Get Mystery Box with random crypto!

በስነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡ በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ | Injibara University

በስነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ፡፡
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ለ195 የግቢ ጸጥታና ደህንነት ሠራተኞች በሥነ ምግባር ምንነት፣ በሥራ ሥነ ምግባር እና በዩኒቨርሲቲው የአመራር አካላትና ሠራተኞች የሥነ ምግባር መመሪያ ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ከፍ በማድረግ የሙስና ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት አስቀድሞ ለመከላከል እንደሀገር የተያዘው የሙስና መከላከል ስትራቴጂ አካል መሆኑን ስልጠናውን የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደሳለው ጌታሁን አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ሙስና በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ሶስተኛው አንገብጋቢ ጉዳይ በመሆኑ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት ተረድቶ ችግሩን ለመከላከል እንዲሁም አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በሀገር ደረጃ ኮሚቴ አቋቁሞ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ዜጋ ተገቢውን ስነ ምግባር ከመላበስ ባሻገር በሙስናና ብልሹ አሰራር ላይ የተሰማሩ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ጥቆማ በመስጠት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ስልጠናውን ያስተባበሩት የዩኒቨርሲቲው የግቢ ፀጥታና ደህንነት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ፈንታ ስልጠናው ለግቢው የጸጥታና ደህነት ስራ አጋዥ ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም ዜጋ ለሀገራዊ የፀረ ሙስና ትግል የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስገነዝብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት ሙስናን ከመከላከል አንጻር ቀደም ሲል በየደረጃው ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲው አካላት ተከታታይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ማከናወኑ ይታወቃል።

ታኅሳስ 27/2014 ዓ.ም፤