Get Mystery Box with random crypto!

የሰሚራ ማስታወሻ ክፍል ስምንት Rayan Huda ...ልክ እንደአዲሱ ማስታወሻዬ ጠቆረ፡፡' ፡ | ISLAM IS SCHOOL️

የሰሚራ ማስታወሻ
ክፍል ስምንት
Rayan Huda

...ልክ እንደአዲሱ ማስታወሻዬ ጠቆረ፡፡"

አሁንም ከአልጋዬ አልወረድኩም፤ ዛሬ መቼም ጉድ ነው፤ ምሣ ሰዓት ተቃርቧል፤ የዝሁር ሰዓትም እየደረሰ ነው፡፡ 'ማንበብ የማይወደው የሰሚራ ባል ካልጋው ላይ እንደተንጋለለ አንድ ጥቁር ማስታወሻ ሲያገላብጥ ዋለ፤ ያውም የሚያውቀውን ከዚህ ቀደም የሰማውን ታሪክ፤ ያውም ከገጽ ገጽ እየጓጓ፤ በሚስቱ የቃላት አደራደር እየተደመመ'፣ ይህ የአመቱ ምርጥ ቀልድ መሆን አለበት፡፡ እኔ እኮ ሰሙ በሚያባብሉ የዋህ ዓይኖቿ እንድትጽፍ የሚያነሳሳትን የጥሞና ጊዜ እንድሰጣት ስትማጸነኝ ሳላንገራገር እስማማለሁ፡፡ ከዚያ ግን የጻፈችው ምን እንደሆነ ሳልጠይቃት ጊዜያት ይነጉዳሉ፡፡ ዝምታዬ በጨመረ ቁጥር መንጨርጨሯ ይግልና አፌን ምን እንደለጎመው ትጠይቀኛለች፤ ዝም እላለሁ፡፡ ከጊዜ በኋላ ሰለቻት መሰለኝ ምን እንደጻፈች አለመጠየቄን ከመጤፍም አለመቁጠር ያዘች፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከመደርደሪያዋ ላይ አንዱን መጽሐፍ መዥርጣ ልትተርክልኝ ትጀምራለች፣ እኔ ሆዬ በእንቅልፍ እጦት እንደምንገላታ ሁሉ ረስቼ ጭል...ጥ እላለሁ፤ ሰሙ ከእንቅልፌ ትቀሰቅሰኝና ድጋሚ ልትተርክልኝ ትሞክራለች፤ እኔ አሁንም ወደእንቅልፍ ዓለም ለመመለስ አኮበኩባለሁ፡፡ ዛሬ የሚታተመውን የመጀመሪያ መጽሐፏን እንኳ አልጨረስኩትም፡፡ ትናንት ማታ ለዛሬ የሚሆን ምሳ እያዘጋጀን የመጽሐፏን ታሪክ እንደዋዛ ጠየቀችኝ፡፡
"ያው አንድ ንጉስ ነበር፤ ሚስቱ ታመመችበት..."
"ይህንንማ ህጻን ልጅም ይፅፈዋል፡፡ በታሪኩ ውስጥ ያለውን ሀሳብና የሚያስተላልፈውን መልዕክት ነው እንድትነግረኝ የፈለግኩት" ቆጣ ትላለች፤ እኔ አይኖቼን በየዋህነት እያቁለጨለጭኩ ዝም እላለሁ፡፡ ዛሬ ወደመጽሀፍ ምረቃው የሄዱት በርከት ብለው ነው፡፡ ትናንት ማታ ለሁላችንም የሚሆን ምሳ ስንሰራ ነበር ያመሸነው፡፡ አሁን ከመምጣታቸው በፊት ሁሉን አዘጋጅቼ ብጠብቃቸው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ቢሆንም ጥቂት ጊዜ አለኝ፡፡ ማስታወሻዉን ዘግቼ በርካታ ገፆችን ዘልዬ እጄ ወደመራኝ ገጽ ገለጥኩ፤ የማስታወሻው መሀከለኛ ገጾች ላይ ጉብ አልኩ፡፡

