Get Mystery Box with random crypto!

አስታዋሾች...... ፈላጊዎች ወንድሜ በቀን ስንት ሰው ይደውልልሃል? ስንቴ ነው ስልክህ የሚጮኸ | Hossana Gospel movement

አስታዋሾች...... ፈላጊዎች


ወንድሜ በቀን ስንት ሰው ይደውልልሃል? ስንቴ ነው ስልክህ የሚጮኸው? ከዘወትር አፍቃሪህ ከቴሌ ሌላ ስንት ሰው ቴክስትስ ያደርግልሃል?

አዎ አንተ ፈላጊህ ከመብዛቱ የተነሳ ደላላ ሆንክ እንዴ? ትባላለህ ሌላኛው ደግሞ በቀን አይደለም በሳምንት እንኳ ስልኩ ጮኾ የማያውቅ "እኔን ሰው አይፈልገኝም ስለዚህ መኖር የለብኝም" በማለት ራሱን ለማጥፋት የወሰነም አለ። ይህን የምለው እንዲሁ በግምት አይደለም ደቡብ አፍሪካ ላይ የተፈጠረን ክስተት በማስታወስ ነው።

በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካ በተፈጠረው ወቅታዊ ክስተት ሰቢያ ቁጥራቸው ከ5000 በላይ በሚሆኑ ወጣቶች ላይ በተደረገ ጥናት መሰረት ተቀባይነት በማጣት ስሜት ህይወታቸው ጥያቄ ውስጥ እንደነበር በየሚድያው የውይይት ርዕስ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ምክንያቱ ከሞባይል ጋር በተያያዘ ሲሆን እነዚህ ወጣቶች በያዙት ተንቀሳቃሽ ስልክ ይደውላሉ እንጂ አይደወልላቸውም። ይህ ደግሞ አንድ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አስገደዳቸው በቃ እኛ ተፈላጊዎች አይደለንም የሚል። በዚህ የተነሳ ብዙ የስነልቦና ባለሙያዎች ሙሉ ለሙሉ የትኩረት አቅጣጫቸውን ወደ እነርሱ አደረጉ።

" የሰው ልጅ ሊያስተናግደው የማይችል ከባድ ነገር በሰው ዘንድ ተቀባይነት ማጣት ነው" የሚባለው ለዚህ ነው። ቃየል ወንድሙን አቤልን የመግደሉ ምክንያት በእግዚአብሄር ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ነው። ቃየል ፈገግታና ደስታ የማይለየው ሰው ነበር መሰል እግዚአብሄር "ለምን ፊትህ ጠቆረ መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አልነበረምን" ዘፍ 4፥6 ሲለው እንመለከታለን።

ወንድሙ አቤልን በመግደል ሞት ምን እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰው ልጆች ሁሉ እንደመልካም ነገር አስተዋወቀ። አይ አለመታደል ቃየል ሞትን ሲያስተዋውቀን ጌታ ደግሞ ህይወትን አስተዋወቀን፤ ቃየል በወንድም ላይ መጨከንን ሲያስተዋውቀን ጌታ ደግሞ ርህራሄን አስተዋወቀን።

ወዳጆቼ ብዙ ነገሮችን እንደቀላልና እንደተራ ነገር እንቆጥራቸው ይሆናል ከዚህ መሀል መጥፋታችን አሳስቧቸው የሚደውሉልን፣ የድምፃችን ሽታ ናፍቋቸው የሚደውሉ፣ እኛን ሲያወሩ የሚደሰቱ ሲደውሉልን "ደግሞ ደወለ" ብለን ደቂቃ ለመስጠት እንወጠራለን። እኛ እንደ ተራ እንየው እንጂ እግዚአብሄርን የምናመሰግንበት ርዕሳችን መሆን ነበረበት።

ብዙ ድምፅ የራባቸው ባዶ ጆሮዎች ባሉበት የኛ ጆሮ የወዳጅን ድምፅ መስማቱ መታደል ነው። እኛም ሰው ሆነን ናፈከኝ ተብለን ሲደወልልን መታደል ነው። ዛሬ ስለኛ ተጨንቀው ጠፋችሁ ብለው የሚደውሉልን ወዳጆች ካሉን በሰው ልብ እንድንታሰብ ያደረገን እግዚአብሄር ይመስገን።

ጠፋህ ብላችሁ ስለምትደውሉልኝ፣ በልባችሁ ስለምታስቡኝ፣ እንደ ወላጅ መውጣት መግባቴ ጨንቋችሁ ለምትደውሉልኝ ሁሉ ክብረት ይስጥልኝ እግዚአብሄር በልቡ መዝገብ ይፃፍልኝ ተባረኩልኝ።


#በወንጌል_አላፍርም