Get Mystery Box with random crypto!

ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ~ ትላንት አንድ 'ኡስታዝ' አንዲትን እህት በብሄሯ ምክንያት ከምትማርበ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል
~
ትላንት አንድ "ኡስታዝ" አንዲትን እህት በብሄሯ ምክንያት ከምትማርበት ግሩፕ አባረራት ተብሎ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይሄው በርካታ ፀረ ኢስላም የሆኑ አካላት ለድሪቶ ፖለቲካቸው ጉዳዩን እየተጠቀሙበት እያየን ነው። ትላንት ጀምረው ጉዳዩን የተለያዩ ክፉ ትርጉሞችን እየሰጡ ማራገብን ተያይዘውታል። እነዚህ ደም መጣጭ የኢስላም ጠላቶች በሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በመሸፋፈን የታወቁ ናቸው። አንድ ማን እንደፃፈው እንኳ የማይታወቅን ፅሁፍ ግን ተቆርቋሪ መስለው እያራገቡ ነው። ለነዚህ አካላት ይህንን ረብ የለሽ ነገር ያቀበሏቸው ደግሞ የኛው በዘር ልክፍት የተለከፉ አካላት ናቸው።
ምን ማድረግ ነበረብን? ጉዳዩ እውነት እንኳ ቢሆን የጠላት መጠቀሚያ እንዳይሆን ከማራገብ ይልቅ በልኩ መያዝ ነበረብን። ይህንን የምለው ከዚህ የተሳከረ የዘር ፖለቲካ ይልቅ ኢስላማቸውን ለሚያስቀድሙ ነው። ፖለቲካው አስክሯቸው ከካ'ፊ'ር ጋር ለተለጠፉ አካላት እንዲህ አይነት ፊትና ቀስቃሽ ቅንብሮች መራገባቸው ለነሱ ስኬት ነው። ነገ ከአላህ ፊት መቅረብን የሚያስብ አማኝ ግን የዘር ጥላቻ ዐቅሉን እስከሚያስተው ድረስ አይዘቅጥም።

ጉዳዩን አጣራን ብለው ያወጡ ሰዎች አይቻለሁ። ያደረጉት ነገር ቢኖር ባለ ጉዳይ የተባለችዋን እህት ደውሎ መጠየቅ ነው። አጠፋ የተባለውንስ ኡስታዝ አናግረዋል? የለም! ነገር እንደዚህ ነውንዴ የሚጣራው? ሰው ለራሱ የማይወደውን አካሄድ እንዴት በሌላው ላይ ያደርጋል? እስኪ በራሳችሁ ላይ አስቡት። አንዲት ሴት በከባድ ዘረኝነት ወነጀለቻችሁ እንበል። ሰዎች ጉዳዩን ማጣራት ፈለጉና እሷ ጋር ደውለው "እውነት ነው ወይ?" ሲሏት "አዎ" አለቻቸው። ከናንተ ማረጋገጫ ሳይወሰድ ያለቀ እውነት ተደርጎ ቢራገብ ደስ ይላችኋል? ማጣራት ማለት እንደዚህ ነው? በጭራሽ! ከሳሽና ተከሳሽ ሲኖር ነገር የሚጣራው ከሁለቱም በኩል ነው። ከከሳሽ በኩል ተጨባጭ ነገር ቢኖር ራሱ በተከሳሽ በኩል ያለውን ማወቅ ይገባል። ምክንያቱም ያገኘነውን እውነታ ሙሉ ይዘቱን የሚቀይር fact ተከሳሽ ዘንድ ሊኖር ይችላልና። "አንድ ከሳሽ 'ይሄው አንድ አይኔ ጠፍቷል፤ ፍረድልኝ' ቢልህ እንዳትፈርድለት። ምናልባትም ተከሳሹ ሁለት አይኑ ጠፍቶ ሊሆን ይችላል" የሚል በዐሊይ ስም የሚወራ የጥበብ ንግግር አለ። የተከሳሹ ብሄር ሌላ ስለሆነ ብቻ ለመፍረድ ልንቸኩል አይገባም።

