Get Mystery Box with random crypto!

‍ እንዳልነበር ከእማ በኋላ ዳግመኛ አላገባም፡፡ እኛን ለማሳደግ በሚችለው አቅም ልክ ጣረ፤ ምናልባ | ISLAM IS SCHOOL️

‍ እንዳልነበር ከእማ በኋላ ዳግመኛ አላገባም፡፡ እኛን ለማሳደግ በሚችለው አቅም ልክ ጣረ፤ ምናልባትም ከሚችለውም ከሚቻለውም በላይ፡፡ የተሰራ ምግብ ለራሱ አቅርቦ ለመብላት የማይፈልገው አባዬ እኛ እንድናጠና በየቀኑ ከስቶቭ እና ከክሰል ጋር ሲታገል፣ ያደፈን ጨርቅ ለማንጻት ሲዳክር ኖረ፡፡ ይሰራበት የነበረውን ቤት አከራይቶ ገቢውን አብቃቅቶ ለመጠቀም ሞከረ፤ እንደምንም ተሳካለት፡፡ ችግሮችን ሁሉ ድል ለመምታት በጣረ ቁጥር ከአንደበቱ ላይ አንድ ቃል አይጠፋም ነበር፤ "አልሀምዱሊላህ!" አሁን አባዬ አለም ላይ እውነተኛ ደስታ ካገኙ ጥቂት ሰዎች መሀከል አንዱ ነው፡፡

ከአዲሱ ክፍሌ ውስጥ ከድሮው የመጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ ጥቁሩን ማስታወሻዬን አነሳሁ፡፡ አለፍ አለፍ እያልኩ የጻፍኳቸውን ማንበብ ያዝኩ፡፡ ሮዟ ማስታወሻዬ ጠፍታ እንደረሳሁት ሁሉ ጥቁሩን ማስታወሻዬንም እንደምረሳው መንገሬን አነበብኩ፤ ግን አልረሳሁትም፡፡ ጥቂት ተጨማሪ ገጾችን ሳገላብጥ ግን አንተ እያልኩ አወራው የነበረውን ማስታወሻዬን "ጥቁር ማስታወሻዬ" ብዬ እየጠራሁ ውሎዬን እንደማጠራቅምበት ተራ ወረቀት መቁጠሬ ገባኝ፡፡ ይቅርታ ጥቁሩ ማስታወሻዬ ካ'ሁን ጀምረን ወደድሮው ጓደኝነታችን እንመለሳለን፤ ይቅርታ ካደረግክልኝ፡፡

