Get Mystery Box with random crypto!

' ኤሴቅ ' ክፍል ~፪፻፲፱~ ( 219 ) በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888 ' መቸገር አልነበ | ቅን ልቦች

" ኤሴቅ "
ክፍል ~፪፻፲፱~ ( 219 )
በአምባዬ ጌታነህ @adwa_1888
" መቸገር አልነበረባችሁም እኮ ሙሌ"አለ ቀዳማዊ። "ኧረ አይባልም። እዛ ብትዳር ጥሩ ነበር በደንብ እድርህ ነበር። ደግሞ አዝመራው ለጉድ ነበር የያዘው። ያመረትነው እህል ብዙ ነበር። ከምግቡ እስከ ሰላሱቱ ድረስ ተመርቶ ነበር።"አለና ሁለቱን አቁማዳ የነጭ ጤፍ ዱቄት ለወይዘሮ ሔዋን ሰጡ። ሌሎቹ ልጆች ደግሞ የጠላ ድፍድፉን ይዘው ተከተሉ። "እግዚኦ ይሄን ሁሉ ነገር ተሸክማችሁ?"አለችና ሔዋን ሙሉቀንናና ዳሳሽን ስማ በዝና እንደምታውቃቸው ነግራቸው ወደ ቤት አስገብታ አስቀመጠቻቸው። ቀዳማዊም አብሯቸው ተቀመጠ። ዳሳሽ ብድግ አለችና "እትዬ የሆነ በርሚል ነገር ይስጡኝ ጠላውን ልጥመቅ"አለች። "ኧረ ምነው ልጄ መጀመሪያ አረፍ በይ እንጅ አሁን አይደል ከመንገድ የመጣችሁት ትንሽማ አረፍ በሉ የሚጠጣም የሚበላም ቀማምሱ እስከዛው ተጫወቱ እኔ የሚበላ ይዤ ልምጣ ብላ ወጣች ቀዳማዊም ተከተላት "እንግዶቹን ትተኻቸው ለምን መጣህ?" "እነሱ እንግዳ አይደሉም ወንድሞቼ ናቸው ስለዚህ ለትንሽ ደቂቃ ብቻቸውን ብተዋቸው ምን ይሆናሉ ብለሽ ነው! እትዬዋ" "እሺ እንዳልክ በል ሳህንና ይሄን ይዘህ ሂድና አስይዛቸው እኔ ወጡን ይዤ እመጣለሁ" "እሺ "ብሎ ይዞ ወጣ
እነ ሙሉቀን ምግብ በልተው በደንብ ከተስተናገዱ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት ተነሱ "ምን ልትሰሩ ነው የምትነሱት?"አለ ቀዳማዊ "እህ አዴጌር ያለበት ቤት ስራ ይጠፋዋል ብለህ ነው? የተገኘውን መስራቴ ነውይ ዳሳሽም ጠላውን ትጥመቅ ወንጠፍትና ገለገይት አምጥተሻል አይደል?"አለ ሙሉቀን ወደ ዳሳሽ ዘወር ብሎ "አዎ የከተሜ ሰው መቼም በቢራና በጠጅ ነው የሚያደርገው ጠላ ከጠመቁ ዝልሉን እንጅ ይሄን የገብሱን አያውቁትም ብዬ ሁሉንም ይዣለሁ። እኔ ምፈልገው ጋን ወይም በርሚል ብቻ ነው። እሱን እንዲያመጡልኝ ንገራቸው"አለች ለቀዳማዊ "እሺ እንግዲህ ካልሽ!" አለና ለሔዋን ዳሳሽ የምትፈልገውን እንድታቀርብላት ነግሯት ከነ መልካሙ ጋር ሻይ ቡና ለማለት ወደ ውጭ ወጡ።
"ቀዳማ እንደው ይቺ ሴትዮማ እናት ማለት አይደለች"አለ ሙሉቀን "ከእናትም ትበልጣለች ወንድሜ ሕይወቴን ምቹና ጣፋጭ ያደረገችልኝ ሴት ነች። ባለቤቷን ደግሞ ይበልጥ ብታየው ትገረማለህ?"አለ "ወትሮም እኮ እሚባለው እልፍ ሲሉት እልፍ ይገኛል ነው!"አለ መልካሙ(አቤል) "እውነት ነው። በእሱ እኔም አምናለሁ። ተመስገን በአንድ በኩል እንደዛ ባይሆኑብኝ ኑሮ ይሄን አለም አላየውም ነበር ብዬ አስባለሁ። እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያስጨክነውም የሚያራራውም በምክንያት ነውና እኔ በበጎ ጎኑ አይቼዋለሁ"አለ ቀዳማዊ "ሙሽሪትን የሰርጉ ቀን ነው የምናያት ቀዳ?"