Get Mystery Box with random crypto!

አንቺ ለኔ .....እኔም ላንተ           ሕይወት ውሏ ጠፍቶብሽ መኖሬ ማንን ይጠቅማል? አ | Hossana Gospel movement

አንቺ ለኔ .....እኔም ላንተ

   
      ሕይወት ውሏ ጠፍቶብሽ መኖሬ ማንን ይጠቅማል? አለመኖሬስ ማንን ይጎዳል? እያልሽ ከራስሽ ጋር ተናንቀሽ ይሆን? አይዞሽ እህቴ ታስፈልጊያለሽ። አንቺ ለዚህች ምድር ለውጥ ፈጣሪ ባለ ብዙ አቅም ብርቱ ሴት ነሽ። እግዚአብሄር የፈጠረኝን ቦታ ብቻ ሸፍኜ ልኑር አትበይ። አንቺ የምታኖሪው ብዙ ነፍስ አለ። ያለ አንቺ የማይሞላ፣ ያለ አንቺ ጎዶሎ የሆነ፣ ያለ አንቺ የማይደምቅ ብዙ ነገር አለ። ዛፍ የተተከለበትን ቦታ ብቻ ሸፍኖ አይኖርም እኛንም ያኖራል። አንቺም ለብዙ ተርፊያለህሽ። ዛፍ የተቃጠለውን አየር ውጦ ኦክስጅን የሚተነፍሰው ለኛ ነው። ያለማቋረጥ ህይወት ይሰጠናል። አንድም ቀን ተሳስቶ ሞትን ሰቶን አያውቅም ሁሌም ህይወትን ይተነፍስልናል።

   ታውቃለህ ወንድሜ? አሁን ከመንገድህ ባገኘኸው ታክሲ ብትገባና ታክሲ ሰው ጭኖ ሞልቶ ሊሄድ ሲል ወራጅ ብለህ ከታክሲው ብትውርድ የሞላው ታክሲ ይጎላል። ታክሲው አይሄድም ረዳቱ መጥራቱን ይቀጥላል፤ አንድ ሰው የሞላ ይላል፤ አንተ ያጎደልከውን ቁጥር ሊሞላ ቆሞ ሌላ ሰው ይጠብቃል።

    እንዲህ አድርገህ አስበው! አንተ ከታክሲው በመውረድህ ታክሲው ሌላ ሰው ለመጫን ሶስት ደቂቃ ቢቆም ረዳቱንና ሹፌሩን ጨምሮ በአስራ ሶስት ሰው ህይዎት ላይ የሶስት ደቂቃ ልዩነት ፈጥረሃል ማለት ነው። አስበው አንተ ብቻህን የአስራ ሶስት ሰው ህይዎት ላይ ሶስት ደቂቃ ታጎላለህ። በተቃራኒው አስበው አስራ አንድ ሰው ጭኖ አንድ ሰው የሞላ ለሚል ታክሲ ሮጠህ ብትገባ ሞልቶ ቢሄድ ለነዚያ ለአስራ አንዱ ተሳፋሪዎች የሆነ ደቂቃ በህይዎታቸው አትርፈሃል።

    ይሄ ነው የአንተም የአንቺም በህይዎት የመኖር አስፈላጊነት! የኔ በህይዎት መኖር ለማንም አይጠቅምም አትበሉ። ካላጎረስክ፣ ካላለበስክ፣ ገንዘብ ካልሰጠህ መኖርህን የምትረሳ ከሆነ የእውነት መኖርህን ዘንግተሀል ወዳጄ ምክንያቱም ካላጎረስከው የማይጠግብ፣ ካልሰጠኸው የማያገኝ ብዙ አለ። ህይወት መዋቅሯ እርስ በእርስ የተገመደ ነው። እጄን ያዘኝ እጅህን ልያዝህ ታስፈልገኛለህ እኔም አስፈልግሃለው።

     ወዳጆቼ ለሰው ቀርቶ ለእግዚአብሔር ታስፈልጉታላችሁ። ባንተ ምስክርነት በአንተ ስብከት የእግዚአብሔር መንግስት ይሰፋል። እግዚአብሔር በአንተ ብቻ የሚሰራው ስራ አለው። እግዚአብሔር በአንቺ ብቻ የሚሰራው ስራ አለው። አለምልጠቅምም አትበይ ካንቺ በላይ ጠቃሚ ማን ነው ከአንተ በላይ ጠቃሚ ሰው ማን ነው? በርቱና በተስፋ ኑሩ!


#በወንጌል_አላፍርም