Get Mystery Box with random crypto!

' አንዳንዴ…………………………………… አንዳንዴ ነገሮች ከመወሳሰባቸው የተነሳ መግለፅ እስከሚከብድ | ISLAMIC SCHOOL

" አንዳንዴ……………………………………

አንዳንዴ ነገሮች ከመወሳሰባቸው የተነሳ መግለፅ እስከሚከብድ ድረስ ቃል ይጠፋል ። የሚመጣው ፣ የሚሄደውና የሚቀረው በመሰለው መልኩ ሀሳቡን ይፈተፍታል ። አንዳንዴ በመኖራቸው ብቻ ደስተኛ የሚያደርጉን ሰዎች አሉ ። ብዙ ፍራፍሬዎች ቢኖሩ አንዷን ፍሬ በተለየ መልኩ ለኛ ጣፋጭ ትሆናለች ። ያቺ ፍሬ ግን ጥፍጥናዋን አታውቅም ። አንዳንዴ ልብ ገና በእንጭጩ ይሸብታል ፣ በቧልት ፣ በቅስም ሰባሪ ንግግሮች ለጥሩ ነገር መበርታት ተስኖት ያረጃል ። ያን የሸበተ ልብ ከሽበቱ መሀል ውበቱ የሚታየው ሌላ ልብ ስለመኖሩ አያስተውልም ። አንዳንዴ ሰው መሆን ክብሩ ይወርዳል ፣ ፣ መኖር ከሞት ያንሳል ፣ እስትንፋስ ይከረፋል ። አንዳንዴ ሰው መሆን ከግዑዝ በታች ይሆናል ። ግዑዛን ግን ሰው መሆን ባለመቻላቸው መለጎማቸውን ባለ አንደበቱ አይረዳም ። አንዳንዴ በጨዋ ማልያ ባለጌ ሲያገባ የልክነት ሚዛን መጠኑ ይዛባል ። በጥሩና በመጥፎ መሀል አለመገኘት ፣ ከሁለት አንዳቸው አለመሆን ይከሰታል ። አንዳንዴ ሰው ሆነው ሰው መፍራት ይገጥማል ፣ ብቸኛ ከመሆን በላይ ከሰው ጋር መሆን ያስፈራል ። አንዳንዴ ቁራጭ ፍቅር የሚወረውር ጠፍቶ በብቸኝነት ረሀብ አብሮነትን መለመን ይለመዳል ። አንዳንዴ ተስፋ ከማጣት በላይ ተስፋ ማጣትን ማሰብ ያሳምማል ። አንዳንዴ እድለኛ ያልሆኑ ሰዎች እድለኛ አደላቹም ብለው በንግግራቸው እድለቢስነታቸውን ያቀብሉናል ። ነገር ግን እድለኛ ስለመሆናችን ማሰብ ያቃተን ንግግራቸውና የነደፈን መርዛቸው መሆኑን አናምንም ። አንዳንዴ የመከራ መዓት የተሸከምን ፣ አቅመ ቢስ እንደሆንን ፣ መኖራችን ፋይዳ እንደሌለው ይሰማንና ትክክል ነው ብለን አምነን ቀናችንን ማስጌጥም ማጠልሸትም የሚችለው እኛነታችን እየገደልነውና አሰልቺውን ጎዳና እያደላደልን ለመጓዝ እየተዘጋጀን መሆናችንን ረስተን ሰበብ አምላኪ እንሆናለን ። አንዳንዴ የደስታችን ምንጭ እራሳችን መሆናችንን ዘንግተን መደሰትንም እንፈራለን ። አንዳንዴ ሰብዓዊነታችንን ደብቀን ፣  ክብራችንን አዋርደን በሰዎች ዘንድ ክብራችንን እንፈልጋለን ።አንዳንዴ ትካዜዎች ትዝታ ይሆናሉ አልፈው ይታወሳሉ ። አንዳንዴ በሰማይ ላይ ጨረቃና ከዋክብት እየደመቁ ፣ ከደመቁበት ሰማይ በበለጠ ይደነቃሉ ። አንዳንዴ ፀሀይ ትናፈቅና ስትበረታ ትሰለቻለች ። አንዳንዴ……………………………………………………………………………………………………………… ከብዙ ንክሻ በኋላ መሻር ፣ ከብዙ ንድፊያ በኋላ ማገገም ፣ ከበሽታ በኋላ ፈውስ ፣ ከብዙ ጨለማ በኋላ ንጋት ፣ ከጦርነት በኋላ ሰላም ፣ ከማጣት በኋላ ማግኘት ፣ ከመሀይምነት በኋላ እውቀት ፣ ከሴት በላይ እናት ፣ ከወንድ በላይ አባት ፣ ከበደል በኋላ ፍትህ ፣ ከጥላቻ በላይ ፍቅር ፣ ከሁሉም ነገሮች በላይ የሁሉም የበላይ ፈጣሪ አለ ። ከብዙ…………………………………………እጅግ ከብዙ ነገሮች በኋላ ጥሩ ነገሮች አሉ ። ነገር ግን ወደፊት ጥሩ ነገሮች ስለመኖራቸው የተጠራጠሩ በጥርጣሬያቸው ወድቀው የሚጠሉትን ወደውና ፈቅደው ለሚጠሉት ተገዝተው ይኖራሉ ። "
     የጉዞ ማስታወሻዬ(@ቶፊቅ)

Join
t.me/IslamisUniverstiy_public_group
  t.me/IslamisUniverstiy_public_group