Get Mystery Box with random crypto!

ከዲያቆን ብርሃኑ ሳታነቡት አትለፉ አቤቱ በእኔ በኩል እለፍ ፡፡ ጌታ ሆይ በኢያሪኮው መንገደኛ | "ቃለ እግዚአብሔር "



ከዲያቆን ብርሃኑ ሳታነቡት አትለፉ

አቤቱ በእኔ በኩል እለፍ ፡፡

ጌታ ሆይ በኢያሪኮው መንገደኛ በኩል እንዳለፍህ ይህች ዐመት ከማለቋ በፊት እባክህን በእኔም በኩል እለፍ፡፡ የጠፋውን በግ አዳምን የፈለግኸው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አቤቱ እኔንም ፈልገኝ፤  ባገኘኸውም ጊዜ እንደተሸከምኸው እኔንም ተሸከመኝ፡፡ የቀደመ ፍጥረትህን አዳምን ቸል እንዳላልከው ከእርሱ አብራክ የተገኘሁ እኔ ደካማ ልጁንም  ቸል አትበለኝ፡፡ ይልቁንም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንድ ሰው የተባለ አዳምን እንደተሸከምከው እኔንም ተሸከመኝ፡፡
አዎን ጌታ ሆይ በመንገድ ላይ የወደቀው ስም የለሽ አንድ ሰው እኔ እንደሆንኩ አውቂያለሁ፡፡ ከኢየሩሳሌም ልዕልና ነፍስ ወደ ኢያሪኮ የኃጢአት ቁልቁለት የወረድሁት እኔ እንደሆንኩ ገብቶኛል፡፡ አንተ ለእኔ ድኅነት የሠራኸውን አሸቀንጥሬ ጥዬ እኔን ካስቀመጥክበት ከፍታ ተንደርድሬ ለእኔ ፍላጎት ወደሚስማማው ቁልቁለት የወረድሁት በወንበዴዎች እጅም የወደቅሁት የኢያሪኮው መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ በምሥጢራት ከሚኖርበት ተግባራዊ የክርስትና ከፍታ በማስመሰልና በውድድር ወደሚኖርበት ዝቅታ የወረድሁት ስም የለሽ መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ በእውነትና በፍቅር ከሚኖርበት የወንጌል ተራራ ጥቅሶችን ወደፍላጎታችን ወደሚለጥጥ ገደል የወረድሁት የተመታሁ መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ አንተን በሕይወቴ አሳድሬ አንተ በእኔ እንድትሠራ ከሚያደርግ ከፍታ እራሴን ለአንተ የሚሠራ ወታደር ወደሚያስመስል የሕይወት አዘቅት አውርጄ የጣልኩት የቁልቁለት መንገደኛው እኔ ነኝ፡፡ ሰለወደቀው በማዘን ስለእርሱም በመጸለይ እውነተኞቹ ልጆችህ ከኖሩበት ከፍታ ሁሉንም ወደሚያስንቅና ወደሚያስተች ዝቅታ የወረድሁት መንገደኛ እኔ ነኝ፡፡ ነገሮችን በመንፈስና በአስተውሎት ከመመርመር በስሜትና በግብታዊነት ወደማበላሽበት ጉድጓድ የወረድሁትም እኔ ነኝ፡፡ በእቅድና በጥበብ ከመሥራት በትችትና በነቀፌታ በእልህና በብስጭት ወደመናገር ብቻ የወረድሁት ከንቱ በእውነት እኔ ነኝ፡፡ ጥቂቶቹን ልዘርዝር ብዬ እንጂ ጌታ ሆይ እኔ ያልተውኩት ሰገነት፣ ያልወደቅሁበትም አዘቅት ምን አለና፡፡

