Get Mystery Box with random crypto!

የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ “እንተ በአማን ንጹሕ ዝናም” የተባለ፣ የነፍሳትን ጥም ያበረደ የሕ | "ቃለ እግዚአብሔር "

የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ

“እንተ በአማን ንጹሕ ዝናም” የተባለ፣ የነፍሳትን ጥም ያበረደ የሕይወት ዝናም፣ የሕይወት ጠል፣ የሕይወት ውሃ ክርስቶስን ቋጥረሽ (በድንግልና ፀንሰሽ፣ በድንግልና ወልደሽ) የታየሽልን እውነተኛ ደመና አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “ንዑ እንከ ከመ ናልዕላ ለዛቲ ደመና ብርሃን እንተ ጾረቶ ለማየ ዝናም ንጹሕ" "ንጹሑን የዝናም ውሃ የተሸከመችውን የብርሃን ደመና ኑ ከፍ ከፍ እናድርጋት” ብሎ ጋብዞናል /አርጋኖን ዘሠሉስ ፮፡፪7። ስትወልጂው ማኅተመ ድንግልናሽ አለመለወጡ፤ አካላዊ ቃል ሰው ሲኾን አምላክነቱ  ላለመለወጡ፣ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባዪ  መኖርሽም ልጅሽ አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው) ሲባል ለመኖሩ ምሳሌ ነውና አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ቢያድርብሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ቢለብስ፤ አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት (ማለትም ከሩካቤ፣ ከዘር፣ ድንግልናን ከመለወጥ) ቢከለክልሽ፣ ኀይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ  ግብራት ቢከልልሽ ለዘላለሙ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን  /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/። እርሱም ሰው ኾኖ ከኃጢአት አንድም ከኃጢአታችን ፍዳ አዳነን።

ደስ ያለህ ባለ ምሥራች ገብርኤል ሆይ! ወደኛ የመጣ የጌታን ልደት ነግረኸናልና ላንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ አንድም “ወነዋ ተወልደ ፍስሐ ዘይከውን ለክሙ ወለኩሉ  ዓለም" "እነሆ ለሕዝቡ ኹሉ የሚኾን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ” ብለህ /ሉቃ.፪፡፲/የጌታን ልደት ለኖሎት (ለእረኞች) ነገርኻቸዋልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ “እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ  ካንቺ ጋራ አንድ ይሆናልና ደስ ይበልሽ” ብለህ /ሉቃ.፩፡፴/ ለእመቤታችን ነግረኻታልና ለአንተ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኚልን፡፡