አንተን ማገላበጤን እንደቀጠልኩ ካ'ንደኛው ገፅህ ላይ ደርሼ ያገኘሁትን ጽሁፍ በቃሌ እስክይዘው ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩት፤ ቆይ ልንገርህ፡
ᐸ"እማ! በአንደኛ ሴሚስተር አንደኛ የወጣውን ልጅ፤ አዩብን ታውቂዋለሽ አይደል?"
"መስጂድ ውስጥ ጫማ የሚጠርገውን ነው?"
"አዎ!"
"እኮ የዘይነብ ልጅ፤ ቅያሱ ጋር የተከራዩት?"
"እህ... እማ! አዎ እያልኩሽ፡፡"
"ምን ያስመርርሻል? ሆ! ጨምላቃ! አሁን ምን ልትነግሪኝ ነው?"
"ትናንት ከቀረ ሶስት ቀን ሆነው፤ ትምህርት ቤት መጥቶ አያውቅም፡፡"
"እና አንቺ ምን ቤት ነሽ?"
"አይ... ጓደኛውን ስጠይቀው የቤት ኪራይ ስለበዛባቸው እንዳይባረሩ ለመክፈል እየሰራ እንደሆነ ነገረኝ፡፡"
"እስኪ አባትሽን አማክረዋለሁ፤ መቼስ ዝም አይል?"
"አመሰግናለሁ እማ!" ቀና ብዬ ሳምኳት፡፡
"ዝምበይ! ሠባኪ... ዘንድሮ ግን እንዳይበልጥሽ፡፡ ተጋድመሽ መዋል አብዝተሻል፡፡ አታዪም እንዴ እንዴት እንደወፈርሽ?"
"የአራት ሠው ምግብ እያስያዝሺኝ ነዋ! ተይ ብልሽ እምቢ አልሽኝ፡፡"
"ቀኑን ሙሉ እየዋልሽ እንዳይርብሽ ብዬ ነዋ! ቁርስሽንም ስትቻኮይ ሳትበዪ ነው የምትወጪው፡፡"
"ለነገሩ ዛሬ የምበላውን በነገታው ምሣዕቃዬን እየተሸከምኩ አቃጥለው የለ?"
"ኧረግ ኧረግ ነገረኛ ሁነሽ የለ እንዴ?"
"ግን ያንቺም ሆድ ጨምሯልኮ፡፡ የሚገፋ ይሁን የሚጠፋ ግን አልገባኝም፡፡"
አሁንም ሣቀች፤ "ድርሠት አልተውሽም ማለት ነው?"
"ኧረ ለምን ብዬ"
"እና ለኔ የሚሆን ግጥም ነገር አልጻፍሽም?" አለችኝ ጸጉሬን እያሻሸች፡፡
"ቆይ በኋላ አነብልሻለሁ፡፡">
:
ያኔ ትዝ ይልኃል አይደል፤ በእማ ሞት ደንግጬ የጻፍኩላትን ግጥም ሆስፒታሉ ውስጥ ስጥለው፡፡ ምናልባትኮ ያ ግጥም አሁንም ድረስ ከቆሻሻ ውስጥ ሆኖ አሊያም ከቆሻሻዎች መሀከል ተቃጥሎ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን የጻፍኩትን አዲስ ግጥም ግን ላንብብልህ፤ ከመሳቢያው ውስጥ ነበር ያስቀመጥኩት፡
:
ᐸእዚህ ኑሮ ይኖራል፣ በገሚሱ ይገፋል፣
ገሚሱን ይገፋል
ገሚሱ ይገፋፋል፣ ገሚሱ ተገፍፎ
ሌላውን ይገፍፋል
ከሙታንስ መንደር፣ ከትቢያው ግርጌ ላይ ህይወት እንዴት ቀጥሏል?
እዚህ ሠው ይገድላል፤ የሟች ደም እንዲደርቅ ሌላ ደም ይፈሳል
ከናንተ መንደርስ ሠው ይተራረዳል፤ መጋደል አይሏል?
ከኛ ከህያዋን ከቆሞ ሂያጆቹ ከኗሪዎች መንደር
የተነሳች ንፋስ ትቢያ አለበሰችኝ ልቤን ልታሸብር
በዓይኔ ውስጥ ገባች ልቤን ልታሳውር
በጆሮዬ ገባች ልቤን ለማደንቆር
የንፋሷ አብራክ ጽንሷ ትቢያ ጎድታኝ
እኔ ልጅሽ አለሁ ትንሿን ትቢያ ሠርክ እየረገምኩኝ
ከዚያ ትቢያ ግርጌስ እማ ካንቺ መንደር
ቋጥኝ ያህሉ ትቢያ ምን ያህል ይጥራል ልብሽን ለማወር
ርግማን ከጅሎ በጆሮሽ እየገባ ልብ ሊያደነቁር
