አንግዶችም በሰልፍ የሚፈልጉትን ምግብና መጠጥ እያነሱ ይስተናገዱ ጀመር። የምሳ ስነስርአቱ እየተካሄደ እያለ ሙሽራውን ይዘው ሚዜየዎቹና አጃቢዎቹ ወደ ሙሽሪት ጉዞ ሄዱ።ሆታውና ጭፈራው እንደ ጉድ እየኖጋ ጉዞ ሙሽሪት ጋ። ሙሽሪት ጋር የነበረው ድግስ አጀብም ለጉድ ነው። የሁለት ኃብታሞች ሰርግ በመባል የተሰየመው የአቶ ሙሉሰውና የአቶ ሱራፌል ሰርግ በብዙ ክዋኔዎች የተሻለ ና የተመሰገነ አቅርቦትና ድግስ ነው። ከብዙ እልህ አስጨራሽ ጭፈራና ጥያቄ በኋላ ወደ ሙሽሪት ክፍል ሚዜዎቹና ሙሽራው ገቡ። የሙሽሪት ሚዜዎች በተራቸው ደግሞ ሙሽራተውን ሸፍነው በጭፈራ የወንዱን ሚዜዎችን አደከሟቸው። ትዕይንቱ ደስ የሚልና የባህልን ይዘት የተላበሰ በመሆኑ በሁለቱም ወገኖች ምንም አይነት ቅሬታ አይፈጥርም። የሴቷ ሚዜዎችም በባህል መሠረት ነው የሚያደርጉት ወንዶቹም የሚጋፉት በደስታ ነው። ባህልና ወግ ለአንዲት ሀገር ምሰሶዎችና መሠረቶች ናቸው። ባህል ሐይማኖት ወግ የሌላት ሀገር ሀገር አትመስልም። የራሷ መገለጫ ሊኖራት ይገባል።አሁን በርካታ የአለም ሀገራት የራሳቸው ወግና ባህል የላቸውም። ለረጅም አመታት በቅኝ ግዛት የተያዙ ሀገሮችም ቋንቋቸውም ባህላቸውም ወጋቸውም በቅኚ ገዥዎች ሀሳብና ተፅዕኖ ጠፍቶ የሌላ ሀገር ወግና ባህል ለምደው እናያቸዋለን።ይህ እንዳይሆን ትልቅ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች አያትቻችን ይግባና እንዲህ ውብ በሆነ የባህል ትውፊት ትዳር ሲመሰረት ደግሞ በጥሩ ሁኔታ ያማረና ለየት ያለ ይሆናል።
በሽማግሌዎችና በቄሶቹ መሀል ቃለ መሀላ ፈፅመው ምሳ ከበሉ በኋላ ወደ ሙሽራው ቤት ተመለሱ። "በሀዘንም በደስታ ጊዜም አብረው ሊሆኑ ላይለያዩ ሚስቱን ሊያከብር ሊንከባከብ እርሷም ባሏን ልትንከባከብ ልታከብ እስከ እድሜ ማብቂያቸው ላይለያዩ በአጋቢ ቄሳቸው ፊት ተማምለው ባልና ሚስተነታቸውን አሳወጁ።ቤተዘመዱም ለሙሽሮቹ ደስታ ወገቡን ፈትሾ በውዝዋዜ አጅበው እንኳን ደስ ያላችሁ የሚል መልዕክት በጭብጫቦና በእልልታ አስተላልፈው ሙሽሮቹን ወደ ወንዱ ቤት ለመሸኘት አንድ ላይ ግልብጥ ብለው ከድንኳኑ ወጡ። ሙሽሮቹን እየዞሩ ሚዜዎቹ ከጨፈሩ በኋላ ለሙሽሮቹ ወደ ተዘጋጀችው ቅንጡ መኪና ሙሽሮቹን አስገብተው ከፊታቸው በፒካፕ ካሜራ ማኖቹ እየቀረፁ አጃቢዎቹ መኪኖችን በሰልፍ ይቀርፁ ጀመር።አጃቢዎቹ መኪናቸውን በንፋፊት ለጣጥፈው በጋራ እየጨፈሩ ጉዟቸውን ወደ ደጃች ውቤ ሰፈር አደረጉ። ከቦሌ የተነሳው ሰርገኝ በፍላሚንጎ መስቀል አደባባይ አድርጎ በጊዮን አልፎ አንባሳደርን በመተው የቸርቸልን መንገድ አቅንተው ወደ ውቤ በረሃ ገቡ። የወንዱ ሙሽራ ቤተሰቦችም ሙሽሮቹ እስኪመጡ አሰፍስፈው እየጠበቁ ነበርና የመምጣታቸውን የመኪና ጡርንባ ሲሰሙ ሁሉም ነገር ጀመረ። ደጂው የሰርግ ሙዚቃ ከፍቶ ይዘፍኑ ጀመር። ሰርግ ብዙ ሰዎች ባይወዱም ነገር ግን አንዳንድ ወላጆች የልጃቸውን ሰርግ ከማየት በላይ ለእነሱ ድል የለም። ተመርቀው ከሚያይዋቸውና በሌላ የስራ መስኮት ዝነኛ ሆነው ከሚረኩት በላይ በልጆቻቸው ሰርግ ይረካሉ ፍፁም ደስተኛ ይሆናሉ። ብዙ የተለፋበትን ድግስም ዘመድ አዝማድ የሩቅ እንግዳ ተጋብዞ ሲሄድ ወላጆች ደስ ይሰኛሉ።ቀዳማዊና ሐምራዊ በዚህ ውብ የአሰራረግ ስነስርዓት ተድረው ኤርስ በእርስ ተዛምደው ወላጆች ከወላጆች በልጆቻቸው ደስታ ተደስተው ሰርጉን ቋጩ። ልጆቻቸውንም እስከወዲያኛው በልጅ የታጀበ ደስታ እንዲሆንላቸው መርቀው ወደ ቤታቸው አስገብተዋቸው። በነ ቀዳማዊ ቤት የተዘጋጀላቸውን ግብዣ ተጋብዘው ተሳስቀው ተጨዋውተው ሙሽሮቹን ጥሩ ጫጉላ እንዲሆንላቸው በመመኘት ተሰናብተዋቸው ወጡ። ቀዳማዊና ሐምራዊ ቤተሰቦቻቸውን ሸኝተው ተቃቅፈው ሶፋው ላይ ተቀመጡ። "የኔ ፍቅር ይቺን ቀን በተስፋና በትዕግስት ለአመታት ስጠብቃት ነበር አሁን ይሄን ቀን በሕይወቴ መቼም አልረሳውም። ይሄው እድሜ ልኬን ደስተኛ ሆኜ እንድኖር ፈጣሪዬን አንተን የልቤን ንጉስ ሰጥቶ አንግሶኛልና ሁሌም የእሱ አመስጋኝ ሆኜ እኖራለሁ"አለችና አይኑን ሳም አደረገችው። እሱ ዝም ብሎ በፍቅር ይመለከታት ነበር ዝምታው በቃል የማይሰፈር አስተያየቱ በምን የማይገለፅ የፍቅር አተያይ ነበር።

@amba88
@ken_leboch