"በአዲሱ ቤታችን፣ አዲሱ ክፍሌ፣ አዲሱ ባለመስታወት መስኮት ላይ አፍጥጬ ደጁን እያማተርኩ ነው፡፡ ከሳምንት በኋላ ደግሞ ወደሌላኛው አዲሱ ቤቴ፤ አዲሱ ክፍሌ አቅንቼ በአዲሱ መስኮት ድሮንም፣ አሁንንም፣ ወደፊትንም እመለከት ይሆናል፡፡ የወደፊቱን ማን ያውቃል? ደጅ ላይ ማቲዎች እግር ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ከማሜ ጋር በእድሜ የሚስተካከሉ በለቀያይ ጢማም ታዳጊዎችም ከህጻናቱ ጋር ይጫወታሉ፤ ማሜ ግን አብሯቸው የለም፤ እያጠና ነው፡፡ ለቀጣይ አመት የማትሪክ ፈተና ዘንድሮ የ11ኛ ክፍል ትምህርትን እያጠና ነው፡፡ እንደኔ ከስድስት መቶ በላይ ለማምጣት ይሻል፡፡ በተለይ አስረኛ ክፍል ላይ "ስትሬይት ኤ" አምጥቶ ካለፈ በኋላ ሞራሉ ተነሳስቷል፡፡ ማቲዎቹ ከሚጫወቱበት አቧራማ ሜዳ ትይዩ ጸሐይ በደመናዎች ተሸብባ ትታያለች፡፡ ጸሀይዋ ራሷ የበረዳት ነው የምትመስለው፡፡ የወትሮው አቃጣይነቷ ዛሬ የለም፡፡ ማቲዎቹ የሚጫዎቱበትን ሜዳ ንፋሱ ትቢያውን እያነሳ ከማቲዎቹ ላይ ያራግፍለታል፡፡ ጋቢዬን እንደተከናነብኩ አዲሱን ሰፈር ማስተዋሌን ቀጠልኩ፡፡ ዓሊ፣ ከንቱዎች ያከነተቷት ድንጋይ፣ ቅያሷ ጋር የተከራዩት እነዘይነብ፣ ታመው የሚጠየቁ ዒማም፣ በሠንጢ የወጋ ዱርዬና በሠንጢ የተወጋን ልጅ በመኪናው ሆስፒታል የሚያደርስ ሽማግሌ... የሌሉባት ሰፈር፡፡ ከጸሀይዋና እንደጋቢ ከጠቀለላት ሸበቷም ደመና ገለል ብሎ ያደፈ የጥጥ ባዘቶ የመሰለ ዝናብ አዘል ደመና ይታያል፡፡ ንፋሱ አሁንም አሁንም ትቢያውን እያነሳ ከህፃናቱ ፊትና ልብስ ላይ ይከምረዋል፡፡ በጸሀይዋ ወበቅም ትቢያ ባዘለው ንፋስም ሊበገሩ ባለመቻላቸው ስደነቅ ጥቁሩ ደመና ድንገት እዬዬውን ይለቀው ጀመር፤ ምናልባትም በህጻናቱ ስቃይ አዝኖ እያነባ ይሆን እንዴ? ማዘኑ ግን ይበልጥ ጎዳቸው እንጅ አንዳንች ነገር አልፈየደላቸውም፡፡

ስልኬ ድንገት ጠራ፤ ሰሎሜ ናት፤ ሲስተር ሰሎሜ፡፡
"ሄሎ ዶክተር!"
"ሰሎሜ! እንዴት ነሽ?"
"ደህና ነኝ፡፡ ዛሬ ሆስፒታል ውስጥ ሳጣሽ ነው'ኮ"
"አዎ ፍቃድ ወሰድኩ፡፡"
"ለሰርገሽ እንዳይሆን?" ድምጿ መደነቋን ያስተጋባል፡፡
"አዎ ለሰርጉ ነው፤ ረፍት ወስጄም አላውቅም፡፡ በዚያ ላይ የምከታተላቸው ፔሸንቶች የሉኝም፡፡ ባለፈው ፓራላይዝድ ሆነው የመጡት ፔሸንት በፊዚዮቴራፒ እያገገሙ ነው፡፡ የኤፒለፕሲ ታማሚ ወጣቱም ቢሆን መድኃኒቱን እየወሰደ ነው፡፡ ከሁለቱም ጋር በስልክ ኮንታክት እያደረግን ነው በዚያ ላይ አዳዲስ ፔሸንቶች መጥተው እኔ ካስፈለግኩ እንዲደወለልኝ ተነጋግሪያለሁ፡፡"
"አለቃሽ መሰልኩሽ እንዴ? ሪፖርት ነው'ኮ የሚመስለው፡፡"
"ማወቅ ከፈለግሽ ብዬ ነው፤ ደግሞም ጠይቀሽኛል፡፡"
"እኔ ስለሰርጉ ነው ማወቅ የምፈልገው፡፡"
"ለምን ዛሬ አትመጪም?"
"በቃ ከሆስፒታል እንደወጣሁ እመጣለሁ፡፡"
"ጥሩ"፤ ስልኩን ዘጋችው፡፡