ወይስ ከናንተ ዘንድ ከሙታኖች መንደር
ርግማን ይሉት ወግ መታወር መደንቆር
ስሜትየለሽ ናቸው በዓለመቀብር
★★★
እዚህ እኛ ዓለም ላይ ካለው ትልቅ ሠማይ
ከባድ ዶፍ ይወርዳል ስቃይን የሚያሳይ
በእትትት ዜማ ዳንኪራ የሚያስመታ
እኔ ነኝ ያለውን በአቆርፋጅ ብርዱ ባንዴ የሚረታ
ይኼ ከባድ ዶፍ የሠማዩ አብራክ መሬት ውስጥ ይሰርጋል
ከሙታኖች መንደር ከትቢያውስ ግርጌ ይኼ ዶፍ ይዘልቃል?
እትትት እያስባለ እስክስታ ያስወርዳል?
ከጋቢ ከእሣት ጥግ ከቤት ያስመሽጋል?
ወይስ ከናንተ ዘንድ በሙታኖች ባህል
እትት ይሉት ዜማ መብረድ የሚሉት ቃል
ትርጉም አልባ ሆኖ ሲሰሙት ያስቃል?
★★★
እዚህ እኛ መንደር ከህያዋን መሀል
ፀሐይ ይሏት እሣት ሠውን ስታበስል
ከሠማይ ተነስታ በግዙፍ ጨረሯ መሬት ላይ ስትደርስ
ሁሌ እገረማለሁ...
አቅሟ ይችል ይሆን ያንን ትልቅ ቋጥኝ ንዶ ለመደርመስ?
እኔ ምን አውቃለሁ እስኪ አንቺ ንገሪኝ
የፀሐይዋ ንዳድ ምን እንደሚያደርግሽ በደንብ አብራሪልኝ
የፀሐይዋ አብራክ ያ ግዙፍ ጨረሯ ከናንተ ጋር ዘልቆ
ንፋስን ያሰኛል እብድስ ያስመስላል ልብስን አስወልቆ?
ወይስ በናንተ ዓለም ሙቀት ያልኩት እኔ
መፍታት የማይችሉት ሆኖብሻል ቅኔ
እስኪ ሁሉን ንገሪኝ ህይወት እዛ እንዴት ናት
እናንተ መንደር ውስጥ እማን የኔን ህይወት ማንነው የሚቀልባት
ወይስ መራብ መጥገብ ፈጽሞ አይነካካት?
★★★
እዚህ በ'ኛ መንደር እኔ ባለሁበት
ትዝታሽ ለምዶኛል ይመጣል በድንገት
ረዣዥሙ ጣትሽ ጸጉሬን ይፈትጋል
የአዘቦት ድካምሽ የኔን ሆድ ለመሙላት ዘላለም ይጥራል
የአንድ ቀን ቁጣሽ ሁሌም ያቅበኛል
የአንድ ቀን ምክርሽ ካሰብኩት ያደርሰኛል
ድምፅሽ፣ ሽታሽ መልክሽ ዛሬም ይታየኛል
ዛሬም ያውደኛል፣ ዛሬም ይሰማኛል
ካ'ንቺስ መንደር እማ ትዝታ ምን ይላል?
ያኔ እማ ያልኩሽ አሁንም ይሰማል?
መቆም ያቃተኝ ቀን አንቺን መደገፌ ሁሌም ይገርምሻል?
የያኔው ጥፋቴ ዛሬም ያስቆጣሻል?
ስኬት ደስታዬስ ያፍነከንክሻል?
ወይስ በናንተ ዓለም ትዝታ ይሉት ቃል የማስታወስ አብራክ
ትርጉምየለሽ ቃል ነው ልክ እንደ "ሶጵቺራክ"
ረስተሽኝ ይሆን ላታስታውሽ መቼም
ወይስ በናንተ ዓለም መርሳትም የሚሉት አንዳችም ቃል የለም?>

ጥቂት ቆይቶ ቤቱ ቀስበቀስ ይወካ፣ ይፈካ ጀመር፡፡ ሩቂ፣ ሰሎሜ፣ ሰባህ፣ ነዋል፣ አክስቶቼ፣ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው... እኔ ወዳለሁበት ክፍል ይመጡ ጀመር፡፡ ጋሽ ሳላህ፣ ማሂር፣ ዛኪር፣ አጎቴ፣ የሩቂ ባል... ሳሎን ውስጥ ከአባዬና ማሜ ጋር ማውራት ያዙ፡፡" ቤቱ ይጮህ ጀመር፡፡"

የግቢው በር ተንኳኳ፤ ተነስቼ ከፈትኩ፤ ሰሙ ነበረች፡፡
.
.
.
ይቀጥላል

SHARE SHARE
╔════════════╗
JOIN: @islam_in_school
JOIN: @islam_in_school     ╚════════════╝