ስወርድ ደግሞ እንደተጻፈው ወንበዴዎቹ አገኙኝና ደበደቡኝ፡፡ የነበረችኝንም ሁሉ ቀሙኝ፡፡ ጌታ ሆይ እየወረድኩም ይዠው ከነበረው ያልቀሙኝ ምንም የለም፡፡ መጀመሪያ የቀሙኝ ስንገዳገድ የምደገፍባትን፤ አቀበት ቁልቁለት የማቋርጥባትን፤ አራዊትን የማርቅባትን፣ ሰንቅና ጓዜን የምሸከምባትን አንዷን ዘንጌን ጸሎቴን ቀሙኝና ድጋፍ አልባ አደረጉኝ፡፡ ተነሥቼ ልጸልይ ስቆም አካሌ እንደ ሐውልት ቆሞ ነፍሴን ይዘዋት ይዞራሉ፡፡ አንዳንዴ ጥርሴን ያስነክሱኛል፡፡ አንዳንዴ ስለአንተ ተቆርቋሪ አስምስለው ጦርነት ውስጥ ይከቱኛል፡፡ ሌላ ጊዜ በአንተ በኩል ማግኘት የሚገባኝን ጥቅም ያሳስቡኛል፡፡ ሌላ ጊዜ አንተ የማያስደስቱ የሚመስሉኝን እንድትቆርጥ እንድትጥል ያሳስቡኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተረሳ ዘመድ ወዳጅ፣ የሞተ የጠፋ ቤተሰብእ ሳይቀር እያሳዩ ተመስጦ በሚመሰል ሕይወት ውስጥ ያጃጅሉኛል፡፡ የቀረ ሥራ የከሰረ ሀብትም አሳስበው ያናድዱኛል፡፡ ብቻ ነፍሴን የማይወስዱበት ቦታ የለም፡፡ ብሞት እንኳ መልአከ ሞት ነፍሴን ሊየንገላታት የማይችለውን ያህል ነፍሴን ያንከራትቷታል፡፡ ጸሎቴን ቀምተው ነፍሴን ማረፊያ ያጣች አሞራ አስመሰሏት፡፡ ስለዚህም የውስጥ ሰላሜ ተነጠቀ፡፡ እንኳን ከሌላው ከትዳር አጋሬ ከወላጅ ከቤተሰቤ በሰላም መነጋገሬን ሁሉ አከታትለው ቀሙኝ፡፡

ትዕግሥቴን ነጥቀዉ እንደ ፍየል ለፍላፊ፣ እንደ ጉጉት ጯሂ አደረጉኝ፡፡ ለሚናገረኝ ካልመለሰኩለት፣ የሚመለከተኝን ካልገላመጥኩት የተጠቃሁ እያስመሰሉ በመልካም የመመለስ ሀብቴን ዘረፉኝ፡፡ ይባስ በለው ልዩነቴን በእወቀት ከማስረዳት፣ ለመግባባት ከመወያየት አፋትተው የተለየለት ግልፍተኛ ተሳዳቢ አደረጉኝ፡፡ አሁንማ ካልተሳደብኩ ዐለም መሸነፌን አውቆ  የሚስቅብኝ እያስመሰሉ እንኳን ይቃረኑኛል ለምላቸው በሀሳብ ይቀርቡኛል የምላቸውንም በእኔ መንገድ ስላልተናገሩ ብቻ የማላደላ ጀግና በማስመሰል እንድወርፋቸው ያደርጉኛል፡፡

ወደ ቀደመ ሕይወቴ እንዳልመለስም መንገዱን አጠሩብኝ፡፡ ጉባኤ ሔጄ እንዳልማር ጊዜ የማባክን ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ መምህራንንም በትችት ስላስናቁኝ የመቀመጥ ትዕግሥቴ ራሱ የት እንደገባ አላውቅም፡፡ በጓደኛ ተጽእኖ ስቀመጥም ለእኔ ብሎ ከመስማት ይልቅ ይህ ለእነ እገሌ ነበር የሚያስፈልግ ያሰኘኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዛሬም ይህን ይሰብካል እንዴ ያሰኘኛል፡፡ እኔ በማዘወትረው ኃጢአት ሳላፍር መምህሩ የሚታወቅ ትምህርት አስተማረ ብሎ አያፍርም ወይ ያሰኘኛል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሚነገረውም አሽሙርና የማይረባ ያስመስልብኛል፡፡ እዚህ ከምማር በቃ ቤቴ ተቀምጬዬ አነብባለሁ ብሎ ካስተዋኝ በኋላ ቤቴ ስገባ ቴሌቪዥን ጋር ያፋጥጠኛል፡፡ እርሱ ሲሰለቸኝ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የወጣ ነገር እንድመለከት በጓደኞቼ በኩል ያስደውልብኛል፡፡ እንደምንም ታግዬ ላነብብ ስነሣ እንቅልፍ እንደበረዶ ያዘንብብኛል፡፡