አሁንም ከመስኮቱ ፊትለፊት የቆመችው እናቷ በሞተች ቀን ራሷን ስትስት የዓሊ ድምፅ "ህይወትሽ ሶጵቺራክ ሆናለች፡፡" እያለ ያቃጨለባት ሴት አይደለችም፡፡ የሱረት አል ኢሻራህን የመጨረሻ አንቀጾች ሰምታ ተስፋ የሰነቀችው እንጅ፡፡ ከዓመታት በፊት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ማትሪክን ጥሩ ውጤት አምጥታ አለፈች፣ ብዙዎች የማይደፍሩትን የህክምና ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ገብታ አጠናች፣ እንደአባቷ ላሉ ህሙማን የመዳኛ ሰበብ ትሆን ዘንድ በኒውሮልጂ ስፔሻላይዝ አደረገች፣ በራሷ ጥረት ቁርዓንን ሐፈዘች... ይህችው ከመስታወቱ መስኮት ፊት የቆመች ሴት፡፡ አሁን ደግሞ ልታገባ ነው፤ አዩብን ልታገባ፡፡"

ስልኬ ጠራ፤ ንባቤን ገታ አድርጌ ተመለከትኩ ሰሙ ናት፤ መምጫቸው ደረሰ ማለት ነው፤ ስልኩን አነሳሁት፡፡
"አሰላሙዓለይኩም አዩቤ!"
"ወዓለይኩም አስሠላም ሰሙ! ዝግጅቱ እንዴት ነበር? ብዙ ነገር አለፈኝ?"
"አሪፍ ነበር፡፡ ሲያንዛዙት እየተመለስኩ ነው?"
"እንዴ? የገዛ መጽሐፍሽን ምርቃት ትተሽ?"
"ታውቃለህ፤ አዘጋጆቹን እንዲያሳጥሩት ነግሪያቸው ነበር፤ እምቢ አሉ፤ ትቻቸው መጣሁ፡፡"
"እነማሜስ?"
"ብቻዬን ነኝ፤ ልሎቹ እዚያው ናቸው፡፡"
"ዝግጅቱን ግን ማቋረጥ አልነበረብሽም፡፡"
"ለምን ሲባል? አንብበህ አልጨረስክም እንዴ?"
"ምኑን?" ግራ ገባኝ፡፡
"ጥቁሩን ማስታወሻዬን ነዋ!"፤ ሣቀች፡፡
"በምን አወቅሽ?"
"የባሌ ጸባይ እንዴት ይጠፋኛል?"
"አዎ አልጨረስኩም" የእፍረት ሳቅ ሳቅኩ፡፡
"በቃ መጣሁ፤ እንቅልፍ የማይወስድህ ከሆነ እኔ አነብልሀለሁ፡፡" ሣቀች፤ ሣቅኩ፡፡
"እሺ!" ስልኩን ዘግቼ፤ ወደንባቤ ተመለስኩ፡፡

"አዎ ይህኛው አዩብ፤ የዚያኛውን አዩብ ስሙን ብቻ ይያዝ ወይስ ግብሩን ጭምር በመጠኑ ብቻ ነው የማውቀው፡፡ የአባዬንም የራሴንም ብዙ ህልሞች ማሳካት ችያለሁ፡፡ የቀረኝ ነገር ቢኖር የራሴን ህይወት መጀመር ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የእናቱን ህልም ለማሳካት የቋመጠን ወጣት ለማግባት ወስኛለሁ፤ ከአባዬ ጋር ተማክረን፡፡ ይህኛው አዩብ መስጂድ ውስጥ ጫማ የሚጠርገው፣ የዘይነብ ልጅ ቅያሷ ጋር የተከራዩት አይደለም፡፡ ያ አዩብ ላይመለስ አሸልቧል፤ ይህኛው ልላ ነው፡፡

እማ ከሞተች በኋላ አባዬ በምንም ነገር ላይ ተስፋ እንዳልቆርጥ ይመክረኝ ነበር፡፡ መንገር ብቻ አይደለም፤ በተግባር አድርጎ አሳየኝ፡፡ እማን እኔ ከሞትኩ እንድታገባ ምከሪያት ሲለኝ