Get Mystery Box with random crypto!

ነሐሴ 12-ቅዱስ ሚካኤል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረደቶ በድል ያነገሠበት ዕለት ንግስት ዕሌኒም በ27 | "ቃለ እግዚአብሔር "

ነሐሴ 12-ቅዱስ ሚካኤል ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን ረደቶ በድል ያነገሠበት ዕለት

ንግስት ዕሌኒም በ272ዓ.ም ታላቁ ቆስጠንጢኖስን ወለደችለት፤ ቆስጠንጢኖስም ገና በወጣትነቱ የአባቱ እንደራሴ ሆኖ እንዳሠራ አባቱ ሞተ፡፡ የአባቱ ባለሟሎችና ህዝቡ ተስማምተው የ18 ዓመቱን ቆስጠንጢኖስን በአባቱ ቦታ ሐምሌ 25 ቀን 300ዓ.ም በሮም ምዕራብ ክፍል በገላትያ አነገሡት፡፡ በጦር ሜዳዎች ብዙ የጀግንነት ሥራዎች ስለሠራ በሠራዊቱ ዘንድ ይወደድ ነበር፡፡
ንግሥት ዕሌኒ ልጅዋን ቆስጠንጢኖስን ከልጅነቱ ጀምሮ ስለክርስትና ሃይማኖትና ስለክርስቲያኖች መከራ ታስተምረው ስለነበር በክርስቲያኖች ላይ የነበረው አመለካከት በሮም ከነገሡት ቄሣሮች ሁሉ የተሻለ ነበር፡፡ በተለይም በ312 ዓ.ም ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር ለመዋጋት "ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት" ብሎ ለዘመቻ እንደተሰለፈ በራእይ በሰማይ ላይ "በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ; የሚል መስቀልና ጽሑፍ ስላየ ለሠራዊቱ ሁሉ የመስቀል ምልክት በመሣሪያቸውና በሰንደቅ ዓላማው ላይ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ወደያው ጦርነት ቢገጥም በቲቤር ወንዝ ድልድይ ላይ ጠላቱን ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግስት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ሆነ፡፡ ይኸውም የሆነው በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ነው፡፡
ሚካኤል ማለት መኑ ከመ እግዚአብሔ "እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?" ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ለፍጥረታት ሁሉ የሚራዳና የሚያዝን የምሕረትና የመዳኛ፤ የሰላም መልአክ ነው፡፡ ‹‹በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል›› (ዳን.12፥1) በማለት በነቢዩ ዳንኤል የተነገረ ሲሆን በሌላ ቦታ ‹‹ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ›› (ዳን. 10፥13) በማለት ያስረዳል፡፡
በድርሳነ ሩፋኤል ላይ እንደተገለጸው ሰባት ሊቃነ መላእክት ቢኖሩም አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል አርምሞ ትዕግሥትን የሚወድ መልአክ ነው፡፡ ‹‹የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፡፡››
ቅዱስ ሚካኤል ከእግዚአብሔር በተሰጠው ኃይል ዲያብሎስን ድል የነሣ መልአክ ነው፡፡ "በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፡፡" ራእ 12፥7-9፡፡
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በመላእክት አለቃ በቅዱስ ሚካኤል ረዳትነት ጠላቶቹን ሁሉ ድል ነሥቶ በጠቅላላው የሮም መንግሥት ግዛቶች ሁሉ ገዥ ከሆነ በኋላ በ300 ዓመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ለክርስቲያኖች የነጻነት ዐዋጅ ዐወጀ፡፡ ክርስትናም ብሔራዊ ሃይማኖት ተባለች፡፡
ንግሥት እሌኒም በተፈጠረላት አመች ሁኔታ በመጠቀም የጌታችን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት በ327ዓ.ም ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ዕሌኒ ልጅዋ ቆስጠንጢኖስ ክርስቲያን ከሆነላት ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን ለመፈለግ እንዲሁም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳት መካናትንና አብያተ ክርስቲያናትን ከማነጽ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ ከዚህ በኋላ ቆስጠንጢኖስ አምኖ በ337 ዓ.ም ተጠመቀ፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች ከእርሷም ጋር ብዙ ሠራዊት ነበር፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በጸሎቱ የምንታመን ሁላችንን የመልአክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤልን ረድኤት በረከቱን ያሳድርብን፡፡ በጸሎቱ ይማረን፡፡
(ምንጭ፡- የነሐሴ ወር ስንክሳር)