አለ ሙሉቀን ወሬውንም ለመቀየር ያህል "አዎ እንግዲህ የእለቱ እለት ማየታችሁ ነው። ያውም ኤኮ መች ነው ምንተዋወቀው እያለችኝ ነበር። አሁን እንዳልደውልላት ከጓደኞቿ ጋር እየተዘገጃጀች ነው።" "ኧረ ችግር የለም ቀስ ብለን እንተዋወቃለን"አለ ሙሉቀን። "ለምንድነው ግን ዳግማዊን ያላመጣችሁት ሙሌ"አለ ቀዳማዊ "ልጅ ይዞ መንገድ ጥሩ አይደለም። በዛ ላይ አያቱ ልጄማ ከእኔ ጋር ነው ሚቆየው ብላ ከረሚላ እሰጥሀለሁ ስትለው እሺ ብሎ አልቀረም መሠለህ" "አይ ጥሩ አላደረጋችሁም ይዛችሁት መምጣት ነበረባችሁ ማርያምን"አለ ቀዳማዊ "ችግር የለም የሚመጣባቸው ገና ብዙ ጊዚያቶች አሉን ስለዚህ ብዙ ቅር አይበልህ
***
"ልጄ ደከምሽ እኮ። ደግሞ ብዙ ነው ያመጣችሁት"አለች ሔዋን ለዳሳሽ ከልቧ እያዘነች። "ኧረ ይቺማ ምን አላት እትዬ አውራጅማ ብዙ ነበር የሚያዝ"አለች ዳሳሽ እየተቅለሰለሰች "አይ ይሄን ሁሉ ይዛችሁ ጭራሽ ትንሽ ነው? አይ ከበቂ በላይ ነው። የሚያግዝሽ እንዳልጠራ ይሄን አጠማመቅ የምትችል ሴት ያለች አይመስለኝም" "ኧረ ችግር የለም ይሄው እየጨረስኩ ነው። ትንሽ ነው የቀረኝ"አለች ለማስተባበል ነገር ግን አንድ ሙሉ ማዳበሪያ ድፍድፍ ነበር የቀረው። ግን ጉሹን ቅመሺው እስኪ እትዬ መወፈሩንና መቅጠኑን"አለችና በመቀነሻ ቀንሳ ሰጠቻት። ጥጥት አድርጊው ገብስ ነው። ጌሾ ትንሽ ነው ያለው" ሔዋን ጠጣችው። በጣም ይጥማል ጭልጥ አድርጋ ጠጣችና እቃውን ሰጠቻት " በጣም ጥሩ ነው። ከዚህ በላይ መወፈርም መቅጠንም ያለበት አይመስለኝም"አለች ሔዋን አፏን እየጠራረገች። "እሺ "አለችና ዳሳሽ መጥመቋን ቀጠለች።
"እንዴት አይነት ግሩም የሆነ ጠላ ነው! እንዴት አድርጋ እንዳዘጋጀችው ብታይ"አለች ሔዋን ለሙሉሰው "እኔ ርኮ የወሎን ባህላዊ ጠላ በጣም ነው የምወድላቸው እስኪ ይዘሽልኝ ነይ ሔዋኔ "አለ ሙሉሰው። ሔዋንም ሂዳ አመጣችለት።
"ይሄ ሰርግ በቃ እንደፈለግሽው ሆነልሽ። ኧረ እንደውም ከፈለግሽው በላይ ነው የሆነው ከመጠጥም ብዙ አይነት ሆነልሽ "አለ ሙሉሰው "እንዴታ የመጀመሪያ ሰርጌ እኮ ነው። ለቀጣዮቹ ልጆቼ ልምድም ይሆነኛል። በል እንዲጨመርልህ ከፈለክ ንገረኝ ወይም ሄደህ በሀይላንድ አስቀድተህ ጠጣ" ብላው ወጣች። ሙሉሰው የኮረፌውን አይን እያዬ "እንዲህ ነው እንጅ ሴትነት የቱባው ባለሞያ ሲሆን ይጥማል"እያለ እያጣጣመ ሳለ "እስኪ አባዬ እኔም ልጠጣ ስጠኝ"አለች ኤሊያና "አይሆንም ትሰክሪያለሽ "አለች ሔመን ድንገት ከመኝታ ቤቷ ብቅ ስትል ኤሊያና ከአባቷ ልትቀበል የነበረውን ኮረፌ በመመልከት "ሔሚዬ ይሄ እኮ አያሰክርም ቡቅሬ በይው ንፁህ ገብስ ነው። እና ማርማር ነው የሚለው ከፈለግሽ አንቺም ልትጠጪ ትችያለሽ"አለ። "እሺ አባዬ በርግጥ ከአንተ በላይ ለኤሊ አስቤ ሳይሆን እንዲሁ ከአፌ ስለመጣ ነው ይቅርታ"አለች ሔመን ሀዘኔታ በተሞላ አነጋገር። "ችግር የለም የኔ ማር እኔም የምፈልገው ይሄን ያህል ለእህትሽ እንድትጠነቀቂላትና እንድታስቢላት ነው። እናንተ እርስ በእርስ ስትዋደዱና ሰትተሳሰቡ ሁሉም ነገር ቀናና የተደላደለ ይሆናል። እርስበርስ መጠባበቅ አለባችሁ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ምርኩዝ ነው መሆን ያለባችሁ። መቼም እኛ ለዘላለም አብረናችሁ አንኖርም"አለና ሙሉሰው ሁለቱንም አቅፎ ሳማቸው

@amba88
@ken_leboch