በቃ በጎው ነገር ካመለጠኝ በኋላ አልያዝ አልጨበጥ አለኝ፡፡ ምክር እንዳልጠይቅ ትልቅና አዋቂ ሰው ነው በሚባል የገጸ ባሕርይ ካባ ሸፍነው አሳፍረውኛል፡፡ ከዚህ ሁሉ የተነሣ በነፍሴ ሕመም ሥጋዬም ታማሚ ሆነ፡፡ እንደወፈረኩ ደከማ፣ እንደጠገብኩ ልፍስፍስ አደረጉኝ፡፡ እንዳልጾም ሰውነቴ ሁሉ እንቢ አለ፡፡ እንዳልሰግድም ጉልበቴ ሁሉ ተብረከረከ፡፡ በሁሉ ባዶ ሆኜ ቁጭ አልኩ፡፡

የነፍሴ መድኃኒት ጌታዬ ሆይ አፍ ማብዛቴን፣ ነገር መውደዴን አይተህ ነው መሰል አፍን በማስክ የሚያስይዝ የተግሣጽ ደዌ ብታመጣም የእኔ ነፍስ ግን አሁንም አላስታዋለችም፡፡ እጆቼ ማስኩን አፌ ላይ ቢያደርጉም ምላሴን ሊያስቆሟት ግን አልቻሉም፡፡ አንተ ለደቀመዛሙርትህ እንዳልከው አፍን የሚያረክሰው ከውጭ የሚገባው ሳይሆን ከውስጥ የሚወጣው ነውና ከነፍሴ ቁስል የተነሣ በአፌ የሚወጣው የነገር ጠረን አካባቢውን አሸተተው፡፡ እንኳን ለሌላው ለእኔም እየተሰማኝ ቢሆንም ነፍሴን የደበደቧት ወንበዴዎች ግን እንድነቃ አልፈቀዱልኝም፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ የአፍ ብቻ ሳይሆን የልብና የኅሊና ማስክ እዘዝልኝ፡፡ እንደ ዳዊት ወዳጅህ ለአፌ ጠባቂ ሹምለት፤ ከንፈሮቼንም እንደ ቤተ መቅደስህ በር በምሕረትና በእውነት የሚከፈቱ አድርግልኝ፡፡ ጌታ ሆይ አሁን ችግሬ ገብቶኛል፤ ማስክ የሚያስፈልገኝ ለውጨኛው ሳይሆን ለውስጠኛው የኅሊና አፌ ነው፡፡ ጸረ ተሐዋሲ መድኃኒትም ከሥጋዬ ይልቅ ለነፍሴ እጆች እንደሚያስፈልጋቸው ገብቶኛል፡፡ አቤቱ ሰነድ በመደለዝ፣ ደም በማፍሰስ የረከሱ እጆቻችን በምን ይነጻሉ? የሐሰት ትርክት በመተረክ፣ የበለው ግደለው ቅስቀሳ በመጻፍ የዋሆችን በማነሣሣት ደም ያፈሰሱ የምሁር እጅ ነኝ የሚሉ የነፍስ እጆቻችንስ ቤትኛው ሳኒታይዘር ይነጻሉ? ጌታ ሆይ ዘንድሮ ሁሉንም ችግሮቼን ነግረኸኛል፡፡ በተለይ ርቀት ያለመጠበቅ፣ ቦታዬንም ያለማወቅ ችግር አስታውሼው አላውቅም ነበር፡፡ የእኔማ የተለየ ነው፡፡ እንኳን በሾምካቸው በጳጳሳት በካህናት በአንተ ወንበር ተቀምጬ ስፈርድ፣ ስገድል ሳድን፣ ስሰጥ ስነሣ ነው የኖርኩት፡፡ በወንጌል አልገባ ቢለኝ በበሽታ አስመስለህ ርቀትህን ጠብቅ ብትለኝም ልመለስ አልቻልኩም፡፡ ግን ወድቄያለሁና ተነሥቶ መቆም ርቀቴንም መጠበቅ እንዳይቻለኝ ደርገው ወንበዴዎቹ አጋንንት ስወርድ አግኝተው ደብደበውኛልና ተመልሶ መቆም ተሣነኝ፡፡