Get Mystery Box with random crypto!

#የማክሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እ | "ቃለ እግዚአብሔር "

#የማክሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

ለምስጋና ኹለተኛ፣ ለፍጥረት ሦስተኛ ቀን በሚኾን በዚህ ቀንም እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ምንጻፍ ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኾናም፡- “ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም” ትለዋለች፡፡ እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፡፡ ክርክር በዕለተ ሰኑይ አልቋልና “ባርክኒ” ብሎ ተባርኮ “አክሊለ ምክሕነ” ብሎ ምስጋናውን ይጀምራል፡፡

፩. ዳዊት ምንም ንጉሠ ነገሥት ቢባል የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም /፩ኛሳሙ.፲፮፥፲፫/፡፡ ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢኾንም የደኅንነታችን መጀመሪያ መኾን አልተቻለውም፡፡ ኤልያስም ምንም ንጹሕ፣ ድንግል ቢኾንም የንጽሕናችን መሠረት መኾን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፣ የንጽሕናችን መሠረት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የመመኪያችን ዘውድ “አክሊለ ሰማዕት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የደኅንነታችን መጀመርያ “ጥንተ ሕይወት” የሚባል ጌታችን ነው፡፡ የንጽሕናችን መጀመርያም ኹሉ በእጁ የተጨበጠ፣ ዓለምንም በመዳፉ የያዘ፤ በጠፈር ላይ የሚቀመጥ ፣ ዳግመኛም መሠረቱን ከታች የሚሸከም “መሠረተ ዓለም” የሚባል ጌታችን ነው /ቅዳ.ማር. ቁ.፶፩/፡፡ እርሱም አካላዊ ቃልን በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፡፡ እኛን ስለማዳን ሰው ኾነ፤ ሰውም ከኾነ በኋላ ግን ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ እንደ ወለደችው ኹሉ እርሱም አምላክነቱ ሳይለወጥ ሰው ኾነ፡፡ እርሷ “ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም)” ስትባል እንደምትኖር ኹሉ እርሱም “አምላክ ወሰብእ (ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው)” ሲባል ይኖራል /ሃይ.አበ.፷፯፡፯/፡፡ ተፈትሖ ሳያገኛት (ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ) እንደምን እንደወለደችው ግን የማይመረመር አንድም ሊነገር የማይችል፣ ከኅሊናት ኹሉ የሚያልፍ ድንቅ ነው፡፡
በማይመረመር ግብር ከወለድሽው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. “ቃል ሥጋ ኾነ” እንዲል በእርሱ ፈቃድ /ዮሐ.፩፡፲፬/፣ “ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” እንዲል በአባቱ ፈቃድ /ዮሐ.፫፡፲፮/፣ “በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው” እንዲልም /ሐዋ.፲፡፴፰/ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሰው ኾኖ አዳነን፡፡ ሊቁ እንዲህ ማለቱ “ወልድ ያለ ፈቃዱ ሰው ኾነ” የሚሉ መናፍቃን ስላሉ ነው፡፡ ሌሎች ሊቃውንትም፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ያለ ፈቃዱ ሰው እንደ ኾነ የሚያምን፤ የሚያስተምር፤ ወይም የአብ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የወልድ ፈቃድ ሌላ ነው፤ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ሌላ ነው የሚል ቢኖር፤ ፈቃዳቸው አንድ፤ መንግሥታቸውም አንድ እንደኾነ የማያምን ሰው ቢኖር ውጉዝ ይኹን” ብለው አስተምረዋል /ሃይ.አበ.፻፳፫፡፪/፡፡

በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ ፍጽምት የምትኾኚ እመቤታችን ሆይ! በድንግልና ጸንተሽ ብትገኚ ላንቺ የተሰጠሸ ጸጋ ፍጹም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ካንቺ ጋራ አንድ ባሕርይ ቢኾን አንድም በጸጋ ቢያድርብሽ ባለሟልነትን አግኝተሸልና ለአንቺ የተሰጠ ክብር ፍጹም ነው፡፡ ይህ ከቃላት በላይ የሚያልፈው ባለሟልነቷ ቅዱስ ባስልዮስ ከሌሎች ቅዱሳን ጋር እያነጻጻረ ሲያብራራው፡- “የዚህ ዓለም ነገር ኹሉ አይመጥናትምና የሚመጥናትን ምን ዓይነት ምስጋና እናቅርብላት? ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ዓለም አልተገባቸውም /ዕብ.፲፩፡፴፰/ ካላቸው ከከዋክብት በላይ ኾና እንደምታበራው ፀሐይ ለኾነችው ለአምላክ እናትማ ምን ልንል እንችል ይኾን?... ምን ምሥጢር እንደተከናወነ ተመልከት፤ ኅሊናን አእምሮን የሚያልፍ ነገር እንደኾነም አስተውል፡፡ ታድያ የአምላክ እናት ታላቅነት እንደምን ኹሉም ሰው አይናገር? ማንስ ነው ከቅዱሳን ኹሉ በላይ እንደኾነች ያላስተዋለ? እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ የሚልቅ ጸጋን ከሰጠና የሚነኩት ኹሉ ሰው ከበሽታው ከተፈወሰ፣ ጥላቸው ያረፈበት ተአምር ከተፈጸመለት፣ ጴጥሮስ በጥላው ካዳነ /ሐዋ.፭፡፲፭/፣ የጳውሎስ የልብሱ ዕራፊ መናፍስትን ካወጣ /ሐዋ.፲፱፡፲፩/ ለእናቱማ ምን ዐይነት ሥልጣንና ኀይል ተሰጥቷት ይኾን? በምን ዓይነትስ ሥጦታ አስጊጧት ይኾን? ጴጥሮስ፡- ክርስቶስ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ስላለው ብፁዕ ነህ ከተባለና የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ከተሰጠው /ማቴ.፲፮፡፲፮-፲፱/ እርሷማ ከኹሉም ይልቅ እንዴት ብፅዕት አትኾን? /ሉቃ.፩፡፵፭/ ጳውሎስ ታላቅ ክብር ያለውን የክርስቶስን ስም በመሸከሙ ምርጥ ዕቃ ከተባለ /ሐዋ.፱፡፲፭/ የአምላክ እናትማ የምእመናን ምግብ የኾነ መናውን ሳይኾን የሕይወት ሰማያዊ እንጀራን ያስገኘች እርሷ ምን ዓይነት ልዩ ዕቃ ትኾን? … ነገር ግን ስለ እርሷ ብዙ እናገራለሁ ብዬ ስለ ክብሯ ጥቂት በመናገር ራሴን በኀፍረት ውስጥ እንዳልጨምር እፈራለኁ፡፡ ስለዚህ ከአሁን ወዲህ የንግግሬን መልሕቅ ስቤ በዝምታ ወደቤ ላይ ማረፍን መርጫለሁ”  ይላል /መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ፣ ነገረ ማርያም በሐዲስ ኪዳን፣ ገጽ ፺-፺፩ ይመልከቱ/፡፡

ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ያያት የወርቅ መሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲፰-፲፱/፡፡ መተርጕማኑ ይህ ምን ማለት እንደኾነ ሲያብራሩ፡- “ከምድር እስከ ሰማይ መድረሷ የልዕልናዋ፣ በላይዋ ላይ ዙፋን ተነጽፎባት ንጉሥም ተቀምጦባት ማየቱ ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀኗ ለመሸከሟ፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ማየቱ ደግሞ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ለማሳረግ አይወጡም አይወርዱም ነበር፤ ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከኾነ በኋላ ግን ለተልእኮ የሚወጡ የሚወርዱ ኾነዋልና ሲል ነው”  ይላሉ /ሉቃ.፪፡፲፬፣ ሐዋ.፲፡፫-፬፣ የኦሪት ዘልደትን ትርጓሜ ይመልከቱ/፡፡

ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ በአምሳለ ንጉሥ ካየው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን