Get Mystery Box with random crypto!

ዐቢይ ጾም ሰኞ መጋቢት 2 ይገባል በቤተክርስቲያን ስያሜ መሰረት በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚውሉ ሰንበታ | 💎ስለ ማርያም አማላጅነት እንመሰክራለን✍

ዐቢይ ጾም ሰኞ መጋቢት 2 ይገባል
በቤተክርስቲያን ስያሜ መሰረት በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚውሉ ሰንበታት እያንዳንዳቸው መጠሪያ ስም ሲኖራቸው እነርሱም፡-
ዘወረደ
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሰንበት ሲሆን ይህም ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምን ፈጥሮ የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ከሰማየ ሰማያት መውረዱንና ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ከንጽሕተ ንጹሐን ከድንግል ማርያም መወለዱን የሚያመለክት ሥያሜ ነው፡፡

ቅድስት
ይህ የሁለተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን ቅድስት የተባለበትም ምክንያት ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ስለሚያወሳ ነው፡፡ እንዲሁም ይህ ዕለት ዕለተ እግዚአብሔር የተባለች የሰንበት ክርስቲያን ቅድስናን ያመለክታል ምክንያቱም የዚች ዕለት ጌታ እርሱ ቅዱስ እግዚአብሔር ነውና ስለዚህም ዕለተ ሰንበት ቅድስት ተብላለች፡፡

ምኩራብ
ይህ የሦስተኛው ሰንበት ስያሜ ሲሆን በዚህ ሰንበት ጌታ በመዋዕለ ትምህርቱ በምኩራብ ገብቶ ማስተማሩ ይነገራል፡፡ እንዲሁም ይህች ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ገብቶ እንዳስተማረ የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡ ምኩራብ ማለት የቤተ አይሁዳውያን የጸሎት ቤት ነው፡፡

መጻጉዕ
ይህ የአራተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ እውራንን ማብራቱ ለምጻምን ማንጻቱ ሽባዎችን መተርተሩ የሚያነሳ መዝሙር የሚዘመርበት እንዲሁም እነዚህ ሁሉ ድንቅ ገቢራተ ታምራቶች የሚዘከሩበት ዕለት ነው፡፡

ደብረ_ዘይት
ይህ የአምስተኛው ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ነገረ ምጽአቱን እንዳስተማረ የሚወሳበት ሰንበት ነው፡፡ ደብረ ዘይት ማለት ወይራ የበዛበት ተራራ ማለት ነው፡፡

ገብርኄር
ይህ የስድስተኛው ሳምንት ሰንበት ስያሜ ሲሆን ይህም ዕለት ለጌታው ታማኝና በጎ የሆነው ባርያ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ተብሎ እንደተመሰገነ የሚነገርበት ዕለት ነው፡፡

ኒቆዲሞስ
ይህ የሰባተኛው ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ይህም ዕለት ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ መምህር በሌሊት ወደ ጌታው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እየመጣ ይማር እንደነበረ ይታሰብበታል በዚም ዕለት የኒቆዲሞስን ታሪክ የሚያስታውስ መዝሙር ይዘመርበታል፡፡

ሆሳዕና
ይህ የስምንተኛው ሳምንት ሰንበት መጠሪያ ሲሆን ይህም ዕለት በነቢዩ በዘካርያስ ላይ የተጻፈው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቷ እና በውርንጭላይቷ ላይ ተቀምጦ ሆሳዕና በአርያም ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ እየተባለ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱ የሚተሰብበት ዕለት ነው፡፡ ሆሳዕና ማለት ‹‹እባክህ አሁን አድን አሁን ባርከን›› ማለት ነው፡፡በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው::
ጾሙን የበረከት ጾም ያድርግልን፡፡