መረጃ እንዴት ነው የሚጣራው?
በኢስላም ከሳሽና ተከሳሽ ሲኖር ማንም በደመ ነፍስ አይጓዝም። የራሱ ስርአት አለው። ይህንን ስርአት ማክበር ከእያንዳንዱ ሙስሊም የሚጠበቅ ነው። ብዙዎቻችን ጋር ያለው ግን ተከሳሹ የምንጠላው ከሆነ ወይም ጉዳዩ ለምናራግበው የፖለቲካ ፍጆታ የሚያግዝ ከሆነ ከስር ከማጥራት ይልቅ በቀላሉ አምነን ሌሎችንም ልናሳምን መነሳት ነው። መሆን ያለበትስ እንዴት ነው? ነብዩ ﷺ እንዲህ ይላሉ:–
لو يعطى الناسُ بدعواهم، لادَّعَى رجال أموالَ قومٍ ودماءَهم، ولكن البينة على المدعِي، واليمين على مَن أنكر
"ሰዎች በሙግታቸው ቢሰጣቸው ኖሮ ወንዶች የሌሎች ሰዎችን ገንዘቦች እና ደሞች ይሞግቱ ነበር። ነገር ግን በከሳሽ ላይ ማስረጃ አለበት። ባስተባበለ ላይ ደግሞ መሀላ አለበት።" [በይሀቂይ ዘግበውታል።]

የተከሰተውን ጉዳይ በዚህ ሐዲሣዊ መመሪያ ስንመዝነው:-
1- ከሳሿ እህት:- ተጨባጭ ማስረጃ ወይም ምስክር ማቅረብ ነበረባት። ማንም ሊያቀናብረው የሚችል ፅሁፍ ሳይሆን ጥርጣሬን የሚገፍ መረጃ መኖር ነበረበት። ለምሳሌ ካለ የድምፅ መረጃ። ይህንን ማድረግ ካልቻለችስ? "ዋሽታለች" ብለን እንደመድማለን? አይደለም። ይልቁንም ወደ ሁለተኛው ነጥብ እናልፋለን።
2- ተከሳሹ "ኡስታዝ" (የእውነት ካለ)፦ እንዲያምን ካልሆነ ማስተባበያውን በመሀላ እንዲያፀና ይጠየቃል።

ቀረበ በተባለው ማረጋገጫ ግን ሁለቱም አልተደረገም። እሷም tangible መረጃ አላቀረበችም። ኡስታዙም ከነ ጭራሹ አልተጠየቀም። የተባለው ኡስታዝ ከነመኖሩም ማወቅ አይቻልም። ምክንያቱም ከነጭራሹ ማረጋገጫ አልቀረበምና። ይባስ ብሎ የጉዳዩ መነሻ እህት ታማኝ ትሁን አትሁን የሚታወቅ ነገርም የለም። አላህ እንዲህ ይላል፦
{ یَـٰۤأَیُّهَا ٱلَّذِینَ ءَامَنُوۤا۟ إِن جَاۤءَكُمۡ فَاسِقُۢ بِنَبَإࣲ فَتَبَیَّنُوۤا۟ أَن تُصِیبُوا۟ قَوۡمَۢا بِجَهَـٰلَةࣲ فَتُصۡبِحُوا۟ عَلَىٰ مَا فَعَلۡتُمۡ نَـٰدِمِینَ }
"እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬን ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ሆናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተፀፃቾች እንዳትሆኑ አረጋግጡ።" [አልሁጁራት: 6]
በታማኝነቱ የማይታወቅ እና በአመፀኝነት የሚታወቅ ሰው የሚያመጣውን ወሬ ሳያርጋግጡ ሌሎች ላይ መፍረድ አይቻልም። በተለይ ደግሞ በዚህ የዘር አጀንዳ በከረረበት ጊዜ የበለጠ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
"በድጋሜ ማንሳት ለምን አስፈለገ?" የሚል ሊኖር ይችላል። ምክንያቴ የኢስላም ጠላቶች አሁን ድረስ እያራገቡት ስለሆነ መሰል ጥፋቶች ከአላፊ ክስተትነት ባሻገር የሌሎች መጠቀሚያ ስለሚሆኑ ለሌላ ጊዜ በምን መልኩ መያዝ እንዳለብን ማሳሰብ ነው። "ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባልና።"

(ኢብኑ ሙነወር፣ ሚያዚያ 6/2016)
=
የቴሌግራም ቻናል :-
https://t.me/IbnuMunewor